ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያለ የምንሰማው ዜና ቅርሶችን የማፍረስ ጉዳይ የተመለከተ ነው። የሚያስተዳድራቸው ማን እንደሆነ ለማወቅ እስከሚያዳግት ድረስ ተቋማት “በአፈርሳለሁ፣ አታፈርስም” ግብ ግብ ሲታመሱ ይታያል። ይህን ቅርሶች የማፍረስ ነገር በባለሙያዎች እና በቅርስ ተቆርቋሪዎች ዘንድ አግባብነት የጎደለውና በጥናት ላይ ያለተመሰረተ በሚል ሁሌም ተቃውሞ እንደገጠመው ነው።
በቅርብ ጊዜያት ቡፌ ዳ ላጋርን ጨምሮ ለበርካታ አመታት የአዲስ አበባ ከተማ ትዝታ እና ማስታወሻ የሆኑ ቦታዎች በልማት እና በሌሎች ምክንያቶች ስም ወደ ፍርስራሽነት ሲቀየሩ አየተናል።
ከሳምንታት በፊት በቅርስነት የተመዘገበው የኢትዮጵያ ሆቴል እና አጠገቡ ያለው የበጎ አድራጎት ሕንፃ ፈርሶ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ይገነባል የሚለው ዜና መውጣቱን ተከትሎ ጉዳዩ ይመለከተናል በሚሉ ወገኖች ርብብርብ የአዲሰ አበባ ባህል፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ሕንፃዎቹ በቅርስነት የተመዘገቡ መሆናቸውን ጠቅሶ ለክፍለ-ከተማው በጻፈው ደብዳቤ መሰረት ሕንፃዎቹን ከመፍረስ ታድጓቸዋል። የወደፊቱ ባይታወቅም የአዲሰ አበባ ባህል፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ህንፃዎቹን ከመፍረስ አድኗቸዋል።
በአሁን ወቅት ላይ ደግሞ እጅጉን እያነጋገረ የሚገኘው ጉዳይ ከተሰራ 80 ዓመት እንዳሰቆጠረ የሚነገርው የንግድ ሥራ ኮሌጅ ሕንፃ ፈርሶ ቦታው ለሌላ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ መሥሪያነት ይውላል የሚለው ዜና ነው። ጉዳዩ ከተሰማ ጀምሮ ባለሙያዎች፣ የቅርስ ተቆርቋሪዎች እና የኮሌጁ የቀድሞ ተማሪዎች ሕንፃው እንዳይፈርስ ድምጻቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።
የንግድ ሥራ ኮሌጅ የመፍረስ ጉዳይ በጭምጭምታ ደረጃ መሰማት ከጀመረ የሰነበተ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል ኮሌጁ ግቢውን ለቆ እንዲወጣ መታዘዙ ከተሰማ ወዲህ ግን በሰፊው እያነጋገረ ይገኛል።
ከሦስት ወር በፊት ነው ሊፈርስ መሆኑን የሰማሁት የሚሉት አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡት የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪ፣ “አብደው ይወስኑታል ብዩ አልጠበኩም ነበር” ይላሉ።
“ለእኔ ቤቴ ስለነበር፣ ያደኩበት ትምህርት ቤት ስለሆነ ነው በጣም የምቃጠለው” ይላሉ አስተያየት ሰጪው።
አሁን የሚያሰጋው ነገር ለነገ መጥፎ ምልክት መሆኑ ላይ ነው። ምክንያቱም ንግድ ሥራ ኮሌጅ ለፋይናንስ ቀጠናው አይመጥንም ብሎ ለማፍረስ መነሳት ማለት ነገ ላይ ብሔራዊ ቲአትርንም እንደዚህ ላለማለታቸው ምንም ዋስትና የለም ሲሉ ስጋታቸውን ያነሳሉ።
ንግድ ሥራ ኮሌጁ ለ80 ዓመታት ያህል በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ትላልቅ ተቋማትን የሚያስተዳድሩ ባለሙያዎችን ያፈራ ተቋም እንደመሆኑ መጠን፣ ኮሌጁን አፍርሶ የፋየናንስ ተቋም መገንባት ማለት ስላቅ ነው የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑትና በግል ድርጅት ውስጥ በአማካሪነት የሚያገለግሉት አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ናቸው።
አንድ ከተማ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ለውጥ ታደርጋለች። አሁን አዲስ አበባ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ሳቢያ እየሰፉና እያደጉ ከሚሄዱት ከተሞች ውስጥ ትጠቀሳለች ይላሉ ባለሙያው።
