የአውቶብሶችን ውጫዊ አካል ለማስታወቂያ ማስነገሪያነት ለማዋልም መመሪያ ተዘጋጅቷል
ሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት ድርጅት የትራንስፖርት አግልግሎት ከመስጠት ባሻገር ዘመናዊ የሆነ የአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ ተቋም ለመክፈት በሒደት ላይ መሆኑን የድርጅቱ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ሳሙኤል ፍሰሃ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አሁን ላይ አስፈላጊ የሚባሉ ግብዓቶችን በሟሟላት ሒደት ላይ እንደሆኑም አክለዋል።
ለማሠልጠኛው የሚሆኑ ቦታዎች በሰሚት፣ቃሊቲ እና ሸጎሌ አካባቢ የሚገኙ እንደሆነና ለጊዜው ከነዚህ አንዱን መርጦ ሥልጠና ለማስጀመር መታሰቡ ታውቋል። በማሠልጠኛው ውስጥ የተግባርም ሆነ የንድፈ ሐሳብ ስልጠናን በሚገባ ደረጃ መስጠት የሚችሉ ብቁ ባለሙያዎች እየተዘጋጁ እንደሆነና በቅርቡ ሥልጠናውን ለማስጀመር እየተሠራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።
አሁን ላይ የማሠልጠኛ ተቋሙን ለማስጀመር ይቻል ዘንድ የብዙ የአሽከርካሪ ተቋማትን ልምድና ክህሎት በመቀመር፣ ለተግባር እንዲሁም ለጽንሰ ሐሳብ ማስተማሪያነት የሚሆኑ ቦታዎችን በማመቻቸት፣ እና ለማሰልጠን የሚረዱ ግብዐቶችን በማሟላት ሒደት ላይ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም የሸገር ብዙኃን ትራንስፖርት ድርጅት ገቢውን ለማሳደግ ይረዳው ዘንድ የአውቶብሶችን ውጫዊ አካል ለማስታወቂያ ማስነገሪያነት ለማዋል እንቅስቃሴ መጀመሩን የሚገልጹት የድርጅት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ሳሙኤል፣ ለዚህም ሲባል መመሪያ ተዘጋጅቶ ለቦርድ ቀርቦ የጸደቀ መሆኑንና ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት መጠናቀቁን አሳውቀዋል።
ከዚህ በፊት በአውቶብሶች ውስጥ ለማስታወቂያ ማስነገሪያነት ሲያገለግሉ የነበሩ የቴሌቪዥን ስክሪኖች አሁን በአብዛኛው ብልሽት የገጠማቸው እንደሆነና በመሥራት ላይ ያሉትም ከማስታወቂያ ይልቅ ስለ ኮሮና ቫይረስ ግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች እየታዩባቸው መሆኑን ገልጸው፣ በቅርብ ግን የማይሠሩትን በመምረጥና በማስጠገን እንደበፊቱ ማስታወቂያ ማስነገሪያ እንዲውሉ ለማድረግ እየተሠራ ነው። በዚህም ማስታወቂያን ብቻ በተመለከተ የሚቆጣጠር ቡድን ተቋቁሞ በሥራ አስከያጁ መሪነት ሥራ መጀመሩን ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ድርጅቱ አስፈላጊ ነው የሚለውን የጥገና ሥራ ካከናወነ በኋላ በአውቶብሶቹ ላይ ማስታወቂያ ለማስነገር ለሚፈልጉ አካላት ግልጽ ጨረታ እንደሚያወጣም አክለው ገልጸዋል።
በ2013 በጀት አመት ደርጅቱ 78 ሚሊዮን ለሚሆኑ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ለሚገኙ ነዋሪዎች የመጓጓዣ አገልግሎት መስጠቱን ያነሱት ሳሙኤል፣ 50 ሚሊዮን በመደበኛ አውቶብሶች እና 28 ሚሊዮን በድጋፍ ሰጪ አውቶብሶች በአጠቃላይ ለ78 ሚሊዮን ሕዝብ የመጓጓዣ አገልግሎት መስጠቱንም አስረድተዋል።
ለተገልጋዮች ቁጥር ከፍ ማለት በድጋፍ ሰጪነት የብዙኃን ትራንስፖርቱን የተቀላቀሉት አውቶብሶች ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በድጋፍ ሰጪነት የተመደቡት አውቶብሶች በቀን ከ122 ሺሕ በላይ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚኖሩ ነዋሪዎችን ያገለግላሉ። እነዚህ አውቶብሶች ከዚህ ቀደም መደበኞቹ የሸገር አውቶብሶች መግባት በማይችሉባቸው በርካታ መስመሮች በመሰማራታቸውና በመዲናዋ አጎራባች አካባቢዎች ላይ አገልግሎት በመጀመራቸው የተገልጋዩን ቁጥር ከፍ አድረጎታል።
በከፍተኛ ሁኔታ የፍላጎት ማደግ በሚታይበት የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ለውጥ እንዲመጣ በማሰብ ድጋፍ ሰጪ አውቶብሶች ወደ ሥራ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በደጋፍ ሰጪነት የመጡትን አውቶብሶች ጨምሮ በአሁን ሰዓት ላይ 630 አውቶብሶች ለሕብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
ሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ግንቦት 19/2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የበላይ ጠባቂነት በደንብ ቁጥር 70/2008 ዓ.ም. በአዋጅ የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።
ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013



