የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 191 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ዕዳ ተሰርዞ ወደካፒታል እንዲዞር ተደረገ

0
967

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወሰደው ብር ውስጥ 50 በመቶ ማለትም 191 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ዕዳ ተሰርዞ ወደካፒታል እንዲዞር ተወስኗል።
የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የመንግሥት ዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዛሬ የአራትዮሽ ሥምምነት አድርገዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እ.አ.አ. ከ2004 እስከ 2016 ከንግድ ባንክ የወሰደው ብድር ሙለ በሙለ እንዲሁም በ2017 የወሰደው ብድር በከፊል ወደካፒታል እንዲዞርለት ተወስኗል።
ተቋሙ እ.አ.አ. ከ2017 ወዲህ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዳቸውን ቀሪ ብድሮች ግን በራሱ እንደሚከፍል አስታውቋል። የዕዳ ስረዛው ተቋሙን 191 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ከነወለዱ የሚያስቀርለት ሲሆን፣ በተያዘው በጀት ዓመት 17 ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በቀጣይ በጀት ዓመት 18 ነጥብ 81 ቢሊዮን ብር ወለድ ከመክፈል ታድጎታል።
በተያዘው በጀት ዓመት ይከፈል የነበረው የ17 ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር ወለድ የተቋሙን የ2013 በጀት ዓመት ገቢ ከ85 በመቶ በላይ ይሸፍናል። የዕዳ ስረዛው የተቋሙን ዕዳ ወደ ካፒታልነት ስለሚያዞረው የሒሳብ መዝገቡን እንደሚያስተካክለው የተገለጸ ሲሆን፣ ተቋሙን ጠንካራና ተወዳዳሪ በማድረግ ወደፊት ለሚያከናውናቸው ሥራዎች አቅም እንደሚፈጥርለት ይታመናል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተቋሙ አጠቃላይ ገቢ 13ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ደርሷል። አፈፃፀሙ ከዕቅድ አንፃር 101 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ክንውኑ ተቋሙ የራሱን ወጪ በራሱ መሸፈን የሚችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ለመሆኑ ማሳያ ነው ተብሏል።
በሥምምነቱ መሠረት አበዳሪው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 191 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብሩን የሚጠይቀው ከተቋሙ ሳይሆን አዲስ ከተቋቋመው የመንግሥት ዕዳና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ላይ ይሆናል።
ከፍተኛ ዕዳ ካለባቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የስኳር ኮርፖሬሽን፣ የቀድሞ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የኬሚካል ኢንደስትሪ፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኢትየጵያ አገልግሎት ዕዳ እንዲሰረዝ የሚያደርግ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here