ከአሜሪካ መንግሥት የተበረከተ ከ450 ሺህ በላይ የሚሆን የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባትን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተረከቡ።
በአሜሪካ መንግስት በኩል ለኢትዮጵያ የተበረከተው ይህ “ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን” የተባለው ክትባት ሲሆን፤ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ቃል ከገባችው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶዝ ውስጥ 453 ሺህ 600 ዶዙ በዛሬው እለት አዲስ አበባ መግባቱ ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት በበርካታ ሀገራት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘውን ይህን ክትባት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ በቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ተረክበዋል::
አሜሪካ በሚቀጥሉት ሳምንታት 25 ሚሊዮን ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት ለ49 የአፍሪካ አገራት ድጋፍ እንደምታደርግ ታውቋል።
ለኢትዮጲያ አሁን ከተላከው 453 ሺህ 60 ጠብታ የኮቪድ ክትባት በተጨማሪ በመጪዎቹ 2 ሳምንታት ውስጥ 800 ሺህ መጠን ያለው ክትባት ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል::
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ከአሜሪካ መንግስት የተገኘው የ 453ሺህ በላይ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት በአንድ ጊዜ የሚሰጥ መሆኑ ለሚደረገው የመከላከል ጥረት ፋይዳው ጉልህ መሆኑን አንስተው ከአሜሪካ መንግስት ለተደረገውም ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል::





