አገር በአጣብቂኝ ውስጥ ስትሆን እንደተቸገረ ሰው ወዳጅና አጋዥ መፈለግ የተለመደ ነው። ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን የመንግሥትነት ቆይታዋ ከኃያላን ተርታ ተሰልፋም ሆነ እንዳሁኑ ችግር በሚደቁሳት ወቅት ውጭ ውጭ ስታይ ኖራለች። የቅርቦቹን እንኳን ብንጠቅስ ሁል ጊዜ ዕርዳታ ፍለጋ ብቻ ሳይሆን ሌላ ሩቅ ያለን ለማገዝም ወዳጅ ስታበጅ ኖራለች። የአፄ ካሌብ ዘመን የየመን ዘመቻችን የዚህ የወዳጅነት ትሩፋት መሆኑም አይዘነጋም። በ16ተኛው ክፍለ ዘመን የዐረብ አገራትን ማየልና እርስበርሳቸው የሚያደርጉትን መተጋገዝ በማየት በአፄ ልብነድንግል እናትና አያት አሳሳቢነት አገራችን ከፖርቱጋል ጋር እንድትወዳጅ የተደረገው ጥረት የሚዘነጋ አይደለም። ይህን ወዳጅነት ተመልክተው የወቅቱ ኃያላን በነበረችው በኦቶማን ቱርክ የሚመሩ አገራት የራሳቸውን ወዳጅነት ከኢትዮጵያውያን አማፄያን ጋር መሥርተው አገሪቱ እንድትከፈል የተደረገበት አጋጣሚ የፈጠረውን ውድመት ታሪክ የሚያውቀው ነው።
ፖርቱጋል በተፈለገችበት ወቅት ሳይሆን ብዙ ጥፋት ከደረሰ በኋላ ማገዟ ቢጠቀስም፣ ወዳጅ ናት ተብሎ ከመጣብን ጥፋት አንፃር የነበረውን ጠቀሜታ የሚተቹት አሉ። በቱርክ አማካይነት ገብቶ የነበረው ዘመናዊ ተተኳሽ የጦር መሣሪያ ሚዛናዊነትን አጥፍቶ ስለነበር የፖርቱጋሎች መኖር የእርስበርሱን ውጊያ ተመጣጣኝ እንዲሆን ማድረጉን የሚያስረዱ አሉ። ቱርክ ከእርስበርሱ ጦርነት ብዙ ያተረፈችው ቢኖርም፣ የላከቻቸው ነፍጠኞችዋ እንደፈለግን ካላዘዝን ብለው ከኢትዮጵያኑ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ተቋርጦ ነበር። ጎራ ለይተው ሊያግዙ የመጡት ኹለቱም ወገኖች በየተራ ተባረው አገሪቷ ከነጥፋትዋና ውድመቷ ቀርታ ነበር።
ከዛን ጊዜ ጀምሮ ከጥፋታችን ሳንማር፣ የውጭ አገራትንም ድብቅ ፍላጎት መረዳት ተስኖን እስካሁን ወዳጅ አገርና ቡድን እያቀያየርን መተላለቃችንን ቀጥለናል። ማንም አገር ለራሱ የሚጠቅመውን ካልሆነ በቀር የራሱን ፍላጎት ትቶ የማንንም እንደማያስቀድም አሁንም የተረዳን አይመስልም። “እከክልኝ ልከክልህ” በሚል ዕሳቤ ወይም “ኹሉም አሸናፊ የሚሆንበት” እየተባለ ሥምምነት ቢደረግም፣ በተግባር ግን ተጠቃሚው ሌላው ወገን ሲሆን መታየቱ የተለመደ ነው። ኢትዮጵያ እንደማንኛውም አገር ራሷን ኃያል አድርጋ ባትመለከትም፣ ከእነሱ ያነሰ መብትን መጠበቅና መጠየቅ እንደሌለባት የአዲስ ማለዳ ዕምነት ነው።
ከሦስት አመት በፊትየኢትዮጵያ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ፖለቲካ ሲቀየር ወዳጅ አገራትንም የቀየረ ሒደት ተስተውሎ ነበር። ለውጡ ብዙዎችን ግራ ያጋባ የመሆኑን ያህል ያመጣውን ውጤት ለመገምገም ጊዜው አጭር ቢሆንም፣ ጥቂት የማይባሉ ያልተሳኩ ሙከራዎች የተደረጉበት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የፈረንሳይና ኢትዮጵያን ሥምምነት በተመለከተ የጦር ቃል-ኪዳን ፈረሙ ተብሎ ለያዥ ለገናዥ እስኪያስቸግሩ የመንግሥት ደጋፊዎች ተቃዋሚዎችን አፍ ለማሲያዝ ሲሞክሩ ነበር።