ሌላው ለለውጡ እንደማሳያ የሚነሳው የሕዝብ ቁጥሩ መጨመር ነው። አሁን ላይ በከተማዋ ከሚወለዱት በላቀ ቁጥር የተሻለ ሥራ እና ኑሮ ፈልገው ወደ ከተማዋ የሚመጡት ዜጎች ቁጥር ከፍ ያለ ነው።
በአሁን ሰዓት በከተማዋ የውልደት ምጣኔ 2 በመቶ ሲሆን፣ ከተለያዩ አካባቢዎች በሥራ እና በተለያዩ ምክንያቶች የሚመጡ ደግሞ የ5 በመቶ ድርሻ አላቸው።
በዚህም ምክንያት ከተማዋ ላይ ጫና እንደሚኖር ግልጽ ነው። ይህ ጫና ይዞት የሚመጣው ተጨማሪ የቤት እና ግንባታ ፍላጎት መኖሩ አየቀሬ ነው። ለዚህም ሲባል የሚፈርሱ ቦታዎች ይኖራሉ።
አሁን ላይ ይሄን ጫና ለመቋቋም ሲባል ለግንባታ እና ለማስፋፍያ በሚል የተመዘገቡ ቅርሶችን ሳይቀር ማፍረስ ይስተዋላል።
“የከተማ ቅርስ ማለት አሮጌ ሕንፃ ማለት አይደለም ” የሚሉት አርክቴክቱ የከተማ ቅርስ ማለት ለከተማው ማኅበረሰብ ትርጉም የሚሰጡ፣ በከተማው ሥነ-ሕይወት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው እና የጋራ ትውስታን የያዙ በአጠቃላይ የከተማዋን መልክ እና የማኅበራዊ መዋቅርን የወሰኑ ጉዳዮች ቅርስ ይባላሉ ሲሉም ያስረዳሉ።
በሌላ መልኩ ደግሞ፣ ቅርስ የሚባለው የተለየ ጥበብ ያረፈበት ወይም ያንድን ዘመን ትውልድ ጥበብ እና አስተሳሰብ የሚወክል ማለት ነው ሲሉ አርክቴክት ዮሐንስ ያክላሉ።
ሕንፃ ሲፈርስ በአጠቃላይ የከተማውን መልክ እና ጠባይ ይቀይረዋል። አሁን ላይ እየታየ ያለው ቅርሶችን የማፍረስ ሒደት በግብር ይውጣ እየተሠራ መሆኑን ለመጥቀስ ከበቂ በላይ ምክንያት አለኝ ይላሉ።
በአንድ የከተማ ዕቅድ ወይም ማስተር ፕላን ውስጥ ቅርስ የሆኑ አካባቢዎች እና ቅርስ የሆኑ ግብረ ሕንፃዎች ተለይተውና ተቆጥረው ለሚከታተለው መሥሪያ ቤት ይሰጣሉ። ቅርስ የሚል መለያም ይሰጣቸዋል። ይሄን ሁሉ ሒደት ያለፈን ጉዳይ ከመሬት ተነስተህ ልታፈርሰው አትችልም ብለዋል።
ከተሞች በየአስር አመቱ የሚከለስ መዋቅራዊ ፕላን እንዳላቸው የሚያነሱት አርክቴክቱ፣ በውስጡ የኢኮኖሚ እቅድ፣ ግንባታው ከተማዋን የመለወጥ ተጽዕኖው እና የሕንፃዎች ርዝመት ውሳኔን ያካትታል። በማስተር ፕላኑ የሚካተት ነገር ግን በብዛት የማይሰተዋለው የከተማዋን መልክ ወይም ጠባይ ከሚወስኑት አንዱ የቅርሶች ጉዳይ ነው ይላሉ።
በዚህ አለማስተዋል ይመስላል በዘፈቀደ ቅርሶች ሲፈርሱ እያስተዋልን ያለነው። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እንኳ በአንድ ወቅት በቅርስነት የተመዘገቡ ነገር ግን እንዲፈርሱ የተደረጉ ነበሩ የሚሉት ባለሙያው፣ ይህ ሲሆን ግን ባለሙያዎች ተከራክረው ቅርሳዊ ፋይዳቸው ዝቅተኛ መሆኑ ከታመነበት ብቻ መሆን ይገባዋል። አሁን በአገራችን እያየነው ያለነው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው ይላሉ።
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ የሆኑት ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፣ ሰንጋ ተራን መንግሥት የፋይናንሺያል ቀጠና አድርጎ እያደራጀ መሆኑን ያነሳሉ። በዚህም ምክንያት የንግድ ሥራ ኮሌጁ 6 ኪሎ ከሚገኘው ቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ጋር አንድ ላይ ሆነው እንዲሠሩ ስለተወሰነ፣ ሰንጋ ተራ ያለው ቆሞ 6 ኪሎ ከሚገኘው ጋር ተጠቃሎ እንዲሠሩ ይደረጋል ብለዋል።
በአሁን ሰዓት ግብረ ኃይል አቋቁመን ኹሉም በተደራጀ መልኩ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው የሚሉት ደግሞ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤቱ ኃላፊ ወርቁ መኮንን(ዶ/ር) ናቸው። በተጨማሪም ሚንስትር ዲኤታው ይህን ይበሉ እንጂ ምንም አይነት ደብዳቤ እንዳልደረሳቸው ይናገራሉ።
