መኮንን አንዳርጋቸው ይባላሉ። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፣ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ናቸው። ባለቤታቸው የቤት እመቤት ስለሆኑ ብቻቸውን ለመሥራት መገደዳቸውን ይናገራሉ።
በወቅቱ ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን ብዙም ሊገፉበት እንዳልቻሉ የሚናገሩት መኮንን፣ የግምበኝነትን ሙያ በልምድ አዳብረው የብዙ አመት የሥራ ልምድ እንዳላቸው ያነሳሉ።
መኮንን ከ1992 ዓም ጀምሮ ወደ ተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እንዲሁም ገጠራማ ቦታዎች ድረስ በመሄድ በቅርጻ ቅርጽ፣ በኮንስትራክሽን ግንባታ፣ድንጋይ በመጥረብ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት እንደቻሉ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።
በቤተክርስቲያን፣ በንግድ እንዲሁም በመኖሪያ ቤቶች ላይ የሥራ አገልግሎት ይሰጡ አንደነበር ጠቅሰዋል። በሰው እጅ ይሠራ የነበረው የቅርጻ ቅርጽ ሥራ ባሁኑ ወቅት በማሽን በመሠራቱ፣ የሰው ኃይል የማያስፈልግበት ሁኔታ መደረሱን ይጠቁማሉ። እኛ በእጃችን እንሠራው የነበረውን ስራ ድርጅቶች ቴክኖሎጂን በመጠቀም በማሽን መሥራት ጀምረዋል ብለዋል።
የቀን ሥራ የሚያገኙት ከዚ በፊት ከሠሩላቸው ሰዎች፣ ለሚያውቋቸው ሰዎች ስልክ በመስጠት፣ በትውውቅ እንዲሁም በኮንትራክተሮች አማካይኝት በቅጥር እንደሆነ ያስረዳሉ።
ከወር አሰከ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ሥራ ሊያጡ የሚችሉበት ሁኔታ ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል። የእሳቸው ሥራ ማግኘትና ማጣት ኮንትራክተሮቹ በሚያገኙት የሥራ ዕድል ላይ የተመሰረተ መሆኑን መኮንን ያነሳሉ።
የቀን ሥራ ዕጦት እንደ ዋና ምክንያት የሚያነሱት መኮንን፣ መንስኤው የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች ዕጥረትና ዋጋ መናር እንደሆነ አመልክተዋል።
የሲሚንቶ እንዲሁም የብረት መወደድ ብሎም ከገበያ ላይ መጥፋትን እንደ ዋና ምክንያት ጠቅሰዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ኮንትራክተሮች የቀን ሠራተኞችን እንደማይቀጥሩ ያነሳሉ።
ብዙውን ጊዜ ኮንስትራክሽን ላይ የሚሠራ ሥራ ለሥራው በሚያስፈልጉ የግብዓት ዕጥረትና የዋጋ መናር ምክንያት የሚወሰን ነው ብለዋል።
በዚህም ምክንያት ባለሀብቶች ሕንጻዎችን ማስገንባት ያቆማሉ። እንዲሁም ምንም አይነት የሥራ እንቅስቃሴ ማድረግ የማይችሉበትን ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል። ኮንትራክተሮችም የሚቀበሉት ትዕዛዝ ስለማይኖር የቀን ሠራተኞችን መቅጠር ያቆማሉ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ለኮንስትራክሽን ግንባታ በሚውሉ መገልገያዎች ዋጋ መናር ምክንያት የተጀመሩ ሕንጻዎች በጅምር የሚቆዩበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፣ እሳቸው ይህ ሁኔታ በተደጋጋሚ አጋጥሟቸው የሚያቅ መሆኑን አስታውሰዋል።
በሕንጻዎች መቋረጥ ሒደት ምክንያት እሳቸውን ጨምሮ ብዛት ያላቸው የቀን ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው ላይ መሰናበታቸውን አንስተውዋል። በወቅቱ ከሥራ በመበተናቸው ምክንያት ብዙ ችግሮች ሊደርስባቸው እንደቻለም ተናግረዋል።
ጊዜው የክረምት ወቅት በመሆኑ ከፍተኛ ዝናብ፣ ጭቃ እንዳንዴም ጎርፎ ስለሚኖሩ የቀን ሥራ የማግኘት ዕድላችንን ያጠበዋል ሲሉም ይናገራሉ። የቀን ሥራ በሚጠፋት ወቅት ነገሮች ከአቅማቸው በላይ ስለሚሆኑ ወደ ክፍለ-አገር ለመሄድ እንደሚገደዱ ይጠቁማሉ።
