የህወሓት ቡድንን ሀገር የማፈራረስ ሴራን የሚያወግዝ እና የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
ከተማዋ ነዋሪዎች “የአብሮነት ጉዟችን በሽብርተኞች አይደናቀፍም”፣ “እኛ ጋምቤላዎች ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን ነን”፣ “ሰላማችን በአንድነታችን ይጠበቃል”፣ “ክብርና ሞገስ ውድ ህይወታቸውን ለሰጡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት”፣ “ኢትዮጵያ በጀግኖቿ አፍራ አታውቅም” የሚሉ መፈክሮች በመያዝ ሰልፉን እያከናወኑ እንደሚገኙም ታውቋል።
በተጨማሪም “አገር በጁንታው ሴራ አትፈርስም”፤ “የህልውናችን መሠረት የሆነው የህዳሴ ግድባችንን እስከመጨረሻው በመደገፍ ከዳር እናደርሳለን”፣ “ጁንታው የኢትዮጵያ ነቀርሳ ነው” የሚሉ እና በርካታ መፈክሮች በጋራ በማሰማት ላይ እንደሚገኙ ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ሠራዊቱን በሚደግፈውና በመንግስት በአሸባሪነት የተፈረጀውን የህወሓት ቡድን በሚያወግዘው ሰልፍ ላይ በርካታ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውም ታውቋል፡፡