ትልቁ መረዳት ያለብን ነገር ቢኖር ይህ ጉዳይ በግለሰቦች ጥረት ብቻ የሚሆን ነገር አለመሆኑን ነው። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የኪነ-ሕንፃ ታሪክ ማኅበር ለማቋቋም እየሠራን ነው የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አርክቴክት እና የከተማ ፕላን ባለሙያ ዳዊት በንቲ ናቸው።
መሥራቾችን ሰብስበን ዓላማው ላይ ተነጋግረን ሕጋዊ መስመር በማስያዝ ላይ ነን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ማኅበሩ ቅርሶችን እንዲጠበቁ የሚጥር መሆኑን እና በቅርስነት መጠበቅ አለባቸው በሚላቸው ላይም ሐሳብ ይሰጣል ብለዋል።
አሁን ብዙዎች ያልተረዱት ነገር ብለው ባለሙያው የሚያነሱት፣ ቅርስ ሳይነካ በዙሪያው ያሉትን ነገሮች መሥራትና ተናበው እንዲሄዱ ማድረግ መቻሉን ነው። በአሁን ሰዓት ላይ የፋይናንስ ቀጠና ለመመሥረት እንደሚፈርስ የተነገረው የንግድ ሥራ ኮሌጅም ጉዳይ አውሮፓውያን የተሳሳቱትን እኛም የመድገም አባዜ ውስጥ እንዳለን ነው። ይህ የፋይናንስ ቀጠና ዕሳቤ የቆየ እና ያለፈበት ነው የሚሉት አርክቴክት ዳዊት፣ እንደነዚህ አይነት አካባቢዎች ቀን ቀን ብቻ እንቅስቃሴ የሚታይባቸውና ማታ ማታ ግን ወደ ሙትነት የሚቀየሩ ናቸው። ይህ ደግሞ በዘላቂ የከተማ ዕሳቤ ውድቅ የሆነ ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ያነሳሉ።
ኮሜርስ ውስጥ ጥሩ ሆነው የተሠሩ ሦስት ወይም አራት ሕንፃዎች ሊገኙ ይችላሉ። የነዚህ ሕንፃዎች መፍረስ የሚያሳስበውን ያህል በተጨማሪ ልናየው የሚገባን ነገር የተማሪዎች አለመኖር አካባቢው ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ጭምር እንደሆነም ያነሳሉ። በሥነ-ከተማ አስተሳሰብ አንድ አካባቢ ሊያሟላቸው ከሚገባቸው መስፈርቶች መካከል በአካባቢው እግረኛ እንደፈለገ መንቀሳቀስ የሚያስችለው ቦታ እና መኖሪያ አካባቢ ሊኖረው እንደሚገባም ይጠቅሳሉ። እነዚህን የማያሟላ ከሆነ ግን አካባቢው ሕይወት አልባ እንደሚሆን አርክቴክት ዳዊት ይገልጻሉ።
ይህ ውሳኔ ሲወሰን ብዙ ያላገናዘባቸው ነገሮች አሉ የሚሉት ደግሞ የኮሌጁ የቀድሞ ተማሪ ናቸው። ከሕንፃው መፍረስ በተጨማሪ መታየት ያለበት ንግድ ሥራ ኮሌጁ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይጠቃለል ማለት ማንነቱን ማሳጣት ማለት እንደሆነ ያነሳሉ።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ከ200 በላይ የሚሆኑ የአስተዳደር ሠራተኞችን ለመበትን ሊገደድ እንደሚችልም ይጠቅሳሉ። ወደ 6 ኪሎ በሚሄዱበት ጊዜ የሥራ ዘርፍ መደራረብ ሊከሰት እና በዚህም ሠራተኛ ወደ ሌላ ቦታ ማሸጋሸግ ውስጥም ሊገባ እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ከምንም በላይ ግን 5000 ተማሪዎችን ወደ 6 ኪሎ ይዞ ሲሄድ ግቢው መተንፈሻ ስለማይኖረው በሚቀጥለው ዓመት በሚቀበላቸው ተማሪዎች ቁጥር ላይም ያለውን ተፅዕኖ በአግባቡ ተንትነው ያዩት አይመስለኝም ሲሉም ስጋታቸውን ያክላሉ።
በአሁኑ ሰዓት በይፈርሳል እና በአታፍርሱብን እየታመሰ ያለው የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ጉዳይ ፍጻሜው እጅግ የሚጠበቅ ነው። በተለያየ ጊዜ እየተነሳ ላለው ለዚህ ጉዳይ እልባት የሚሰጥ አንድ አካል ሊኖር እንደሚገባ ይነሳል። የባለሙያ ደሀ ባልሆነች አገር እንደዚህ ያሉ ውሳኔዎች ሲወሰኑ እነሱን ያካተተ ጥናት እና የውሳኔ ሐሳብ ማቀረብ የሚቻልበት አሠራር ሊዘረጋም ይገባል።
ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013



