የውጪ ሀገር ካምፓኒዎች የኢትዮጵያን የቡና ስያሜዎች ለመከራየት ጥያቄ እንዳቀረቡ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ገለፀ፡፡
የኢትዮጵያን የቡና ስያሜዎች ለመከራየት ጥያቄ ያቀረቡት የቻይና እና የካናዳ ካምፓኒዎች እንደሆኑም ተነግሯል፡፡
ባለፉት አምስት አመታት ኢትዮጵያ የቡና ስያሜዎቿን በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስጠበቅ ከ30 በላይ ከሚሆኑ ሀገራት ጋር የውል ስምምነት ማድረጓ ይታወቃል፡፡
አሁን የውል ስምምነቱ በመጠናቀቁ የተለያዩ ሀገራት የቡና ስያሜዎቹን ለመከራየት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አሳውቋል፡፡
የሀረር ፣የይርጋጨፌና የሲዳሞ ቡና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘችባቸው የሀገራችን የቡና ስያሜዎች ሲሆኑ ከ 30 በላይ በሚሆኑ ሀገራት በንግድ ምልክትነት መመዝገባቸውና የስያሜዎቹ ህጋዊ መብት እንዲጠበቅ መደረጉን ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያ ቡናውን ወደ ውጭ ስትልክ የውል ስምምነቱን ለፈረሙት ብቻ መሸጥ ሲኖርባት የውል ፈራሚዎች ጥምረቱ እንዳይጠናከር በሚያደረግ መልኩ ቡና መግዛት ለሚመጣ ሁሉ እየሸጠች ነው፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ የአምራዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ኢትዮጵያ በራሳ እጅ ውሉን ማፍረሷን አሳውቋል፡፡
በዚህም ምክንያት አለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያን የቡና ስሞች ለመከራየት ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡ ሁለቱ የቻይናና የካናዳ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የቡና ስያሜዎች በየአምስት አመቱ በሚታደስ ውል መሰረት ለመከራየት ጥያቄ ማቅረባቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም ዘግቧል፡፡


