ስለአባት ማናዬ ይባላሉ። ስለምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ሁናቴ በርካታ ጥናቶችን በማካሄድ የተለያዩ መጻሕፍትንና ጥናታዊ ጽሁፎችን አቅርበዋል። ላለፉት ስምንት ዓመታት በጋዜጠኝነት ሙያ እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆን፣ አባይን እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድና የመካከለኛው ምስራቅ የዐረብ አገራት መንግስታትን በተመለከተ ጠለቅ ያለ ዕውቀት አላቸው። ከአዲስ ማለዳው ቢንያም ዓሊ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያን የከበቧት አገራት ያላቸውን አመለካከት አሁን ካለው ፖለቲካዊ ግንኙነት አኳያ እየመዘኑ ሐሳባቸውን ነግረውናል።
አሁን በአባይ ምክንያት እየተቀየረ ያለውን የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል?
የምስራቅ አፍሪካን ፖለቲካ በተመለከተ ከ2011 የዐረቦች አብዮት በኋላ ትልልቅ ለውጦች መጥተዋል። መሐመድ ቡአዚዝ ራሱን ማጥፋቱን ተከትሎ የነበረው እንቅስቃሴ የመካከለኛው ምስራቅና የሰሜን አፍሪካ አገራት ከዛ በፊት የነበራቸውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲቀይሩ አድርጓቸዋል። ወደ ውስጥ ይመለከቱ የነበሩትን ወደ ውጭም እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል። እንደዘውድ ስርዓት ዕድሜያቸውን ለማራዘም አበክረው ይሠሩ የነበሩትን እንደ መሐመድ ጋዳፊን የመሳሰሉ መሪዎችን አብዮቱ አስወግዷል። ቱኒዝያ ጀምሮ ሊቢያ፣ ግብጽ፣ ሶሪያና የመንን አዳርሶ ብዙ ውድመት ያስከተለ ለውጥ ነበር። ሌሎች አገራትንም አናግቶ የተወሰነ ቢሆንም ለውጥ ያስከተለ አብዮት ነበር። ኳታርን የመሳሰሉ አገራት ደግሞ የውጭ ፖሊሲያቸውን በመቀየር አብዮቱ እንዳይዛመትባቸው ያደረጉ የዐረብ አገራት ናቸው።
በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውን ለውጥ አገራቱ እንደአተያያቸው የተለያየ ትርጓሜ ቢሰጡትም፣ ለእኛ ግን ምዕራባውያን አዲስ የፖለቲካ ካርድ የመዘዙበት ወቅት እንደሆነ እንገነዘባለን። የምዕራባውያኑ እጅ ቢኖርበትም ሕዝቡ የኑሮ ውድነት ብሎ ነበር የተነሳው። መንግሥታቱ ከነዳጅ ገቢ የተላቀቀ ኢኮኖሚ ለመፍጠርና የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ባለመቻላቸው አብዮቱ ፈንድቶባቸዋል። የተቀሩት የምግብ ፍላጎታቸውን ከደቡብ አሜሪካና ከእስያ ይሸፍኑ ስለነበር፣ ተመርኩዘውባቸው የነበሩት አገራት በውስጥ ጉዳያቸው ሲወጠሩ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ትኩረታቸውን ወደ ምስራቅ አፍሪካ ለማዞር ተገደው ነበር።