በሠላሙ ጊዜ ወዳጅ ነን እያሉ ለመንግሥት የፈረሙ አገሮች በርካታ ቢሆኑም፣ ዐረብ አገራትንና ምዕራባውያኑን በቀዳሚነት መጥቀስ ይቻላል። በእነዚህ ሥምምነቶች ምክንያት አገራቱ በአባይ ግድብ ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ፣ እንዲሁም መሬት እየተሰጣቸው ያለምንም ጨረታ በዋናዋ ከተማ ጭምር እንዲጠቀሙ ሲደረግ ነበር። ይህ ጥቅማቸው ሳይቋረጥባቸው፣ እነሱ ግን ሌላ ጥቅም በመፈለግ ብቻ ሳይሆን ሌላ ወዳጃቸውን ላለማስከፋት ይበልጡብናል ብለው በክፉ ጊዜያችን ሲከዱን ተስተውሏል።
ምዕራባውያኑ ያለእኛ ፈቃድ ያላዘዝናችሁ ጋር ውጊያ ገባችሁ በሚል አስተሳሰብ፣ በክፉም በደጉም እንደጋገፍ ተብሎ የተፈረመውን ውል ትተው ርቀዋል። በተለይ አንዳንድ የዐረብ አገራት ደግሞ ከግድቡ ጋር በተገናኘ በጀርባችን ለማሴር እንኳን ሳይፈሩ በግላጭ ተሰብስበው ለማውገዝና ጫና ለማሳደር ተነስተዋል።
ወዳጅ መመስረት ተገቢ መሆኑን የምታምነው አዲስ ማለዳ፣ በፍትሐዊነት ላይ የተመሰረተ ካልሆነ ግን እንደማይዘልቅ ብቻ ሳይሆን ጎጂ ሊሆን እንደሚችል ማስገንዘብ ትወዳለች። በ1970ዎቹ ከሱማሊያ ወግና የጦር ሠፈር ገንብታላት የምታውቀውን ትታ ጓዳ ጎድጓዳዋን ኹሉ ለኢትዮጵያ ወዲያው ገልብጣ ከሰጠችው ራሺያ መማር ይገባናል። አሜሪካም ብትሆን ከኢትዮጵያ ጎን ለብዙ ዘመናት ቆማ ወዳጅ ነኝ እያለች ከነበረችበት፣ ጠላቴ የምትላትን ሱማሊያን ለማገዝና ለማስታጠቅ ጊዜ አልፈጀባትም ነበር። ኹለቱ አገራት ቀዝቃዛ ባሉት ጦርነት ዜጎቻቸውን ሳያስገድሉ እርስ በርስ ባላቸው የውስጥ ስምምነት ወዳጅ ብሎ የተጠጋቸውን ሲያጫርሱ ኖረዋል፤ አሁንም እያደረጉት ይገኛሉ።
አፍጋኒስታን የኃያላን መጫወጫ ሜዳ ሆና ያየችው ፍዳ፣ ለወደፊትም የሚያሳይዋት መከራ፣ ለሚሠሩት ሥራና ለክህደታቸው በቂ ማስረጃ ነው። ከትልቁ አሌክሳንደር ጀምሮ በወራሪ እየተደቆሰች አንዱን አስተናግዳ ሳትጨርስ ሌላው መጥቶ የሚገዛት ይህች አገር፣ የተቆረቆረችበት ቦታ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ዜጎቿ አንዱን ደግፈው በሌላው ላይ የመነሳት ባህሪን ስለሚያዘወትሩ ራሷን ችላ ለመቆም ሳይቻላት ኖሯል። የአውሮፓውያንን፣ ቻይናን፣ የዐረቡ ዓለምን፣ እንዲሁም የቅርብ ኃያላንን መስፋፋት ስትዋጋ የኖረችው ይህች ምስኪን አገር፣ የተገባላት ቃል ኪዳን እየተተወ፣ የፈረመችው ስምምነት እየተጣሰ ባዶ ሜዳ ላይ እየተተወች ስትቸገር ማየት የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም።
አሜሪካ በአፍሪካ፣ ቬትናምን በመሳሰሉ የእስያ አገራት፣ እንዲሁም በመካከለኛውና ደቡብ አሜሪካ አገራት በተመሳሳይ የወዳጅነት ውል እየፈረመች ጉድ የሠራቻቸው በርካቶች እንደሆኑ የታሪክ ምሁራን ያነሳሉ። ተቀናቃኞቿ እነራሺያ ደግሞ ሶሻሊዝም በሚል ሽፋን እየገቡ፣ ወንድም አገር ሌላን አያጠቃም እያሉ ለመተጋገዝ ምለው ባዶ ማስቀረታቸውን የምስራቅ አፍሪካ፣ የእስያና የምስራቅ አውሮፓ አገሮች ተሞክሮ ይመሰክራል። ቻይና እንደተለመዱትና እየተፈራረሙ እንደሚክዱት ስለመሆኗ፣ ኃይል ሆነች የተባለችበት ዘመን አጭር እንደመሆኑ በቂ ማስረጃ ማቅረብ ቢያስቸግርም፣ በንግዱ ዘርፍ እንደምታደርገው ጠላት ለሆኑ ኹሉ ወዳጅ ሆና ጥቅሟ እስካልቀረ ቢጨራረሱም ደንታ እንደሌላት የሚናገሩ አሉ።
