ወደ ትግራይ ክልል የሚገባ ማንኛውም ሰብአዊ ድጋፍ ተገቢው ፍተሻ ተደርጎለት በአፋጣኝ ለተረጅዎች እንዲደርስ ለማስቻል ተጨማሪ የፍተሻ ማሽኖች እየተተከሉ መሆኑን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በሰጡት መግለጫ ምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁሶችን የያዙ 61 ከባድ ተሽከርካሪዎች መቀሌ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ሌሎች ተመሳሳይ ቁሳቁሶችን የጫኑ 60 ከባድ ተሽከርካሪዎችም በአፋር ክልል በኩል ወደ ትግራይ በመግባት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ወደ ትግራይ የሚገባ ማንኛውም ሰብአዊ ድጋፍ ተገቢው ፍተሻ ተደርጎለት በፍጥነት ተደራሽ እንዲሆን ተጨማሪ የፍተሻ ማሽኖች (X-Ray) ተከላ በመደረግ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሰርዶና አፍዴራ ሁለት የፍተሻ ማሽኖች እየተገጣጠሙ መሆኑን ጠቅሰው የ10 ማሽኖችም ግዥ እንደሚከናወን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።



