በከተማዋ ቀላል ባቡር መንገዶች እና የቀለበት መንገድ ላይ የሚስተዋለውን የመንገድ ማቋረጫዎች ችግር ለመፍታት ዘመናዊ የእግረኞች መሻገሪያ ድልድይ ለማስገንባት በሂደት ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታውቋል።
በድልድዮቹ የግንባታ ዲዛይን እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የኤጀንሲው አመራሮች እና የቻይናው ዥ ያንግ ዚ ዘ ሰከንድ ከተባለ የግንባታ ኩባንያ ጋር ውይይት አድርገዋል።
በከተማዋ በቀላል ባቡር መንገድ የሚጨናነቅባቸው ጉርድ ሾላ፣ መሪ ሲ ኤም ሲ እና ጎጃም በረንዳ እንዲሁም በአዲስ ሰፈር ሃኪም ማሞ በተባሉ አከባቢዎች የሚገነቡት ዘመናዊ የእግረኛ መሻገሪያ ድልድዮች ግንባታ የሚሆን ጥናት እና ዲዛይን ላይ ውይይት ተደርጓል።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንደ ብርሃኑ ግርማ ገለጻ በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራፊክ ፍሰት ለመቀነስ እና የመንገድ ደህንነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።
እነዚህ ድልድዮች ከዚህ በፊት የተለያዩ አካባቢዎች ተገንብተው ሰው የማይጠቀምባቸው አይነት እንዳይሆን ተገቢው ትኩረት እንደተሰጠው ያነሱ ሲሆን አካል ጉዳተኞችንም ባማከለ መልኩ ምቹ ሆነው እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል።
በውይይቱ ላይ የቀረበው ጥናት ድልድዮቹ በሚገነቡባቸው ቦታዎች የመሬት አጠቃቀም፣ወደ መንገዶቹ የሚወስዱ መጋቢ መንገዶች፣ የአውቶቡስ እና የታክሲ መጫኛ እና ማውረጃዎችን፣ የእግረኞች እንቅስቃሴን እና በአካባቢዎቹ የሚስተዋሉ የትራፊክ ፍሰቶችን መሰረት ያደረገ መሆኑን እንዳለበት ያመለክታል።
ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013