ከ2013 እና 2014 ጀምሮ በርካታ የዐረብ መንግሥታት ወደአፍሪካ ቀንድ መጥተዋል። ሶማሊ ላንድን እንኳን ብናይ የተባበሩት ኢሚሬቶች፣ ኳታርና ሳዑዲ አረቢያ ትኩረት አድርገው ገብተውባታል። ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲና ሱማሊያ ላይ በርካታ የአረብ መንግሥታት እጃቸውን ሰደዋል። በወደብና የጦር ሰፈር በመመስረት ይዞታቸውን አጠናክረዋል። የኢኮኖሚ ትስስራቸውን ሲያጠናክሩ የተወሰኑ የሚባሉ የባህረ ሰላጤው አገራት ሱዳንና ግብጽ ላይ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ መዋዕለ-ንዋያቸውን አፍሰዋል። በአባይ ወንዝ ላይ መሠረታቸውን አድርገው አሁንም ድረስ በአገራቱ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።
2014 እና 2015 ላይ ራሺያ እጇን በማስገባቷ የሶሪያ ፖለቲካ አዲስ ቅርጽ እየያዘ ሲመጣ ነገሮች ተቀያይረዋል። የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ የተዋቀረው በእንግሊዝና ፈረንሳይ ስለነበር ለራሳቸው እንዲመቻቸው አድርገው የከፋፈሉት አካባቢ ሌሎች ተዋንያን ሲገቡበት ሊቀያየር ችሏል። ቻይናም በ2016 የቻይና ወረቀት በመባል የሚታወቅ የውጭ ፖሊሲዋን የሚገልጽ አውጥታ ነበር። ዐረቦችን የተመለከተ ፖሊሲን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ያወጣችው። በመካከለኛው ምስራቅ ላይ የቻይና ፍላጎት ምን መምሰል እንዳለበት የሚያመላክተው ይህ ወረቀት በአካባቢው ላይ የሚኖራትን ተሳትፎ ያመላከተ ነበር።
አሸባሪው አይ ኤስ እየተስፋፋ በነበረበት ወቅት መካከለኛው ምስራቅ ላይ የተለያዩ መንግሥታት ፍላጎት እያሳደሩ መጥተዋል። ቡድኑን ለማጥፋት ራሺያና አሜሪካ ጭምር የተስማሙበት አጋጣሚ ነበር። የተለያዩ አገራት የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረትን አስታከው ፊታቸውን ወደ ምስራቅ አፍሪካ በማዞር በርካታ የጦር ሠፈሮችን መስርተዋል። ለምሳሌ ጅቡቲን ብናነሳ የተለያዩ አገራት ቦታን እየተኮናተሩ የጦር ሰፈራቸውን መስርተውባታል። ይህ የሆነው የባሕር ላይ ውንብድናና ሽፍትነት የገነነበት ወቅት ስለነበር ነው። የኢትዮጵያ አብዛኛው የውጭ ንግድ የተመሰረተው ጅቡቲ መስመር ላይ ስለሆነ፣ ሌሎች አማራጮችም እንደጅቡቲ ወደብ አዋጭ ስላልነበሩ እኛንም ይመለከተን ነበር።
በጅቡቲ ከ2009 በፊት የአሜሪካና የፈረንሳይ የጦር ሠፈር ብቻ ነበር የነበረው። ከዛ ጊዜ ወዲህ ግን የባሕር ዘራፊዎች መብዛታቸውን ተከትሎ ቻይና ጭምር ውል ተዋውላ የጦር ሰፈር አቋቁማለች። የመርከብ የዋስትና ዋጋ መወደዱ የዓለም ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ በማሳደሩ የተለያዩ አገራት በጋራ ለመሥራት ተስማምተው ነበር። ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ በባብኤል መንደብ ስለሚተላለፍ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ነበር። የመን የቀይ ባሕርን ተከትሎ ባለው ባብኤል መተላለፊያ ወሳኝ ቦታን የያዘች ቢሆንም በአገሪቱ ያለው አለመረጋጋት እሷ ተመራጭ እንዳትሆን አድርጓታል። በዚህ ምክንያት ጅቡቲ ላይ ከግማሽ ደርዘን በላይ የሚሆኑ አገራት የጦር ሰፈር አቋቁመዋል።
