አቶ ደመቀ መኮንን በተባበሩት መንግስታት የፖለቲካ እና ሰላም ግንባታ ምክትል ዋና ፀኃፊ ጋር ተወያዩ

0
888

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በተባበሩት መንግስታት የፖለቲካ እና ሰላም ግንባታ ምክትል ዋና ፀኃፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ ጋር በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

በውይይታቸው መንግስት የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ያወጀው በትግራይ ክልል የሚገኙ አርሶአደሮች የክረምቱን ወቅት እንዲጠቀም ለመርዳት ቢሆንም ሰሚ እንዳላገኘ አቶ ደመቀ አስረድተዋል።

ምንም እንኳን የሕወሃት ቡድን ለመንግስት በጎ ተግባር አክብሮት እንደሌለው በመግለፅ በእኩይ ምግባሩ ቢቀጥልም አሁንም የኢትዮጵያ መንግስት ለተኩስ አቁም ቁርጠኛ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው ገልፀዋል።

ሚኒስተሩ ቡድኑ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ መስመር ላይ ያሉ ሰብአዊ እርዳታ መተላለፊያ መንገዶችን ለመዝጋት መሞከሩንና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ተስፋ ለማስቆረጥ እየተሯሯጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሮዝመሪ ዲካርሎ በበኩላቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  የተኩስ አቁሙን እንደሚያደንቅና እንደሚደግፍ ገልጸው ሁሉም ወገን ተመሳሳይ ሁኔታን እንዲከተል ያስፈልጋል ብለዋል።

የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ አቶ ደመቀ ጉዳዩን አላስፈላጊ ፖለቲካዊ መልክ ማስያዝ የድርድር ሂደቱን ከመጎተት በቀር ምንም ጥቅም እንደሌለው ገልፀዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው ሂደት ለሁሉም ተደራዳሪ ወገኖች የእርቀ ሰላም መፍትሄ ለማምጣት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በግልፅ ሁኔታ ሰላማዊ ሆኖ የተከናወነ በመሆኑ በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት መንገዱን አመቻችቷል ብለዋል።

በኢትዮጵያ እና በሱዳን የድንበር ግጭት ዙሪያ ባደረጉት ውይይት የሱዳን መንግስት በሕገ-ወጥ መንገድ የኢትዮጵያን ግዛቶች መያዙ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተስፋ እንዲቆርጥ ለማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዋና ፀሃፊዋም ኢትዮጵያ የቀጠናው ምሰሶ በመሆኗ መረጋጋቷ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ ሰላማዊ መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here