እንደእሳቸው ገለጻ፣ የቀን ሥራ ማጣትን ያስከትላል ብለው የሚያስቡት የኮንስትራክሽን ግብዓት ዕጥረትና የዋጋ መናር በመሆኑ፣ ይህን ጉዳይ የሚመለከተው አካል ሁኔታውን ተመልክቶ ቢያስተካል ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብዬ አምናለሁ ሲሉ አስረድተዋል።
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተገናኘ አዲስ ማለዳ ኢንጅነር ብዙአየሁ ደምሴን አነጋግራቸው ነበር። ከሥራ ድርሻቸው መካከል የባለሙያ ረዳት ወይም የቀን ሠራተኞች መቆጣጠር እንደሆነ ገልጸዋል።
እንደ አሳቸው ገለጻ በአሁኑ ወቅት ለሚስተዋለው የቀን ሠራተኞች ሥራ አጥነት ዋነኛው ምክንያት የኑሮ ውድነት መሆኑን ተናግረዋል። አሁን ላይ በአገሪቷ በጅምር የቀሩ ሕንጸዎችን ማየት የተለመደ ነው ብለዋል።
የኮንስትራክሽን ሥራ በባህሪው ብዙ ሰዎችን በማቀፍ የሥራ ዕድል ፈጥሮ ለቀን ጉርስ የሚሆን ገቢ የሚያስገኝ ነው ይላሉ።
ለኮንስትራክሽን የሚውሉ ግብዓቶች እንደ ሲሚንቶና ብረት የመሳሰሉ ላይ የአቅርቦት ችግር እንዲሁም የዋጋ ንረት መኖሩንም አንስተዋል። እነዚህ ችግሮች ቢቀረፉ ባለሀብቶች ለራሳቸው ብለው ሥራዎችን በፍጥነት ማስኬድ ስለሚችሉ፣ ብዙ የቀን ሠራተኞችን መቅጠር የሚቻልበት ሁኔታ እንደሚኖር አስረድተዋል።
የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ በቋሚነት ባለመቀጠሉ ምክንያት የሥራውን ሁኔታ ለማስቀጠል በባለድርሻ አካላት ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን፣ ይህም በሠራተኞችና አሠሪዎች ላይ ክፍተት ይፈጥራል ብለዋል።
በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ ሴቶችም የአቅማቸውን የሚሠሩበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል። በክረምት ወቅት የቀን ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞች በብዛት ተማሪዎች በመሆናቸው የሥራ አጥነቱን እንደሚያሰፋው ገልጸዋል።
እሳቸው እንደ መፍትሄ ያነሱት የኮንስትራክሽን ግባዓቶችን ዋጋ ማስተካከልና በገበያ ላይ የሚታየውን ዕጥረት መቅረፍን ነው።
ሌላኛዋ ታሪኳን ያካፈለችን ፈትያ ነስር ናት። የክፍለ0አገር ልጅ እንደሆነችና አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ መሆንዋን ትገልጻለች። ፈትያ ባለትዳርና የኹለት ልጆች እናት ስትሆን በአሁኑ ወቅት ከቀን ንግድ በሚገኝ ገቢ ኑሮዋን እየመራች እንደምትገኝ ታስረዳለች።
ሰዎች በብዛት የሚንቀሳቀሱበት ቦታ ለሥራዋ አመቺ ሁኔታ እንዳለው ታነሳለች። በዚህም ምክንያት በሕዝብ ትራንስፖርት መጠበቂያ ሥፍራዎችን ላይ ተገኝታ በቆሎ፣ ድንች፣ የተጠበሱ ብስኩቶች፣ እንዲሁም ትኩስ ነገሮች በመሸጥ ላይ እንደምትገኝ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራት ቆይታ አንስታች።
ከንግዱ የምታገኘው ገቢ ያን ያህል አዋጭ የሚባል ሁኔታ ላይ ባይሆንም፣ የዕለት ጉርስ ለመሸፈን ግን የሚያስችል ነው ስትል ጠቅሳለች። በብዛት ካርድ፣ ውኃ፣ የተጠበሱ ብስኩቶችን እንዲሁም ትኩስ ነገሮች የሚገዝዋት የትራንስፖርት ሠራተኞች፣ የሕዝብ ትራፕራንስፖርት ተጠቃሚዎች እንዲሁም የቀን ሠራተኞች እንደሆኑ ተናግራለች።
ጊዜው የክረምት ወቅት በመሆኑ ሥራው ትንሽ ሊቀዘቅዝባት እንደቻለ ታስረዳለች። እሷ እንደ ምክንያት የምታነሳው ብዙውን ግዜ በዝናብ ወቅት ሰዎች ከቤታቸው ግዴታ ካልሆነባቸው በቀር እንደማይወጡ በማንሳት ንግዱ ሊቀዘቅዝባት እንደቻለ አንስታለች።
