አማራጭ ወደቦችን መጠቀም ለቀጣናዊ ትስስር መጠናከር ይጠቅማል ተባለ

0
1153

በጎረቤት አገራት ያሉ አማራጭ ወደቦችን የመጠቀም ዕድሎቿን ኢትዮጵያ ማስፋቷ ኢኮኖሚውን ከመደገፉም ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን ለመጠቀም ያሏትን ዕድሎች የማስፋት ተግባራት እያከናወነች እንደሆነም ነው የተገለጸው።
በወጪና ገቢ ንግድ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ወደብ በተጨማሪ የታጁራ፣ በርበራና ፖርት ሱዳን ወደቦችን እየተጠቀመች እንደምትገኝም ታውቋል።
እያደገ የመጣውን የገቢና ወጪ ንግድ መሸከም የሚያስችል ተጨማሪ ወደብ መጠቀም እንደሚያስፈልግ የተጠቆመ ሲሆን፣ የላሙ ወደብን ለመጠቀም ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ እንደሆነ ተነግሯል።
አማራጭ ወደቦችን በመጠቀም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የማስፋት ዕድል የሚፈጥር መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ ወጪን በመቀነስም ለልማት ማዋል የሚቻልበትን ሁኔታ እንደሚያመቻችም ታምኖበታል።
ለአብነትም በዚህ ዓመት በታጁራ ወደብ ብቻ ከ700 ሺሕ ቶን በላይ የድንጋይ ከሰልና ከ200 ሺሕ ቶን በላይ ካርጎ መግባት በመቻሉ በጅቡቲ ወደብ ላይ ይወሰድ የነበረውን ጊዜ እንዳሳጠረ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ወደብ ካላቸው አገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት አብሮ ለመልማትና የሕዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ሰፊ ዕድል የሚፈጥር መሆኑም ታውቋል።
ከወደብ አገልግሎቱ በተጨማሪ የመሰረተ ልማት ሥራዎችና መንገዶች ወደሌሎች የቀጣናው አገሮች መሸጋገሪያ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ይበልጥ የሚጠናከርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሰራ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here