ደን ለዓለማችን አስፈላጊ ነው ብሎ ለማስረዳት መሞከር ሳንባ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ነው ብሎ ለማስተማር እንደመሞከር ነው። የተክሎች አስፈላጊነትን ከልጅነታችን እየተማርን ብናድግም የደን መመናመንን ግን እንደሕዝብ ማስቀረት ሳንችል አሁንም ሽፋኑ እያሽቆለቆለ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። የዓለም ምግብ ድርጅት(FAO) በፈረንጆቹ 2020 ባወጣው ሪፖርት መሠረት በየዓመቱ የደን ሽፋናችን መጠን በ92 ሺሕ ሄክታር ይቀንሳል። በአንድ ዓመትም የሚሰፋው የደን መጠን 19 ሺሕ ሔክታር ብቻ ስለሆነ በየዓመቱ በአጠቃላይ 73 ሺሕ ሔክታር መሬት ይራቆታል። ከፈረንጆቹ 1990 ጀምሮ ባሉት 20 ዓመታት ከነበረው ሽፋን 18.6 በመቶ ወይም 511 ሺሕ ሔክታር ደን ተመንጥሯል።
ኢትዮጵያ የቆዳ ስፋቷ 1.13 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ ስፋት ውስጥ ሊታረስ የሚችለው መሬት 15.2 በመቶው ብቻ እንደሆነ ብሔራዊ ባንክ አምና ካወጣው አመታዊ ሪፖርቱ ለመረዳት ይቻላል። ይህ አሀዝ በ1990ዎቹ 45 በመቶ ነበር ተብሎ የተመዘገበ ቢሆንም፣ በ2011 ከ14 .3 እስከ 15.2 በመቶ እንደሚሆን የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ሠነዶች ያሳያሉ። ሊታረስ ከሚችለው ከዚህ መሬት ውጭ በደን የተሸፈነው መሬት 15 በመቶ አካባቢ እንደሆነ ዓለም ዐቀፉ የምግብ ድርጅት ያወጣው መረጃ ይጠቁማል።
በፈረንጆቹ 1990፣ 19 ሚሊዮን 258 ሺሕ ሔክታር ይሸፍን የነበረው የደን ስፋት ተመናምኖ በ2020 ወደ 17 ሚሊዮን 68 ሺሕ ሔክታር ወርዷል። በዓለም ዐቀፍ መስፈርት መሠረት እንደ ደን የማይቆጠር ቁመቱ 2 ሜትር በማይሞላ ቁጥቋጦ የተሸፈነው 22 ሚሊዮን 394 ሺሕ ሄክታር መሬት እንደሆነም ተገምቷል። ከ111 ሚሊዮን 971 ሺሕ ሔክታር አጠቃላይ የኢትዮጵያ መሬት ሽፋን ውስጥ ይህ ቁጥር አነስተኛ መሆኑ አያከራክርም። በደን ከተሸፈነው 17 ሚሊዮኑ ውስጥ 15 ሚሊዮን 865 ሺሕ የሚሆነው የተፈጥሮ ደን ሲሆን፣ በሰው እጅ የተተከለው ግን በጣም ጥቂት ነው። 1 ሚሊየን 203 ሺሕ ሔክታሩ ብቻ በሰው ጥረት የተሸፈነ እንደሆነ ተቋሙ የ2015 የመሬት መረጃን ተመርኩዞ የ2020 ሽፋን ምን እንደሚመስል መረጃውን ይፋ አድርጓል።
ኢትዮጵያ የደን ሽፋኗን ለማሳደግ እንቅስቃሴ ከጀመረች 100 አመታት አልፏታል። አፄ ምኒልክ የመሬቱ መራቆት ብቻ ሳይሆን የማገዶ እጥረቱንም ለመቅረፍ ባሕር ዛፍን አስመጥተው አሁን ካለው የደን ሽፋን 1.7 በመቶውን እንዲሸፍን አድርገዋል። 17 ሚሊዮኑን ሔክታር ከሸፈኑት አጠቃላይ የዛፍ ዝርያዎች ከኹለቱ በስተቀር ኹሉም ማለት ይቻላል አገር በቀል መሆናቸውን ጥናቶች ይጠቁማሉ። ምድሪቱን በደን ለመሸፈን የሚደረግ ጥረት በቅርብ የተጀመረ ባይሆንም፣ የቀደሙት ነገስታት ነባሮቹ እንዳይመነጠሩና እንዳይነኩ በማስጠበቅ ላይ ያተኮረ ፖሊሲን ይከተሉ ነበር። ከሺሕ አመታት በፊት እንዳይነኩ ጠባቂ ተመድቦላቸው ባሉበት የቆዩት ሱባና ደንቆሮ ጫካ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው። ቤተክርስቲያን አጥራና ከልላ ከምትጠብቃቸው በተጨማሪ መንግሥታትም የየአቅማቸውን ሲጥሩ ለመቆየታቸው ብዙ ማስረጃዎች አሉ።