እንደ ፈትያ አረዳድ ብዙ ሰዎች ከኮቪድ ጋር በተያያዘ እንደ ድሮው መንገድ ዳር ላይ የሚሸጡ ምግቦችን እንዲሁም ትኩስ መጠጦችን እንደልብ አይጠቀሙም ትላለች። በዚህም ምክንያት በቀን ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ይዛ ለመግባት ተዳርጋለች ።
ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገችው ሌላ የቀን ሰራተኛ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራት ቆይታ፣ በሰዎች ቤት አየተዘዋወረች ልብስ በማጠብ የምትተዳደር መሆኑን ተናግራለች። ባለትዳር እንደነበረችና ኹለት ልጆች ያሏት ስትሆን ከባለቤትዋ ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ባለመግባባታቸው ትዳራቸው ሊፈርስ እንደቻለ ጠቅሳለች። ሆኖም ግን ልጆችዋን ብቻዋን ለማሳደግ በመገደድዋ የቀን ሥራ በመሥራትና ገቢ ማግኘት ለገጠማት ችግር እንደ መፍትሄ ወስዳለች።
እንደእሷ ገለፃ የምትሰራው ሥራ ገቢው ዝቅተኛ ቢሆንም፣ በተቻላት አቅም ያገኘችውን አብቃቅታ ለወር ወጪ፣ ለልጆችዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በማሟላት እንደምትጠቀምበት ታስረዳለች።
ይህን ኹሉ የምታከናውንበት የገቢ ምንጭዋ ግን በወቅቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቁማለች። ውቅቱ ክረምት በመሆኑ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሥራ ማግኘት ቀላል አይደለም ስትል ትገልጻለች።
በክረምት ወቅት ሥራ ከሚጠፋበት ዋነኛ ምክንያት ብላ የምታነሳው፣ ተማሪዋች ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ቤተሰባቸው ስለሚመለሱ ሰዎች ሌላ ሰው መቅጠር ላይጠበቅባቸው ይችላል። በቤት ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎችን ራሳቸው ሊያከናውኑ እንደሚችሉ ትናግራለች።
ከዚህም ጋር አያይዛ አሁን ባለንበት ዘመን በብዛት ድሮ በሰው ይሠሩ የነበሩ ሥራዎቸ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በማሽን መሥራት በመጀመሩ እንደከዚህ ቀደም ሰዎች በቀላሉ የቀን ሥራ ማግኘት እጅግ ከባድ ሆኗል ትላለች። በክረምት ወቅት ከፍተኛ ዝናብ ስለሚጥል በፈለኩት ሰዓት ተንቀሳቅሼ ሥራ መፈለግ አልችልም ትላለች።
የቀን ገቢ ሊያስገኝ ከሚችሉ ሥራዎች መካከል የኮንስትራክሽን፣ የተለያዩ አልባሳትን፣ ቁሳቁሶችን በመንገዶች ላይ መሸጥ፣ የድለላ ሥራ የሚጠቀሱ ናቸው።
ከመንገድ ዳር ንግዶች መካከል በጋሪ ላይ የሚደረግ ሽያጭም ተጠቃሽ ነው። የበቆሎ ሽያጭ፣ የተለያዩ ለምግብነት የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬ ማቅረብም ይጠቀሳል።
እንደ አትክልት ያሉ የመንገድ ዳር ሽያጮች በይበልጥ ሴቶች የሚሠሩት ሥራ መሆኑን የነገሩንን ፀሐይ ግርማ ናቸው። የተለያዩ አትክልቶችን በመንገድ ዳር በመሸጥ የቀን ገቢ እንደሚያገኙ፣ በዚህም የሚያስፈልጉ የወር ወጪያቸውን እንደሚሽፍኑ እንስተዋል። የክረምት ወቅቱ ግን የቀን ገቢያቸው ላይ ጫና እንደሚያሳድር ይጠቅሳሉ።
የሥራ ቦታቸው መንገድ ዳር በመሆኑ ዝናብ ሲዘንብ መንገዱ ጭቃ ስለሚሆን የሰዎች እንቅስቃሴ ይገደባል። በዚህም ምክንያት የሚገዛቸው ሰው እንደሚያጡ ተናግረዋል።
በዚህ የሥራ መስክ የሚተዳደሩ ሰዎች የክረምት ወቅት ሥራቸውን እንደሚፈትነው ተናግረዋል። ለሽያጭ ይዘውት የወጡትን ዳግም ወደ ቤታቸው ይዘው የሚመለሱበት ሁኔታ ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።
የክረምት ወቅት ጫናው ከዚህም ባለፈ ዝናብ በሚዘንብ ጊዜ የሚጠለሉበት ቦታ ስለማይኖር ጥላ እንዲሁም ላስቲኮችን መጠቀም አልፎ አልፎ ደግሞ በሚጥለው ዝናብ መመታት ዕጣ ፈንታቸው መሆኑን ገልፅዋል።
