ከ4.5 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪ ተጭነው ሲጓጓዙ በቁጥጥር ስር ዋሉ

0
808
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ከ4.5 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን አስታወቀ።
በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-24590 ኢት. ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪ (ቦቴ) ተጭኖ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲጓጓዙ የነበሩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ሐምሌ 28 ቀን 2013 በሞጆ ከተማ፣ ቀበሌ 02፣ ልዩ ቦታው አፍሪካ ነዳጅ ማደያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ ሊያዙ የቻሉት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ የፀረ-ኮንትሮባንድ ዳይሬክቶሬት፣የቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍና የሞጆ ከተማ ፖሊስ ከህብረተሰቡ የደረሳቸውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ በጋራ ተቀናጅተው ባደረጉት ክትትል መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ ቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዋሪዮ ጉዮ ገልፀዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ ከ4.5 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሲሆን የተለያዩ ልባሽ ጨርቆች፣ ለማህበረሰቡ ጤና ጠንቅ የሆኑ ሲጋራዎችና ሺሻዎች መሆናቸውንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ኮንትሮባንዲስቶቹ ምንም እንኳን የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ደብቀው ለማሳለፍ የተለያዩ ስልቶችን የሚጠቀሙ ቢሆንም ፖሊስ ከህብረተሰቡ የሚደርሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግና የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ በቁጥጥር ስር እያዋላቸው መሆኑን በወንጀል መከላከል ዘርፍ የፀረ-ኮንትሮባንድ ዳይሬክቶሬት፣ ሻለቃ ሁለት፣ ዲቪዥን ሁለት ሀይል አመራር ረዳት ኢንስፔክተር ዓሊ ሰይድ ገልፀዋል፡፡
በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ማንኛቸውንም ህገ-ወጥ ተግባራት ሲመለከት ህብረተሰቡ ለህግ አስከባሪ አካላት ፈጥኖ ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ መቅረቡንም ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here