ሱማሊያ ላይ ቱርክ የመጀመሪያዋን ከግዛቷ ውጭ ያለ የጦር ሰፈርን አቋቁማለች። የጦር ሰፈር መገንባት ብቻ ሳይሆን የሞቃዲሾ ትልቁን ወደብ የምታስተዳድረው እሷ ናት። ኳታር፣ የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶችና ሳዑዲ አረቢያ ፑንት ላንድና ሶማሊ ላንድ ውስጥ ገብተዋል። የጦር ሰፈርና የወደብ ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ነው። በተለይ የኢምሬቶች ኩባንያ በምስራቅ አፍሪካ በወደብ ማስፋፈትና ግንባታ ዘርፍ ቀዳሚ ሆኗል።
የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከ40 ዓመት በኋላ ዳግም የቀዝቃዛው ጦርነት ያረበበበት ቀጠና እየሆነ ነው። አሁን አሜሪካ መራሹ የምዕራባውያን ኃይል የቻይናን ተፅዕኖ ከአፍሪካ ለመግታት የመረጡት ይህን አካባቢ ነው። በፊት የኃያላን መግቢያ ሰሜን አፍሪካ የነበረ ቢሆንም አሁን ምስራቅ አፍሪካ ሆኗል። ከምስራቅ አፍሪካ አገራት በሕዝብ ብዛቷና በአቀማመጧ እንደመልህቅ የሚያዩዋት ኢትዮጵያን ስለሆነ ለአካባቢው ሰላም መስፈን አስፈላጊ አድርገው ያዩዋታል። ምዕራባውያኑ እንዳሉ ሆነው ራሺያ፣ ቻይናና ዐረብ አገራት መጥተዋል። የዐረቦቹን ለየት የሚያደርገው እርስ በርሳቸው የሚጠላሉና የማይስማሙ አገራት ትኩረት ማድረጋቸው ነው። በ2017 ኳታር ላይ ማዕቀብ ሲጣል የአፍሪካ ቀንድ አገራት ከማን ጎን እንደሚሰለፉ ግራ ገብቷቸው ነበር። ኢትዮጵያ ገለልተኛ ነኝ ብላ የነበረ ቢሆንም አስቸጋሪ ወቅት ነበር። ከኳታር የወገነችው ቱርክ ብቻ ነበረች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የባሕረ ሰላጤው አገራት ከፍተኛ የሆነ የጦር መሳሪያ ከምዕራባውያኑ እየሸመቱ ነው። አንድ የስቶኮልም ዓለም ዐቀፍ ተቋም ባጠናው መሰረት፣ በከፍተኛ መጠን የታጠቁ የዓለማችን አገሮች ከሕዝብ ብዛታቸውና ከአመታዊ የምርት መጠናቸው አንጻር ሲገመገሙ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት በቀዳሚነት ታጥቀዋል፤ ከፍተኛ በጀትም ለጦራቸው መድበዋል። አያድርሰውና እርስበርሳቸው እንኳን ቢጣሉ ጦር መሳሪያው የት እንደሚደርስ ይታወቃል።
ቱርክ የሱዳኗን ሱዋኪ ደሴትን ለማልማት ከአገሪቱ መንግሥት ጋር መስማማቷን ተከትሎ፣ ግብጽና ሳዑዲ አረቢያ ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር። ቱርክ ሊቢያ ውስጥ መግባቷም ግብጽን አስቆጥቷት ነበር። ኹለቱ አገራት ለዘመናት የቆየ ቁርሾ ነው ያላቸው። አፍሪካ ቀንድ ላይ እየመጡ ያሉት እንደነዚህ አይነት አመለካከት ያላቸው አገሮች ናቸው። አሜሪካ አፍሪካ ውስጥ ያሉኝን ጥቅሞች ለማስጠበቅ ኹለት ቀጠናዎች ወሳኝ ናቸው ብላ በአፍሪኮም ዋና አዛዥ በኩል አስነግራለች። ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ሱዳን ናቸው። እነዚህ ቀጠናዎች ለምን ተፈለጉ ብለን መመርመር ያስፈልገናል። ኢትዮጵያ በኹለቱ አገራት መካከል በአቅራቢያ እንደመገኘቷ ሊያሳስበን ይገባል።
ምዕራባውያንና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ለኢትዮጵያ ያላቸው አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀያየሩን እንዴት ይመለከቱታል?
