በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ ያሉ ዩኒቨርስቲዎችን አሰመልክቶ በባህርዳር ከተማ “አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት ፣ ለተቀናጀ የዓባይ ተፋሰስ ልማት” በሚል መሪ ቃል አገር ዐቀፍ የምክክር መድረክ መካሄዱ ተገለጸ።
ይህ መድረክም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ ባዘጋጁት የምክክር መድረክ በተፋሰሱ የሚገኙ 10 ዩኒቨርስቲዎች የዓባይ ተፋሰስን ለማልማት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡና የጋራ መግባባት ላይ እንዲርሱ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።
የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኝ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ የምታስመዘግበው ድል ከአድዋ ጋር ምሳሌ ይሆናል በማለት ገልጸዋል።
አያይዘውም በአድዋ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በቅኝ ገዢዎች ላለመያዝና ነጻነታቸውን ለማስጠበቅ እንደታገሉት፣ የአሁኑ ትውልድም ራሱን ከድህነት ነጻ ለማውጣት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን ለሚያስፈልጉ ቴክኒካል ጉዳዮች በተፋሰሱ ዙሪያ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ሚና ከፍ ያለ እንደሆነም አብራርተዋል።የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄም (ዶ/ር) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከግድብ በላይ ለኢትዮጵያውያን ሕልውና ነው በማለት ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዛሬም ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በ2013 ዓ.ም. ከ2.49 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013