ችግኝ መትከልን በተመለከተ አፄ ምኒልክ ባህር ዛፍን ለተከለ አንድ ጠገራ ብር ይሸለማል ብለው ለማበረታታት ሞክረዋል ከሚባለው ውጭ፣ አሁን አሁን ሕብረተሰቡን ለማሳተፍ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ቅስቀሳ ሲደረግ አይስተዋልም።
ለእርሻም ሆነ ለማገዶ ተብሎ የሚካሄድ የደን ምንጣሮ የሚባባሰው አገሪቱ በጦርነት ስትታመስና የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ እንደሆነ ባለሙያዎች ይስማሙበታል። የዘውዱ ስርዓት ያስጠብቃቸው የነበሩ ጥብቅ ደኖች የደርግ መንግሥት ሲተካ እምብዛም ትኩረት ባለማግኘታቸው የለውጡ ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደነበር የሚናገሩ አሉ። ስርዓቱ ከደን መጠቀም አለብን በሚል እሳቤ “ደን ልማት” የሚባል ተቋም መስርቶ፣ ለግለሰቦች ጭምር የቤት መሥሪያ አጣና በማቅረብ ጭፍጨፋውን ለመቀነስ ሞክሮ ነበር።
በኢሕአዴግ ዘመን ፓርክ እየተባለ በተለያየ አካባቢ ችግኝ ሲተከል እንደነበረም የሚታወስ ነው። በተለይ በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ውስጥና ጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል አካባቢ፣ እንዲሁም የአፍሪካ መሪዎች ለማስታወሻ እዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት ፊት ለፊት የተከሉት የሚታወስ ነው። ከዚህ ቀደም የተተከሉት ምን ደረጃ እንደደረሱ ይፋ የሆነ ዝርዝር ሪፖርት ባይኖርም፣ ከቀበና ልደታ አልፎ እንዲሁም ከእንግሊዝ ኤምባሲ ጀርባ የተተከሉት ጫካ ሆነው ውስጣቸው ጅብ እስኪራባባቸው ድረስ ጨልመዋል።
ከባለፈው 3 አመት ወዲህ ለውጥ መጣ ተብሎ የሥልጣን ቅብብል ከተደረገ ወዲህ የደን ሽፋንን ለመጨመር በሚል የተሞከረው ተግባር በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ እስከመሆን ደርሷል። በቀን 350 ሚሊዮን ችግኝ ተተከለ ሲባል፣ እንዴት ሊሆን ይችላል? ብለው አንድ ኢትዮጵያዊ ቢያንስ 3 ችግኝ መትከል ይጠበቅበታል እያሉ ለማጣጣል የሞከሩ ቢኖሩም ማስረጃ ማቅረብ ስላልቻሉ ዝም ብለው ቀርተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በፈረንጆቹ 2022 በአጠቃላይ 20 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ አለው ተብሎ ተነግሮ ነበር። በአመት 4፣ 5 እና 6 ቢሊየን ችግኝ ተዘጋጅቶ እየተተከለም ይገኛል። 1 ቢሊዮን ለጎረቤት አገር የሚሰጥ ነው በመባሉም፣ ዕቅዱን ለማሳካት ቢያንስ ከአሁን በኋላ 6 ቢሊዮን ችግኞችን አፍልቶ ማጽደቅ ይጠበቅበታል።