የአረብ አገራት አካሄድ መስመርን መለየት ያለብን ይመስለኛል። እነሱ በዓባይ ፖለቲካ ምንግዜም ከግብጽ ጋር ናቸው። ከግብጽ ጋር ከተጣሉ ብቻ ነው ከኢትዮጵያ ጎን የሚሆኑት። ከሙስሊም ወንድማማቾች ጋር በተገናኘ ከግብጽ ጋር በተጣሉበት ወቅት የባሕረ ሰላጤው አገራት ለግድቡ እንርዳችሁ እስከማለት ደርሰው ነበር። ከዚህ በስተቀር የአረቡ ዓለም ቀንዲል አድርገው ስለሚመለከቷት ሁሌም ከጎኗ ናቸው። የአረብ ሊግም ግብጽን በተደጋጋሚ የሚደግፈው በዚሁ ምክንያት ነው።
በሌላ በኩል፣ ከፖለቲካና ኢኮኖሚ ትስስር አኳያ ካየነው ይለያል። ለምሳሌ የተባበሩት አረብ ኢምሬት የውጭ ፖሊሲ የተቀረጸው ከንግድ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ አኳያ ነው። እንደነሳዑዲና ኳታር ለኃይማኖት ቅድሚያ ስለማትሰጥ የተለያዩ ቦታዎች ለመግባት ችላለች። ዓላማችን ከአፍሪካ ቀንድ ጋር በኢንቨስትመንት መተሳሰር ነው ብለው በግልጽ አስቀምጠውታል። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያን ገፏት ወይስ አፈገፈጉ የሚለውን ለመገምገም ጊዜው ገና ነው።
ምዕራብ ዘመሙ ግንኙነትን በተመለከተ ከራሺያና ቻይና ጋር ግንኙነታችን በመጠናከሩ የመጣ ለውጥ አለ። ምዕራባውያኑ አፍሪካን የመቀራመት አዝማሚያ እያሳዩ ነው። ላለፉት አራት አመታት ዶናልድ ትራንፕ አፍሪካን ረስቶ ነበር። የተሳደቡትን ትተን የመጀመሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው እዚህ አፍሪካ መጥተው ሲመለሱ ለማባረር ምድር እስኪረግጡ እንኳን አልጠበቋቸውም ነበር። የአፍሪካን ፍላጎት ለመስማት ዝግጁ አልነበሩም። ፕሬዝዳንት ባይደን ደግሞ ወደሥልጣን እንደመጡ አሜሪካ የዓለም ስርዓትን ወደማስጠበቅ ቦታዋ እየተመለሰች ነው የሚል ልዕለ ኃያልነቷን ለማስገንዘብ ሞክረው ነበር። አፍሪካ ላይ ያሉበትን ሲያዩ በብዙ ነገር መበለጣቸውን አውቀዋል።
የኮሮና ቫይረስ ከመሰራጨቱ በፊት በ2019 የአፍሪካና የአሜሪካ የንግድ ግንኙነት እስከ 90 ቢሊዮን ዶላር ይደርስ ነበር። ባለፉት 10 አመታት እየጨመረ የመጣው የቻይናና የአፍሪካ ግንኙነት ደግሞ 220 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር። ልዩነቱ በከፍተኛ ደረጃ ስለጨመረ አሜሪካንን አሳስቧታል። እሷ ሰላምና ልማት ላይ ብታተኩርም፣ በተለያየ መስክ ቻይና እየበለጠቻት ነው። ራሺያም ብትሆን ለሰላማዊ የኃይል ማመንጫነት በሚል ከበርካታ የአፍሪካ አገራት ጋር የኑዩክሌር ስምምነት አድርጋለች። ይህ አሜሪካውያኑን ግራ እያጋባ ነው። ከኢትዮጵያም ጋር ተመሳሳይ ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።