የክረምት ወቅት በመጣ ቁጥር ብዙ የማሕበረሰባችን ክፍሎች ስጋት ላይ ይወድቃሉ። የጎርፍ አደጋ እንዲሁም ሥራ አጥነት በጥቂቱ የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ ነው። ሥራ ለመፈለግ ወይም ተንቀሳቅሶ ለመሥራት የግድ ከቤታቸው መውጣት ይጠቅባቸዋል።
የቀን ሠራተኞች የገቢያቸው ምንጭ በዕለት ላይ በመመስረቱ ሳይሠሩ ለመዋል ይቸገራሉ። አብዛኞቹ የቀን ሠራተኞች በክረምት ወቅት ከፍተኛ ኪሳራ ላይ ይወድቃሉ። መሰረታዊ ነገሮችን ለማሟላት እንዲሁም የቀን ጉርሳቸውን እንኳን ለመሸፈን አዳጋች ይሆንባቸዋል።
በክረምት ወቅት ይበልጥ ተፈላጊ የሆነው የመንገድ ዳር የጥላ ንግድ ነው። ሰዎች በበጋም ሆነ በክረምት እራሳቸውን ከፀሐይና ዝናብ ለመከላከል ጥላ ይጠቀማሉ። የጥላ ሽያጭ በክረምት ወቅት ግን በይበልጥ ገቢ ያስገኛል።
የዘንድሮ ክረምት ግን እንደታሰበው የቀን ገቢ ሊያስገኝላቸው እንዳልቻለ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነጋዴዎች ይናገራሉ። ለዚህ የገበያ መቀዝቅ ዋናው ምክንያት ብለው የሚያነሱት የዋጋ መጨመር ነው። ሕብረተሰቡ መግዛት እየፈለገ እንኳን የጥላው ዋጋ እንቅፋት ሆኖበታል ብለዋል።
እነሱም ኑሯቸው በቀን ገቢ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ ለእንግልት ተዳረገናል ይላሉ። የቀን ወጪ መሸፈን፣ የቤት ኪራይ መክፈልና መሰል ነገሮችን ማሟላት እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል።
ኃይሉ ይባላል፤ ከሦስት ዓመት በፊት ከክፍለ-አገር እንደመጣና አዲስ አበባ ብዙም እንዳልኖረ ይናገራል። ብቻውን የሚኖር ሲሆን የኮቪድ 19 ወረርሽን መከላክያ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን እንዲሁም ሳኒታይዘሮችን በመሸጥ እንደሚተዳደር ይናገራል።
ከአሁን ቀደም የሚያገኘው ገቢ ጥሩ የሚባል ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ዝቅተኛ መሆኑን ያስረዳል። ለዚህም ምክንያት እንደ አብነት የሚያነሳው በሕብረተሰቡ ላይ የሚስተዋለውን የጥንቃቄ ክፍተት እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ መዘናጋትን ነው።
በአሁኑ ወቅት ሰዎች የኮቪድ ወረርሽኝ የለም ብለው ስለሚያስቡ ወረርሽኙን ለመከላከል የአፍና አፍንጫ ጭንብል እንዲሁም ሳኒታይዘር አይጠቀሙም። እሱም የተቀበላቸውን ጭምብልና ሳኒታይዘሮች እንደ ልብ መሸጥ አቅቶኛል ሲል ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
ቀድሞም በተዳከመ የሽያጭ አገልግሎት ላይ የክረምት ወቅት ተጨምሮ ሁኔታውን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎብኛል ይላል።
አንዳንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የቀን ሰራተኞች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት የቀን ሥራ ሠርተው የሚያገኙት ገቢ ዝቅተኛ እንደሆነ አንስተው፣ ባሁኑ ወቅት ግን ምንም አይነት ሥራ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
ከሥራ መጥፋት ጋር ተያይዞ ሥራ በሚያገኙበት ጊዜ የልፋታቸውን ዋጋ በማይመጥን ክፍያ ሊሠሩ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል። የቀን ሥራ ማጣቱ በዚሁ ሁኔታ ከቀጠለና መፍትሔ የማይገኝለት ጉዳይ ከሆነ አማራጭ ስለማይኖራቸው ወደ ጎዳና የሚወጡበት ዕድል ሰፊ መሆኑን በምሬት ሐሳብ ሰጪዎቻችን አንስተዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013