በሌላ በኩል፣ ይህን ያህል መጠን ማለትም፣ ከሕዝብ ቁጥራችን አንፃር 200 እጥፍ የሚሆንን ችግኝ ተንከባክቦ ለማሳደግ አዳጋች ያደርገዋል የሚሉ አሉ። አንድ ኢትዮጵያዊ ቢያንስ 180 ችግኞችን ውኃ አጠጥቶ፣ ኮትኩቶ፣ ለአካለ ዛፍ ማድረስ ይጠበቅበታል። ተፈጥሮ ተንከባክቦ የሚያሳድግበት ምቹ ቦታ ቢኖርም፣ የበጋው ወቅት ከመድረሱ በፊት ሥራቸውን አስረዝመው ድርቅን መቋቋም የማይችሉት ምን ያህሉ እንደሆኑ በአኃዝ የተደገፈ ማስረጃ ስለሌለ ሊታሰብበት እንደሚገባ የሚናገሩ አሉ።
ችግኝ መትከሉ ጠቃሚ ቢሆንም፣ ያለእንክብካቤና ክትትል ያን ያህል ለውጥ እንደማያመጣ ይታመናል። መንግስት ይህን ያህል መጠን ያለው ችግኝ አስፈልቶ፣ መትከያ ጉድጓድ አስቆፍሮ፣ ወደሚተከሉበት አጓጉዞ፣ የሚተክሉን ቀስቅሶና አንቀሳቅሶ፣ እንዲሁም የተለያዩ ወጪዎችን ሸፍኖ ለአንድ ችግኝ ምን ያህል እንደሚያወጣ በእርግጠኝነት ባይታወቅም፣ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚሆን ግን ግልጽ ነው። ከድሀ አገር ሀብት አንፃር ከፍተኛ በጀት የወጣባቸው እነዚህ ችግኞች ታዲያ ያለ ተንከባካቢ ሊተዉና ለከፍተኛ ኪሳራ ሊያጋልጡ እንደማይገባ ግልጽ ነው። ከዛሬ 2 አመት በፊት የተተከሉትን ዝናብ ሲጠፋ ተካዮቹ ሆ ብለው በሌላ ከፍተኛ ወጪ አንዴ ብቻ ሄደው ማጠጣታቸው እንዳማያዛልቅ ብዙዎች መናገራቸው የሚታወስ ነው። በመደበኛነት በአካባቢያቸው ያለ ማሕበረሰብ በቅርብ እንዲንከባከባቸውና በዳዋ ከመበላትም እንዲጠብቃቸው ካልተደረገ ውጤታማነቱ ዝቅተኛ እንደሚሆን የሚናገሩ ብዙ ናቸው።
በሌላ በኩል፣ የቁጥሩን መጋነን እየጠቀሱ እውነትነቱን ለማረጋገጥ የሚጥሩም አሉ። ከኢትዮጵያ አጠቃላይ 113 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ደን ሊተከልበት የሚችለውን መጠን በመለየት የሚናገሩ ናቸው። 15 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው የተፈጥሮ ደን ያለው በመሆኑ፤ 22 ሚሊዮኑ በቁጥቋጦ በመሸፈኑ፤ 20 ሚሊዮን ገደማው የሚታረስ በመሆኑ፤ 768 ሺሕ ሔክታሩ በውኃ የተሸፈነ በመሆኑ፣ እንዲሁም አፋርን በመሳሰሉ በረሃማነት ያላቸውና ችግኝ ሊተከልባቸው የማይችሉ ቦታዎች ሲቀነሱ ቀሪው ቦታ ከግማሽ ያንሳል።
ለግምት እንዲመች ግማሹ ቦታ ላይ መትከል ይቻላል ቢባል እንኳን ወደ 555 ቢሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ ይሆናል። ይህ ማለት በ27 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አንድ ችግኝ መኖር እንዳለበት ያመለክታል። 5 ሜትር በአምስት በሆነ ቦታ ላይ በአማካይ አንድ ችግኝ መተከል ከኖረበት፣ አሁን ካለው የከተማ አቅራቢያ ሽፋን አኳያ 20 ቢሊዮን ይተከላል ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ያደርገዋል። ሦስት አራተኛው እስከዚህ ዓመት መጨረሻ ድረስ ይተከላል ብሎ ለማመን፣ የተራቆተውን አብዛኛውን የኢትዮጵያ መሬት በማየት አነጻጽሮ መገመት ያስፈልጋል።
