የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮችን ለመታደግ የተጀመረ እንቅስቃሴ

0
1054

ኢትዮጵያ የተለያየ ቋንቋ፣ ወግ፣ የአኗኗር ዘይቤና ባህል የሚከተሉ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን አቅፋ የምትገኝ አገር ናት።
’’ድር ቢያብር አንበሳ ያስር’’ ወይም ’’ጥርስና ከናፍር ተደጋግፎ ያምር’’ እንዲሉ ልዩ ልዩ ዜጎቿ የአንድነት የኅብር ውበትን አጎናጽፈዋት ’’ብዙ ሆና አንድ አንድ ሆና ብዙ’’ የሚለውን አኩሪ ምስጢር በተግባር ያስመሰከረች አገር መሆኗን የዘመናት ታሪክ ይመሰክሩላታል።
ለኢትዮጵያ አገራቸው መከታ ለወገናቸው አለኝታ የሆኑ ሕዝቦች፣ ቋንቋ፣ ዘር፣ ቀለም ሳይገድባቸው አገራቸው ላይ አይኑን ለሚያቀላ ክንዳቸው የማይዝል ዜጎች፣ ለቅኝ ገዥዎች የማይመቹ ጀግና ሕዝቦች ባለቤት መሆኗን ለማረጋገጥ አንገትን ወደ ኋላ መለስ ደርጎ የዓድዋን ድል እንደ አብነት መመልከት ይቻላል።

ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ልጆቿን በሰላም፣ በፍቅር፣ በመከባበር፣ በመደጋገፍ፣ በአንድነት ዕቅፍ ድግፍ አድርጋ ብዙ ዘመናትን ስለመሻገሯ ታሪክ ያወሳላታል። አሁን ላይ ግን ነገሮች መልካቸውን ቀይረዋል፤ መስመራቸውንም ለቀው እየተንሻፈፉ መጥተዋል።
አገራችን ያሳለፈችውን ያን መልካሙን፣ ልዩነት ያልገደበውን የአንድነት ዘመን እንደ ታሪክ ማውሳት ቢቻል እንጅ በተግባር ለማየት ቢፈለግ እየከበደ እንደመጣ ብዙዎች ይስማሙበታል።

በመልካም ዜና ፈንታ ሐዘን፣ በፍቅር ፈንታ ጥላቻ፣ በአንድነት ፈንታ ልዩነትን፣ በመከባበር ፈንታ መነቃቀፍ፣ እንዲሁም በሠላም ፈንታ ጦርነት ማየትና መስማት በኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ የዘወትር ልምድ እየሆነ መጥቷል።
ለዘመናት በልጆቿ የገነባችው አገራዊ አንድነት እና ፍቅር በዘር ፖለቲካና ሥልጣን ጥቅም ምክንያት እየተናደ ለልብ ሕመም ውጋት ዳርጓት ፈውስ በመሻት አንገቷን ደፍታለች። ለዚህም የልብ ውጋት ሕመሟም አሁን ላይ የሚግበሰበሰው የፖለቲካ አሻጥር አይነተኛ መንስኤ መሆኑ የማይካድ ሐቅ ነው።

ኢትዮጵያ በውጭ ጠላት የተከሰቱባትን ችግሮች የአንበሳውን ቦታ በመያዝ በድል ትወጣለች እንጅ በማንም አንገቷን ደፍታ እንደማታውቅ የታሪክ ምሁራን ሲዘገቡላት ኑረዋል። ዛሬ ላይ አንገቷን ያስደፋት ግን በውጭ ጠላት ሳይሆን በአብራክ ክፋዮቿ የተፈጠረው መከፋፈል ያስከተለው ሕመም ሳይሆን አልቀረም።

አሁን ላይ ቀድሞ በስሩ ሊያደርጋት ሲቋምጥ ድል ያደረገችው የውጭ ኃይል፣ በልጆቸዋ ደካማ ጎን ገብቶ መልኩን በመቀየር በቀሉን ሊወጣ እየተፍገመገመ ስለመሆኑ አስተዋይ አእምሮ የተላበሰ ሰው የሚስተው እውነት አይደለም።
የሆነው ሆነና አሁን ላይ በአገራችን ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሳቢያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ማኅበረሰቦች ከቄያቸው እየተፈናቀሉ ከመሰደዳቸው በዘለለ በግፍ የሚገደሉበት ዘመን ላይ ደርሰናል። የእርስ በእርስ መናቆርን፣ ጦርነትንም ሆነ የጦርነት ወሬ መስማት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጥቷል።

በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ጉዳት እያስከተለ ላለው ለዚህ የፖለቲካ አለመረጋጋት ውስብስብ የፖለቲካ ኣሻጥሮች ሲኖሩ፣ ከእነዚህም መካከል ዋናዋናዎቹን መጥቀስ ይቻላል።
የተለያዩ ፖለቲከኞች ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚያደርጉት ሩጫ፣ በክልል ወሰኖች የሚታዩ የይገባኛል ጥያቄዎች፣ የጠባብ ብሔርተኝነት መንፈስና የተለያዩ የውጭ ኃይሎች የሚጫወቱት አገሪቱን የማዳከም የፖለቲካ አሻጥር ዋናዋናዎቹ ተግዳሮቶች ናቸው።
ሥልጣን ላይ የመውጣት ሩጫን ያነገበውና በኢትዮጵያ ላይ ዓይናቸውን ከሚያቀሉ የውጭ ጠላቶች ጋር እንደተሰለፈ የሚነገርለት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሰሜን ወሎ በተለያዩ አካባቢዎች እያደረሰው የሚገኘው ጥቃት በአብነት ተጠቃሽ ነው።

በሽብርተኝነት የተፈረጀው ይህ የህወሓት ቡድን የመንግሥትን የተናጠል ተኩስ አቁሙ ስምምነት ምክንያት በማድረግ አንሰራርቶ በተለያዩ የአማራና የአፋር ክልል አካባቢዎች ላይ ጥቃት ፈጽሟል። ያደረሰው ጥቃትም በእነዚህ አካባቢ የሚገኙ ማኅበረሰቦች ላይ ለደረሰ ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር፣ ለዜጎች ንብረት መዝረፍና ቤታቸውን ለቀው መፈናቀል መንስዔ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ይጠቁማሉ።

ይህ ቡድን የሚፈጽመውን የጥቃት እንቅስቃሴ በአፋር ክልል አሁን ላይ መመከት የተቻለ ቢሆንም፣ በተለያዩ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ማለትም በአላማጣ፣ በራያ በቆቦ፣ በላሊበላ፣ በሙጃ፣ በአድርቃይ፣ በጋሸና፣ እና በሳንቃ ጥቀቱን መቀጠሉ ይነገራል። ሽብርተኛ ቡድኑ ይህ አልበቃ ብሎት ገፍቶ በመምጣት በወልድያና በመርሳ ተመሳሳይ የጥቃት ድርጊት እያካሄደ መሆኑን አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በቦታዉ ከነበሩ የዓይን እማኞች ማረጋገጥ ችላለች።

የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ህወሓት ጥቃቱን አሁንም ባለማቆሙ ምክንያት ቁጥራቸው በግልጽ ያልታወቀ ነዋሪዎች ለሞት የተዳረጉ ሲሆን፣ በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት ከተቆጣጠራቸውና ጥቃት ከሰነዘረባቸው ከተለያዩ አካባቢዎች ከ300ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በደሴና በኮምቦልቻ ከተማ ተጠግተው እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ለመረዳት ችላለች።

ከተፈናቃዮች መካከል የምትገኘው ስሟ እንዲጠቀስ ያፈለገችው ወጣት የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንዲህ በማለት ትናገራለች፣“በክረምት ልጅ ይዞ መሰደድ በቃሌ ከምገልጸው በላይ ከባድ ነው የሆነብኝ፤ ልጄን አዝየ በምሸሽበት ጊዜ የጦርነቱ ድምጽና የክረምቱ ዝናብ ይፈራረቁብኝ ነበር። እኔ ከኋላችን ለሚተኮሰው ጥይት እራት ከመሆን ባመልጥም መንገድ ላይ ወድቆ የመቅረት ዕድል የገጠማቸውን ሰዎች በዓይኔ አይቻለሁ። እህቴ ነፍሰጡር ነች፤ መሮጥ አትችልም፤ እንዴት እንደሆነች አላውቅም፤ ልጄን በዚህ ሁኔታ አጥብቼ ማሳደግ አልችልም። መንግሥት አስፈላጊውን ዕርምጃ ወስዶ ወደየ ቤታችን እንዲመልሰን እንጠይቃለን።’’

ሌላኛው የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ “በዚህ ጦርነት ምክንያት አባቴን አጥቻለሁ፤ አሁንም ቢሆን ኔትወርክ በመቋረጡ ምክንያት ቀሪ ቤተሰቦቼ በሕይወት ለመኖራቸው ምንም ዋስትና የለኝም። አሁን በደሴ ኃይስኩል ተጠግቼ ነው ያለሁት፤ የመከላከያ ሠራዊቱ ወይ ጠላትን ይመክትልን ካልሆነ መሣሪያዉን ያስረክበን። ሕዝቡ ከአላማጣ ጀምሮ እየተገፋ እዚህ ደርሷል። መከላከያውም ከሕዝቡ ጋር ነው የሚሮጠው፤ መንግሥት ይህን ጉዳይ በጥልቅ ሊመለከተውና መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል’’ ሲል ነው የገለፀው።

