የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በአንድ ጊዙ ለማካሄድ አለመቻሉን ተከትሎ በኹለት ዙር ለማድረግ መገደዱ የሚታወስ ነው። በዚህ የመጀመሪው ዙር ምርጫ ሰኔ 14/2013 ተካሂዶ ኹለተኛው ዙር ምርጫ ጳጉሜ 1/2013 እንድካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት ቢሆንም ቦርዱ ቀኑን ለማራዘም ማሰቡ ተገልጿል።
ቦርዱ የኹለተኛውን ዙር ምርጫ በተመለከት ባሳለፍነው ሐሙስ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ውይይት ጳጉሜ 1/2013 እንድካሄድ ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት የኹለተኛው ዙር ምርጫ መስከረም 18/2014 እንዲካሄድ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል ተብሏል። ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ውይይት ሰኔ 14 ምርጫ ያልተደረገባቸው አካባቢዎች ምርጫ ወደ መስከረም እንዲሸጋገር የጠየቀው ቅድም ሥራዎች በአግባቡ ባለመከናወናቸው ነው ተብሏል።
ምርጫ ቦርደ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በአንድ ቀን ማድረግ ያልቻለው የጸጥታ ችግር፣ የመራጮች ምዝገባ በአግባቡ አለመከናወን፣ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ያጋጠሙ እንከኖች እንዲሁም ቦርዱ ምርጫውን በተመለከተ በፍርድ ቤት እየታዩ ያሉ የምርጫ ጉዳዮች ባለማጠናቀቁ ነበር።
የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሰኔ 14 ተካሂዶ የምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በሠራቸው ዘገባ በተለይ የጸጥታ ችግር ያለባቸው አከባቢዎች የጸጥታ ችግሩ መሻሻል ካላሳየ ቦርዱ ኹለተኛውን ዙር ምርጫ ጳጉሜ አንድ ማድረግ እንደማይችል መዘገቧ የሚታወስ ነው። ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ ተቆርጠው ከቀሩት ቦታዎች መካከል ሱማሌ እና ሐረሪ ክልል ሙሉ በሙሉ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ በኹለት ዞኖች እንዲሁም በሌሎች ክልሎችም ምርጫ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች አሉ።
ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013


