የፌደራል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አግልግሎት በተጠናቀቀው 2013 የበጀት ዓመት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ንብረት በማስወገድ 63 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ።
የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በ2013 በጀት ዓመት የ74 መሥሪያ ቤቶች 144 ተሽከርካሪዎች እና የ40 መሥሪያ ቤቶች 628 ያገለገሉ ንብረቶችንና መለዋወጫዎችን እንዲሁም፣ አልሙኒየምና ስቲል ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን በሽያጭ በማስወገድ 63 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
አገልግሎቱ በ2012 በጀት ዓመት ከንብረት ማስወገድ 51 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት የሰበሰበው ገቢ ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ16 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል። መሥሪያ ቤቱ በ2012 በጀት ዓመት የ46 መሥሪያ ቤቶች 110 ተሸከርካሬዎችን፣ የ25 መሥሪያ ቤቶች 774 ንብረቶችን እንዲሁም የተለያዩ ቁርጥራጭ ብረታብረቶችን በሽያጭ በማስወገድ 51 ሚሊዮን ብር ለመንግስት ገቢ ማድረጉን የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጎጃም ታደለ አስታውሰዋል።
በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ በአሁኑ ወቅት ተከማችተው የሚገኙ የመንግሥት ንብረቶች በነጠላ ከአንድ ሺሕ ብር በላይ ለሚሆኑ እንዲሁም ከአጠቃላይ ንብረቶቹ ከ 100 ሺሕ ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ የሚያስገኙ የመንግሥት ንብረቶች ለግዢና ንብረት ማሰወገድ ገቢ ይሆን እንደነበር አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።
አዲስ በወጣው የንብረት ማስወገድ መመሪያ መሰረት ግምታቸው ከአምስት ሺሕ ብር በላይ በነጠላ ዋጋ እንዲሁም በጥቅል ከ 5 መቶ ሺህ ብር በላይ ከሆነ ለግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ገቢ መደረግ ይኖርበታል። ይህንም መስፈርት አሟልተው የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ንብረታቸውን ማስወገድ እንደሚችል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አስታውቋል።
በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ላይ የሚገኙ በነጠላ ከአምስት ሺሕ ብር በታች የሚያወጡ፣ እንዲሁም በጥቅል ከ 5 መቶ ሺሕ ብር በታች የሚያወጡ ንብረቶችን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በራሳቸው መንገድ ንብረቶቹን ማስወገድ የሚችሉበት አዲስ መመርያ መውጣቱ ታውቋል።
በዚህም መሥሪያ ቤቶቹ ንብረት የማስወገድ መብት ስለሚኖራቸው ወደ መንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አይልኩም።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ወደ አገልግሎቱ የሚልኩት የሚወገድ የንበረት መጠን የሚቀንስ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በ2013 በጀት ዓመት የተለያዩ ግዥዎችን በመፈጸም 47 ለሚሆኑ አቅራቢ ድርጅቶች የ10.6 ቢሊዮን ብር የአሸናፊነት ደብዳቤ ሰጥቷል።
በማዕቀፍ ስምምነት እና ስትራቴጂክ ግዥ የፌደራል መሥሪያ ቤቶች እና የመንግሥት ዩንቨርስቲዎች የሚጠቀሙባቸውን ተመሳሳይ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ግዥ ለመፈጸም ባቀደው መሰረት የደንብ ልብስ፣ የጽሕፈት መሳሪያዎች፣ የተሸከርካሪ ጎማ፣ የጽዳት ዕቃዎች፣ የፕሪንተርና ፎቶ ኮፒ ማሽን ቀለሞች፣ የኮቪድ19 መከላከያ ቁሳቁስ፣ የላፕቶፕ እና የአይሲቲ መሳሪያዎች፣ የተሽከርካሪዎች የመድን ዋስትና (የ342 ተሸከርካሪዎች)፣ የስንዴ ግዥ በድምሩ ለ47 አቅራቢ ድርጅቶች በብር 10.6 ቢሊዮን ብር ግዥ ፈጽሟል።
በ2013 በጀት ዓመት የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ላይ የሚገኙ ንብረቶችን የማስወገድ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ኮቪድ-19 ከፍተኛ ተጽኖ ማሳደሩን አገልግሎቱ ጠቁሟል።
ለቫይረሱ ተጋላጭ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች መካከል አንዱ፣ ብዙ ሰው በሚገኝበት ስፍራዎች ላይ መገኘት ተጠቃሽ በመሆኑ ጨረታ በሚደረግበት ወቅት አነስተኛ ጥር ያላቸው ሰዎችን ለማሳተፍ ተገደዋል። በዚህም ምክንያት ጨረታዎች በተደጋጋሚ በመራዘማቸው ዕቅዱን በታሰበው መልኩ ማሳካት አልተቻለም ተብሏል።
ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013