ተፈናቃዮቹ አያይዘውም፣ በደሴ የሚገኙ ማኅበረሰቦች የቻሉትን ለመርዳት ቢሞክሩና የከተማ አስተዳደሩ ለተወሰኑ ዜጎች መጠለያ የማዘጋጀት ሥራ ቢሠራም የተፈናቃዮች ቁጥር ብዙ ከመሆኑ አንጻር አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች የክረምቱን ዝናብ እየተፈራረቀባቸው እንዳሉ ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል ሕፃናትን የያዙ እናቶች ተጠቃሽ ናቸው። በመሆኑም የምግብ፣ የልብስና መጠለያ ዕጥረት ስላለ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው በተስፋ እየጠበቁ መሆናቸውን ነው የአዲስ ማለዳ ምንጮች የተናገሩት።
አክለውም በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን በተቆጣጠራቸው አካባቢ የቀሩ ማኅበረሰቦች እስካሁን ምንም አይነት ድጋፍ እየተደረገላቸው ስላልሆነ ግፍ እየተፈጸመባቸው ነውና የመከላከያ ሠራዊቱን አጠናክሮ መንግሥት ካሉበት ችግር ሊያወጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም፣ አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የሰሜን ወሎ ተወላጆችና ከተለያዩ የአካባቢው ቦታዎች ተፈናቅለው የመጡ ዜጎች ጉዳዩን በማስመልከት ነሐሴ 8/2013 በወቅታዊ ሁኔታ ባካሄዱት ውይይት ላይ ለመታደም ችላለች።

የተፈናቀሉ ዜጎች በቂ ድጋፍ እንዳላገኙና በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን በተቆጣጠራቸው ቦታዎች የሚገኙ ማኅበረሰቦች እስካሁን ድረስ በጥቃቱ ሰለባ በመሆናቸው ልንደገፋቸውና ግንባር ድረስ ሒደን ነጻ ልናወጣቸው ይገባል ብለዋል።
ተፈናቀለው በደሴ ከተማ የሚገኙ ከተለያዩ የሰሜን ወሎ አካባቢ የመጡ ማኅበረሰቦች ለመኖር የሚያስፈልጉ መሠረታዊ የሆኑ የምግብ፣ የልብስና የመጠለያ ችግር እንደተጋረጠባቸው ተወያዮቹ ጠቁመዋል።

በተያያዘም በራያ ቆቦ፣ በመቄትና በጋሸና በህወሓት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ዜጎች ምግብ የማዘጋጀት ግዳጅ ስለተጣለባቸው ያላቸውን ንብረት ጨርሰው ለድህነት እንደተጋለጡም ነው አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ማረጋገጥ የቻለችው።
በአሁኑ ሰዓት የገፈቱ ቀማሾች የሆኑት በጉርብትና የሚገኙት የአማራና የአፋር ሕዝቦች ቢሆኑም ነገ ጧት ወደ አዲስ አበባ ላለመምጣታቸው ምንም ዋስትና የለምና የመከላከያ ኃይሉን በማጠናከር መንግሥት ይህን ቡድን የመመከት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል ተወያዮቹ።
ለዚህ ጉዳይ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ኹለም ዜጋ ኃላፊነት አለበት ያሉት ተሰብሳቢዎች፣ በዚህ ዕለት ለድጋፍ የሚሆን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻላቸውንና ግንባር ድረስ ሒደዉ ለመሰለፍ ዝግጁ መሆናቸዉንም ገልጸዋል።

በህወሓት የተከፈተውን የጥቃት ዘመቻ የመመከት ኃላፊነቱ ለአማራ ሕዝብ ብቻ የተጣለ ግዳጅ ነው የሚመስለው ያሉት ተሳታፊዎቹ፣ አገር የሚገነባው በጋራ ነውና መንግሥትም የድርሻውን በመወጣት ሊያግዘን ይገባል፤ በዚህም ኢትዮጵያን እንታደጋት በማለት ገልጸዋል።
በስብሠባቸው ማጠቃለያም ለተቸገሩት በመድረስ የድርሻችንን እንወጣለን በማለት ኮሚቴዎችን በማዋቀር የአቋም መግለጫቸውን አስቀምጠዋል።

በሽብርተኝነት የተፈረጀው የትህነግ ቡድን መንግሥት የወሰነውን የተናጠል ተኩስ አቁምና የጥሞና ጊዜ ወደ ጎን በመተው በተለያዩ የወሎ አካባቢዎች የሚያደርገውን የግድያና የዝርፊያ ተግባሩን በጥብቅ እናወግዛለን፤ ያቆምም ዘንድ እንጠይቃለን ብለዋል።
የአሸባሪው ቡድን ተጨማሪ አደጋ ሳያደርሰና ሌሎች አካባቢዎን ከመውረሩ በፊት መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች እንዲያስወጣልን እየጠየቅን፣ እኛ በአዲስ አበባ የምንኖር የወሎ ተወላጆች በገንዘብ፣ በእውቀትና ግንባር ድረስ ሒዶ በመዋጋት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአማራ ሕዝብ ላይ ጥቃት እየሰነዘረ የሚገኘውን ቡድን ለመመከት ዝግጁ መገሆናችንን እናረጋግጣለን ሲሉም ፍላጎታቸውን አሳውቀዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አጎራባች ከተሞች ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በአዲስ አበባና በውጭ አገር ከሚኖሩ ተወላጆች ገንዘብ በማሰባሰብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል እንገባለን በማለትም አቋማቸውን አሳውቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here