ቁጥሩና እውነታው ይለያያል የሚሉ ሰዎች የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርባሉ። ከሪፖርት አቀራረቡ ጋር በተገኛኘ ልዩነት ይፈጠራል የሚሉ፣ በበጀቱና በሚወጣው ወጪ መሰረት ባለሥልጣናቱ የሚያውቁትና መሬት ላይ የሚተከለው እንደሚለያይ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። ችግኞቹን ካፈሉት ጀምሮ ቆጥሮ የሚረከበውና አጓጉዞ የሚያስረክበው ትክክለኛውን ቁጥር ስለማቅረቡ የበላዮች ለማወቅ እንደሚሳናቸው ይገምታሉ። ይህ ጉዳይ ይበልጥ ተጠንቶ ቁጥሩ ከወጣው ወጪ አንጻር ብቻ ሳይሆን ከተተከለው ጋር ተመሳክሮ መገለጽ እንዳለበት አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ መንከባከቡም ሆነ ምን ያህሉ ጸደቀ ብሎ ለመገመትና ለማወቅ ቢሞከር የበለጠ ስሕተት ላይ ይጥላል ይላሉ።
ችግኝ ሲተከል በምን ያህል ርቀት መተከል እንዳለበት ከዝርያ ዝርይ የሚለያይ ቢሆንም፣ ከአቆፋፈሩ ጀምሮ የሚያፈሉት ጋር በመቀናጀት በጋራ መሠራት እንዳለበት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህን ያህል ቢሊዮን ተዘጋጅቷል እየተባለ ለመትከል የፈለጉ ወጣቶች ችግኝ የለም ሲባሉ መስማትም የተለመደ ነው። ብዙ ወጪ ወጥቶ ሠራተኞች ለተከላ ከተጓዙ በኋላ እጥረት ተፈጥሮ መትከል ሳይችሉ የተመለሱ እንዳሉ መስማቱም አዲስ አይደለም።
የችግኝ ተከላውን የሚያስተባብረው የመንግሥት አካል እስካሁን ምን ይህሉ እንደተተከለ መረጋገጡን፣ እንዲሁም ስንቱ እንደፀደቀ ፣ ምን ያህል ወጪ እንደተደረገ፣ ከዕቅዱ ምን ያህሉ በምን ምክንያት ሳይተከል እንደቀረ፣ ከተተከለውስ ምን ያህሉ ገቢ ሊያስገኝ የሚችል ፍራፍሬን የመሳሰለ ዝርያ ነው የሚለውን፣ ችግኞቹ በማን እንደፈሉ፣ የማንና ምን አይነት መሬት ላይ እንደተተከሉ፣ ቆጠራውና ቁጥጥሩ በማን እንደሚካሄድ፣ ከክልሎች ክፍፍል አንጻር ያፈሉትና የተከሉት ድርሻ ምን እንደሚመስል፣ ማን ሊጠብቃቸውና ሊንከባከባቸው እንደሚችል፣ እንዲሁም ለጎረቤት አገራት ይሰጣሉ ከተባሉት ምን ያህሉ ተወሰዱ ወይስ በእኛ ወጪ ተሰጥተው ተተከሉ የሚለውን ለሕዝብ ማሳወቅ ይጠበቅበታል። በዚህ ጉዳይ ይመለከታቸዋል የተባሉት የመንግሥት ኃላፊ በሥራ ምክንያት ከከተማ ስለወጡና መረጃውን ማግኘት ስላልቻልን በቀጣይ ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን።
ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013




ደን የተፈጠረውን ሚዛን ከማስጠበቅም በሻገር ለኢኮኖሚው ትልቅ ፈይደው አለው ስለዚህ የደን ሽፈንን መጨመር ያስፈልጋል ።