ቡናን ከአርሶ አደሮች ተቀብለውና ዕሴት ጨምረው ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ኩባንያዎች መዘጋጀታቸው ተገለጸ

0
1724

በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ ኩባንያዎች፣ ቡናን ከአርሶ አደሮች በቀጥታ ተቀብለውና ዕሴት ጨምረው ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ መዘጋጀታቸው ተነገረ።
በኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉ ኩባንያዎች ዕሴት ጨምረው ቡና ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ መዘጋጀታቸው ከዚህ ቀደም የነበረውን የቡና የውጭ ንግድ እንደሚያሳድግ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ምንም አይነት ዕሴት ሳይጨመርበት በደረቁ ወደተለያዩ የውጭ አገራት፣ በተለይ አውሮፓና አሜሪካ፣ ይላክ እንደነበር ጠቅሰው፣ በዚህም የሚገኘው የውጭ ገቢ አነስተኛ እንደነበር ይናገራሉ።

ይህንን ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በአገር ውስጥ ካሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በመተባበር ኩባንያዎች ዕሴት የተጨመረበትን ቡና ወደ ውጭ አገር እንዲልኩ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ ታውቋል።
ከነዚህም መካከል በይርጋአለም አግሮ ኢንዱስተሪ ፓርክ ውስጥ የተወሰኑ ኩባንያዎች ገብተው ሥራ መጀመራቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። በተመሳሳይ በጅማና በሐዋሳ ኢንደስትሪ ፓርኮች ሌሎች ኩባንያዎችም ከአርሶ አደሩ ቡናን በቀጥታ ተቀብለው ዕሴት ጨምረውበት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ሒደቶችን መጀመራቸውን አንስተዋል።

በዘንድሮው 2013 በጀት ዓመት ዕሴት የተጨመረበት ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተነግሯል።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ጥሬ ቡና ወደ ውጭ ገበያ ይላክ ነበር። ይህም አገሪቷ ካላት የቡና ብዛት አንጻር በስፋት ገቢ ማስገኘት ባለመቻሉ ቡና ዕሴት ተጨምሮበት ለውጭ ገበያ መቅረብ መጀመሩን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ዕሴት የተጨመረበት ቡና ለወጭ ገበያ ለማቅረብ የቡናና ሻይ መመሪያ በማዘጋጀት ለተጠቃሚ እንዳቀረቡ እና በአገራችን የሚገኙ ኢንቨስተሮችም በቡና የውጭ ንግድ ላይ በስፋት ገብተው እየሠሩ እንደሚገኙም አውስተዋል።

ቡናን ከአርሶ አደሩ በቀጥታ ተቀብሎ ወደ ውጭ ገበያ የመላክ ሂደት ለአርሶ አደሮቹ የተሻለ ጥቅም የሚያገኙበት እድል እንደሚሆን የሚያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ከጥሬ ቡና ውጪ የተቆላና የተፈጨ ቡና ወደ ገበያ ለማስገባት በሚደረግ ጥረት ላይ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ አንስተዋል።

ዕሴት የተጨመረበት ቡናን በአገር ውስጥ በስፋት እንዳይሸጥ ያደረገው ሕብረተሰቡ የተቆላና የተፈጨ ቡናን ከመጠቀም ይልቅ ጥሬ ቡና ገዝቶ መጠቀም ስለሚመርጥ ነው ብለዋል።
እንደ ዳሬክተሩ ገለጻ፣ ይህን የአገር ውስጥ ዕሴት የተጨመረበትን የቡና ግብይት ለማሳደግ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

አያይዘውም የኢትዮጵያን የተቆላና የተፈጨ ቡና በዓለም ዐቀፍ ገበያ ውስጥ ለማስገባትና ትርፋማ ለማድረግም ዕክሎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ በመጥቀስ፣ ዕሴት የተጨመረበት የተቆላና የተፈጨ ቡናን በውጭ አገር ገበያ ውስጥ ተደራሽነቱን ለማስፋት ኩባንያዎች ከተለያዩ አገራት ጋር ተቆራኝተው መሥራትን እንደ አንድ ኣማራጭ መጠቀም ይኖርባቸዋል ሲሉ መክረዋል።

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያን ቡና የሚገዙት የውጭ አገራት አምስት የነበሩ ሲሆን፣ ባሁኑ ወቅት ወደ 33 ደርሰዋል። የኢትዮጵያ ጥሬ ቡና ደንበኞች የነበሩት አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ቤልጂየምና ሳዑዲ ዐረቢያ እንደነበሩም ጠቅሰዋል።

በቀጣዩ 2014 በጀት ዓመት በጥሬው ኲለት መቶ ሰማንያ ሺሕ ቶን ቡና ተልኮ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዷል። ዕሴት የተጨመረበት ቡናን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ዘንድሮ የተገኘውን ሦስት ሚሊዮን ዶላር ወደ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here