በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ችግር ላይ መሆናቸውን ገለጹ

በጸጥታ ችግር ምክንያት ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው አዲስ አበባ የሚገኙ የመቐለ፣ አክሱም፣ የዓዲግራት እና ራያ ዩኒቨርስቲ መምህራን ከኹለት እስከ ሦስት ወር ደሞዝ ባለመከፈላቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ገለጹ።
በአራቱ ዩኒቨርስቲዎች ሲያስተምሩ የነበሩት መምህራን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የደሞዝ ክፍያው የተዛባው ከጥቅምት 2013 ጀምሮ ቢሆንም፣ በመሀል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ተወካዮች በኩል ክፍያ ተፈጽሞ ነበር ብለዋል።

ነገር ግን ይላሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ከግንቦት ወር ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች የሦስት ወር ደሞዝ እንዳልተከፈላቸውና ባንክ ላይ ያላቸውን ገንዘብ አውጥተው እንዳይጠቀሙ የባንክ አካውንታቸው መታገዱን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም መምህራኑ የሚሠሩባቸው ዩኒቨርስቲዎች በሚገኙበት አካባቢ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ዝውውር ቢጠይቁም ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን ተናግረዋል።

የወር ደሞዛቸውን ጠብቀው የዕለት ጉርስ የሚያገኙ እና ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ የዩኒቨርስቲ መምህራን መኖራቸውንም ለአዲስ ማለዳ የደረሰው ቅሬታ ያሳያል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ከሆነ ከጥቅምት ጀምሮ የነበረው ደሞዝ በወቅቱ ካለመድረሱ ባሻገር የደህንነት ስጋት ውስጥ እንደቆዩ ይገልጻሉ።

ነገር ግን የመምህርነትና አገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በቦታው የቆዩት ከ400 የሚበልጡ መምህራን የማስተማር ኃላፊነታቸውን ተወጥተው መከላከያ አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በተከሰተው የደህንነት ስጋት ምክንያት አካባቢውን ለቀው ቢወጡም፣ ያገለገሉበትን ክፍያ ግን ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

የተለያዩ መምህራን ተደራጅተው ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት የደሞዝ ጥያቄ በደብዳቤ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩም ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ባንክ እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ገልጾላቸው ነበር።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን ቢገልጽም፣ ይህ ዜና እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ደሞዛቸው እንዳልተከፈላቸውና የአብዛኞቹ መምህራን የባንክ አካውንት እንዳልተለቀቀላቸው ነው ቅሬታ አቅራቢዎቹ የገለጹት።

ቅሬታቸውን ካቀረቡት በርካታ መምህራን መካከል ስድስት የሚሆኑት በአራቱም ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩ መምህራን ለአዲስ ማለዳ ድምጻቸውን አሰምተዋል። ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው ያልተጠቀሰ ሲሆን፣ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች መንግሥት በአፋጣኝ እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

መከላከያ ሰኔ 21 ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት ሰኔ 19 ነው ከተማውን ለቅቄ የወጣሁት ያሉ አንዱ ቅሬታ አቅራቢ፣ “ በክልሉ ያሉ ዩንቨርስቲዎች ላይ በቀጣይ ለማስተማር ከፍተኛ ስጋት አለብን›› ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹ሌላ ዩኒቨርስቲ ለማስተማር ዕድሉን ባገኝም አሁን ከማስተምርበት ዩኒቨርስቲ መልቀቂያ ማምጣት ስለሚያስፈልግ ሌላ አማራጭ ሥራ መሥራት አልቻልኩም፤ መልቀቂያ ማምጣት በክልሉ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ የማይታሰብ ነው›› ሲሉ ቅሬታ አቅራቢው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በአራቱም ዩኒቨርስቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች በሰላም የተመለሱ ሲሆን፣ ተመራቂ ተማሪዎችንም ለማስመረቅ ሁኔታዎችን እያመቻቸ እንደሚገኝ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ነሐሴ 7፤2013 አስታውቋል።

መቐለ ዩኒቨርስቲ ሲሠራ የነበረ እና እስከ አሁን የደረሰበት የማይታወቅ መምህር መኖሩንም ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ለማወቅ ተችሏል። ተማሪዎች ገብተዋል ኮርስ መያዝ አለባችሁ ተብለው በድጋሚ የሔዱ መምህራን የነበሩ ሲሆን፣ በጦርነቱ ምክንያት ቀድመው ወደ ቤታቸው የተመለሱ ቢኖሩም እዛው የቆዩ መምህራን እንደሚገኙም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።

መቐለ ከሚገኙት መምህራን ይልቅ ወደ የቤታቸው የተመለሱት ኑሮ በአንጻራዊ እንደሚሻል የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ ክልሉ ላይ ሕይወታቸውን እየቀጠሉ ያሉት የበለጠ እየተጎዱ ነው ሲሉ ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here