ምዕራባውያኑን ይበልጥ የሚያሳስባቸው ‹የአንድ ቀበቶ የአንድ መንገድ ፕሮጀክት› ነው። የአፍሪካ መግቢያው የአፍሪካ ቀንድ ስለሆነ ነው በጣም ያስጨነቃቸው። ኢትዮጵያ ዋና መግቢያ ትሆናለች ብለው ከጎናቸው ለማድረግና ተፅዕኗቸውን በማሳረፍ የቻይናን እንቅስቃሴ ለመግታት ይፈልጋሉ። ይህን ዓላማቸውን የሚያስፈጽም መንግሥት ይፈልጋሉ። ይህ ነው ኒዎ ኮሎናይዜሽን በመባል የሚታወቀው አዲሱ ቅኝ አገዛዝ። ለእነሱ ተንበርካኪ መንግሥታትን አሁንም መፍጠር እንደሚፈልጉ አዝማሚያው እየታየ ነው። ይህ ለመሆኑ በሆነ ባልሆነው የሚያሳርፉት ተፅዕኖ አመላካች ነው።
እስራኤል በአፍሪካ ካላት ፍላጎትና ከዓባይ ወንዝ ከምታገኘው ጥቅም አኳያ ውግንናዋ ወዴት ይሆናል ይላሉ?
ከውኃ ፖለቲካ አኳያ የእስራኤልን አቋም ካየነው ብዙ ጥናትና ምርምር ያስፈልገዋል። ከዚህ አኳያ ብዙ ያልተዘጉ ዶሴዎች አሉ። የእስራኤል አገር ጠንሳሽ ቴዎድሮስ ሄንዝ ራሱ የዓባይን ወንዝ ጠልፎ በመውሰድ በረሃውን ማልማት እንደሚያስፈልግ ሐሳብ ነበረው። የአረብ መንግሥታት ስውር እጅ በሚለው መጽሐፌ ላይ እንደጠቀስኩት የፍልስጤም ስደተኞችን በተመለከተ፣ አንዲሁም የዓባይ ወንዝን ወደ ጋዛ ጠልፈው በመውሰድ ለመጠቀም ማሰባቸው ተጠቅሶ ነበር። በሲናይ በረሃም ፍልስጤሞችን ለማስፈር በእስራኤል በኩል ከኔጌብ በረሃ ቦታ ለመስጠት የሚሉ ሃሳቦች ነበሩ። ይህ ከግብጽ መሪዎች ጋር የመከሩበት ጉዳይ ያልተዘጋ አንዱ ዶሴ ነው።
በሌላ በኩል የእስራኤሉ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታናይሁ በአፍሪካ ላይ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥ አምጥተዋል። እስልምና ከሚከተሉም ሆኑ ከሌሎች አገራት ጋር ወዳጅነት መስርተዋል። የኢትዮጵያና እስራኤል ወዳጅነት ጥሩ ደረጃ ላይ ለመሆኑ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይመስለኝም።
ከምዕራቡ ዓለምና ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር ያለን ግንኙነት እየቀነሰ መጥቷል መባሉን እንዴት ያዩታል?
ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ ያላቸው ፍላጎት እየቀነሰ አልመጣም። ነገር ግን ዳግም የቅኝ ግዛት መንፈስ እያቆጠቆጠባቸው ነው። ይህን ፍላጎታቸውን የሚያረጋግጥ ተግባራቸው እኛ አገር ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በርካታ አገሮች ላይም በግልጽ እየታየ ነው። ድሮ የሰው ኃይል ነበር የሚፈልጉት። አሁን አፍሪካዊ ተሰቃይቶም ስለሚሄድላቸው የሚፈልጉት ጥሬ ዕቃን ብቻ ነው። ለምሳሌ ማሊን ብንወስድ ችግር ላይ የወደቀችው በግዛቷ ያለውን ዩራኒየም ስለሚፈልጉት ነው። የቤት ሥራችን መሆን ያለበት እየመጣብን ያለውን ለመመከት ሁሌም ዝግጁ መሆን ነው።
እኔ ባካሄድኳቸው ጥናቶች ኢትዮጵያ ላይ በታሪኳ የውጭ ጫና የሚበዛባት ውስጧ ሲከፋፈል ነው። ውስጣዊ አንድነቷ መፍረክረክ አጋጥሞታል ብለው ሲያስቡ ነው የሚጠነክሩብን። አንድ ናቸው ብለው ሲያስቡ አይሞክሩም።
የዓባይ ግድብን በተመለከተ ድርድር እንድናደርግ የሚፈልጉት እነሱ እንደመሆናቸው ለምንድን ነው የምንስማማው? ስምምነት ላይ መድረሱስ የግድ አስፈላጊ ነው?
