የኦሎምፒኩ እሰጥ አገባ

0
489

በየ4 አመቱ እየመጣ የብዙዎችን ትኩረት የሚስበው የኦሎምፒክ ውድድር ከዚህ በፊት እንደተለመደው ኢትዮጵያውያንን ከማስደሰት ይልቅ አስከፍቷል። ውድድሩ ከተያዘለት ፕሮግራም አንድ ዓመት ዘግይቶ በመጀመሩ ብዙዎች ተወዳዳሪዎች ይበልጥ ተዘጋጅተው ውድድሩና ፉክክሩ ይጦፋል ብለው ገምተው የነበረ ቢሆንም እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቷል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስና የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ አለመስማማታቸው ገሀድ ከወጣ ቆይቷል። የኹለት ግለሰቦች አለመግባባት የኹለት አገራዊ ተቋማትን መለያየት በእዚህ መጠን ያስከትላል ብሎ የገመተ አልነበረም። በቶክዮው ኦሎምፒክ ወቅት ችግር ሊያመጣ ይችላል ብለው የሚያውቁትን ሳይዘረዝሩ እልባት እንዲሰጠው የወተወቱ ቢኖሩም፣ ሰሚ ሳያገኙ ኹለቱም ወገኖች በየፊናቸው ወደ ዓለም ዐቀፉ ውድድር አምርተዋል።
የቀደመው የ2016ቱ ኦሎምፒክ ላይ በተሳትፋ አትሌቶቿ ጥሩ የሚባል ውጤት አስመዝግባ የተመለሰችው ኢትዮጵያ፣ ለውድድሩ ተመድቦላት የነበረው በጀት 40 ሚሊዮን ብር ገደማ እደነበር የሚያነሱ የውስጥ አዋቂዎች አሉ። በዘንድሮው ውድድር በቂ አይደለም ተብሎ ይሁን ወይም የበለጠ ውጤት እንዲያመጡ በግልፅ ባይነገርም በጀቱ በ5 ዕጥፍ ገደማ እንዲያድግ ተደርጎ ነበር ይላሉ። ይህ ቢሆንም ግን የተገኘው ውጤት ከባለፈው ከግማሽ በታች መሆኑ ብዙዎችን አሳዝኗል።
የውጭ አገር ተፎካካሪ ተወዳዳሪዎች ጭምር ኢትዮጵያ የሠራችው ትክክል እንዳልሆነ፣ ተወዳዳሪ አመራረጥ ላይ ከባድ ስህተት መፈፀሙን የእኛዎቹ ሳይናገሩ ቀድመው በዓለም ዐቀፍ ሚዲያ አስተጋብተውታል። ዓለም ያወቀው ችግራችን እልባት ሳያገኝ የሚያስቆጭ ውጤት ስለተገኘ ወደ አገር ቤት ሲመለሱ አቀባበል ሳይሆን ግምገማ ይጠብቃቸዋል እያሉ የተናገሩ ብዙ ናቸው። የማስተካከያ ዕርምጃ ቀደም ብሎ ባለመወሰዱ ያዘኑ፣ ልዩነቱን የፈጠሩት ኹለቱም ፕሬዝዳንቶች እንዲወገዱ እስከመጠየቅ ደርሰዋል።
የባለሥልጣናቱ ልዩነት እንዳለ ሆኖ አትሌቶቹን መጨመሩም ብዙዎችን ያስገረመ ድርጊት ነበር። እርስበርሳቸው ተቦዳድነው ጨርሰው፣ “ሊያስመልሱኝ ይችላሉ” ከሚል ስጋት ጀምሮ እንዳይወዳደሩ የተደረጉም መኖራቸው ሲሰማ አጀብ አስብሎ ነበር። “ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” እንደሚባለው አሸናፊዎቹ የላካቸውን ሕዝብና አገር ረስተው ሜዳልያዎቻቸውን በየፊናቸው ላሰለፉዋቸው አመራሮቻቸው መስጠታቸው ጉድ አስብሎ ነበር። በመሪዎቹ የጀመረው አለመግባባት ልዩነቱ ገዝፎ ጋዜጠኞችንም እስከማጓተት ደርሶ ነበር። አንዱ ተነስቶ ሌላውን ጎራ ሲዘልፍ፣ ያኛውም የራሱን ጎራ አሰልፎ በእንካሰላንቲያ ሲጠዛጠዙ ሕዝብ ግራ እንደገባው ቆይቷል።
አገርን ያዋረደው ክፍፍሉ በእከክልኝ ልከክልህ እዚህ ሲደርስ፣ ኹለቱም እንዳያኩ የሚያጸዳቸው ጠፍቶ መሳለቂያ እስከመሆን ተደርሷል። ኹለቱም ቡድኖች አለቃ የሌላቸው ይመስል ልዩነታቸውን እያሰፉ መንግሥትንም እንዳይከፍሉ የሚል ስጋት አሳድሯል። መለያየታቸውን የሚፈልግና ከፋፍሎ ለመግዛት የሚመኝ ያለ ይመስል ስፖርቱን ጦርነት ካስመሰሉት፣ አገር እንዲመሩ ቢደረግ ኖሮ ምን ሊውጠን ነበር ሲሉ አንዳንዶች በፌዝ መልክ ምልከታቸውን አጋርተዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here