ከጋምቤላ ፣ ከሲዳማ እና ከደቡብ ህዝቦች ክልል የተውጣጡ ልዩ ኃይሎች በመተከል ዞን የግዳጅ ቀጣና ገለፃና የስራ መመርያ ተሰጣቸው

0
904

ከጋምቤላ ፣ ከሲዳማ እና ከደቡብ ህዝቦች ክልል የተውጣጡ ልዩ ኃይሎች በመተከል ዞን የግዳጅ ቀጣና ገለፃና የስራ መመርያ እንደተሰጣቸው ተገለፀ።

በመተከል የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሀይል ኮማንድ ፖስት አባል ብ/ጄ አለማየሁ ወልዴ ለአባላቱ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ፤ በመተከል ተከስቶ ስለነበረው የፀጥታ ሁኔታና ሰላምን ለማስፈን ኮማንድ ፖስቱ ስለፈፀማቸው ተልዕኮዎች እንዲሁም አሁናዊ የመተከል ዞን ፀጥታ ዙሪያ ሰፊ ገለፃ አድርገውላቸዋል።

ከሁለት ሺህ በላይ ታጣቂዎች ስልጠና ወስደው የበደሉትን ህዝብ ይቅርታ የጠየቁበትና ለሰላም እየሰሩ ያሉበት እንዲሁም፤ የህዝብ ለህዝብ የእርቀ ሰላም መድረኮች ተካሂደው በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም የሰፈነበት ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረም አብራርተዋል።

ይህን ሰላም ለማምጣት የኢፊዴሪ መከላከያ ፣ የፌዴራል ፓሊስና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ዘርፈ ብዙ መስዋእትነት መክፈላቸውን ነው የተናገሩት።

“እነዚህ ምቹ ሁኔታዎች በተፈጠሩበት ወቅት ነው ከኢፌዴሪ መከላከያ እና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን የሚሰጣችሁን ተልዕኮ የምትፈፅሙት” ያሉት ብ/ ጄኔራል አለማየሁ፤ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ቀጣናን ፍፁም ሰላማዊ ማድረግ ፣ የሚጓጓዙ ንብረቶችን ደህንነት ማረጋገጥ፣ በጊዚያዊ መጠለያ ላይ የሚገኙ ተፈናቃዮችን መጠበቅና ሰላምን ለማደፍረስ የሚፍጨረጨሩ ሀይሎችን መደምሰስ ዋንኛ ግዳጃቸው መሆኑንም ገልፀዋል።

ግዳጁን ሲፈፅሙ ከአካባቢው ህዝብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መፍጠር እና በፍፁም ወታደራዊ ስነ ምግባር ታንፀው ሊሆን እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

የጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶ ኡኮች በበኩላቸው ፤ የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ የገጠሟትን ከባድ ፈተናዎች ተቋቁማ ሁለተኛውን የህዳሴ ግድብ ሙሌት በስኬት ባጠናቀቀችበት ማግስት ተልዕኮ ተቀብሏል ብለዋል ፡፡ ይህንን ታሪካዊ ተልዕኮ ልዩ ሀይሉ በስኬት እንደሚፈፅም እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ቱት ኮርዳክ እንዳሉት ፤ የክልሉ ልዩ ሀይል ከዚህ በፊት በተሰማራበት ተልዕኮ ሁሉ አኩሪ ገድል የፈፀመ ሲሆን፤ የህዳሴውን ቀጣና ፍፁም ሰላማዊ በማድረግ የክልሉን እና የኢትዮጵያን ህዝቦች ለማኩራት ተዘጋጅተዋል።

የደቡብ ክልል ልዩ ሀይል የሰራዊት አባላት የአርብቶና የአርሶ አደር ልጆች በመሆናቸው አሁን በሚሰጣቸው የግዳጅ ቀጣና ከሚገኙ ህዝቦች ጋር ተግባብቶ ለመስራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል ያሉት የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የልዩ ሀይል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኮሚሽነር አለማየሁ ባውዲ፤ኣ ናቸው።

ከክልላዊ ተልእኮ ወደ ሀገራዊ ተልዕኮ ለመፈፀም መታጨት ታላቅ እድል መሆኑን ጠቅሰው የዚህ ታሪካዊ ስፍራ የታሪክ ተካፍይ መሆንን እንደ እድል በመቁጠር ልዩ ኃይሉ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጀግንነት በላቀ መልኩ ግዳጃቸውን እንደሚፉፅሙ ያላቸውን መተማመን ገልፀዋል ፡፡

የሰራዊት አባላትና አመራሮችም ማንኛውንም ግዳጅ ለመፈፀምና ለኢትዮጵያ ህዝቦች ጥቅም መረጋገጥ እስከ ህይወት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን ከሀገር መከላከያ ሠራዊት የማህበራዊ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here