ኢትዮጵያ ለምን ወደ ድርድር ውስጥ ገባች የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። በታሪካችን የተናጥል አካሄድ ተከትለን አናውቅም። ልዩነቶች በድርድር መፈታት እንዳለባቸው ኢትዮጵያ ታምናለች። የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶችን እንደመቀበሏ ለሕጎቹ ተገዢ ናት። ያንን የማስቀጠል መርህ ነው የምትከተለው። ዓባይ እንደሌሎች 260 በላይ እንደሚሆኑ ወንዞች ድንበር ተሸጋሪ ነው። ኢትዮጵያ ካላት የዲፕሎማሲ አቋም አኳያ ከወንዞቿ ለመጠቀም ስምምነት ቢኖር ትመርጣለች። ዓለም ዐቀፍ መርሆዎችን ተከትላ ለድርድር መቀመጧ ችግር የለውም። ዋናው ጉዳይ ባለፈው 10 አመት በተደረገው ድርድር ነጥብ ጥላለች ወይ የሚለው ነው። እስካሁን ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፎ የሚሰጥ ስምምነት አልተደረገም። ይልቁንም በ2015 ካርቱም ላይ እንደተስማማችው የሚጠቅማትን ለማግኘት ችላለች።
ሌሎች አገሮች በወንዞቻቸው ላይ ግንባታን ሲያካሂዱ ይህ አይነት ስምምነት እንዲደርሱ ካለመጠየቁ አኳያ የእኛን ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?
ጠንካራ አቅም ካለ እንኳን መደራደር እንደራደር የሚል አይኖርም። ለምሳሌ፣ አሜሪካ ኮሎራዶ ወንዝ ላይ ግድብ ስትገነባ የተከተለችው መርህ፣ ማንም በወንዜ የፈለኩትን ባደርግ አያገባውም የሚል ነበር። ነውጠኛ የውኃ ቀኖና የሚባለው ይህ ነው። ቻይናም ብትሆን አቅም ስላላት የፈለገችውን ስታደርግ የሚናገራት የለም። እኛ እንደዛ እንዳንል ከግድቡ ውጭ በውጭ ድጋፍ የምናከናውናቸው ሌሎች የልማት ሥራዎች ስላሉ ነው። በሌላ በኩል ጉልህ የሆነ ጉዳት ግድቡ እንደማያስከትል የምንናገረውን ለዲፕሎማሲው ማሕበረሰብ ማሳየት እንችላለን።
ድርድሩ እንደፍላጎታችን ወደ አፍሪካ ሕብረት ቢመለስም፣ ሕብረቱ ከምዕራባውያን ተፅዕኖ ውጭ ነው ማለት ይቻላል?
በሕብረቱ ያለው አቋም ስለሚታወቅ ይመስለኛል ጉዳዩ እንዲመለስ ሲጣር የነበረው። ድርድር ሲባል ኹለት ውጤቶች ይኖሩታል። ተስማምቶ መውጣት ወይም አለመስማማትን አውቆ መውጣትም ይቻላል። በአፍሪካ ሕብረትም ቢሆን ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚጎዳ ከሆነ ልዑካኑ አይስማሙም። ስምምነት መድረስ ግዴታ አይደለም።
ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013