ያም ሆነ ይህ ከአገራት ጋር የሚደረግ ውል ብቻ ሳይሆን ከዓለም ዐቀፍ ተቋም አባል ሆኖ የሚጠበቅ የሥምምነት ተግባርም ውጤት ሳያመጣልን፣ እንደውም ሲጎዳን ተስተውሏል። በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል ለመሆን ተብሎ፣ ለዘመናት ያቆየን ሕግ ተሸቀንጥሮ በአዲስ ተተክቶ፣ እነሱ ያሉት እንዲሟላ በተለይ የጣሊያን ተቃዋሚነትን ተቋቁመን ብንሞክርም አባል መሆን ተችሎ እኩል መሆን ግን አልተቻለም ነበር። ራሷ ጣሊያን የቻይናዋን ማንቹሪያንንና ኢትዮጵያን ስትወር የሙሶሎኒን ቁጣ ማስታገሻ ብለው ራሳቸው ላይ እስኪመጣ ዝም ካሉበት ታሪክ መማር እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ለአድዋ ጦርነት መንስኤ የሆነው የውጫሌው ውል እንደሆነ ይታወቃል። ውሉ ባይፈረም እንደአገር የሚያስፈልጉንን ጥቅሞች ልናጣ ብንችልም፣ ያስከተለብንን መዘዝ ላስተዋለ ግን ያለ ስምምነት እንደተራ ገበያተኛ ብንሞክር ይሻለን ነበር የሚሉ በርካቶች ናቸው። ወዳጅ እንሁን ብለን እኛ ባንጠይቃቸውም፣ የጦር ቃል ኪዳን በማድረጋችን እውነተኛውን ውስጣችንን እንዲያውቁ ያደርጋቸዋል። ይህ እንዲንቁን ከማድረጉ ባሻገር በራስ መተማመናችን እንዲቀንስ፣ እንዲሁም ሕዝቡ ያለእነሱ እገዛ ምንም ማድረግ እንደማይችል በማሰብ በሥነ-ልቦናው ጦርነት እንዲያሸንፉት በር እንከፍታለን። ጣሊያን ለኹለተኛ ጊዜ ስትወረን ቶሎ ያላሸነፍናት ሌሎቹ ምዕራባውያን ያግዙናል በሚል ባዶ ተስፋ፣ እንዲሁም አንችላቸውም በሚል እነሱን አግዝፎ በማየት የተፈጠረ እንደሆነ ይነገራል።
ያም ሆነ ይህ፣ ከውጭ አገራት በተለይም ከኃያላን ጋር የሚደረግ ቃልኪዳን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። አፄ ምኒልክ ለልጅ እያሱ ቃል አስገብተውት ነበር እንደሚባለው፣ የቅኝ ግዛት ሕልም የሌላቸው ጫናቸውንና ተፅዕኗቸውን ለማሳደር ከማይፈልጉ ጋር መወዳጀቱ ሳይሻል አይቀርም። ስዊዘርላንድን ከመሳሰሉ በገለልተኛነታቸው ከተመሰከረላቸው አገራት፣ አሊያም ከመሰሎቻችን ጋር አብረን በምንፈጥረው ሕብረት በራስ መተማመናችንን ብናዳብር እንደሚሻል አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ኢትዮጵያ ላለፉት 500 ዓመታት በየ40 ዓመት ጦርነት ተለይቷት እንደማያውቅ ታሪክ አዋቂዎች ያስረዳሉ። ከቅርቡ ብንጀምር ከ2008 ወዲህ እስካሁን ያለው፤ በ1968 የጀመረው የሶማሊያ ወረራ፤ በ1928 የተደገመው የጣሊያን ወረራ፤ ከ40 ዓመት በፊት በ1988 የነበረው የአድዋው ጦርነት፣ እንዲሁም ከእዛ በፊት የተነሱ ጦርነቶችና የእርስ በርስ ግጭቶች ብዙ ሰው ጨርሰዋል፤ በርካታ ውድመትም አስከትለዋል። ኹሉም ማለት በሚቻል መልኩ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን አስተናግደዋል። በፈጣሪ የሚተማመኑ መንስዔውን ሲናገሩ፣ እስከዛሬ ጠብቆ ባቆየን ፈጣሪ መተማመንን ትተን በሌላ ፍጡር ወይም በጦር መሳሪያ መመካት ስለጀመርን ነው ይላሉ። በሌላ በኩል፣ የእኛ መለያየትንና የኃያላኑን ስግብግብነት በማንሳት ኋላ ቀርነታችንን ምክንያት የሚያደርጉም አሉ።
መንግሥት የትኛውንም ምክንያት ይቀበል፣ አሁን ቱርክ ሔዶ የሚያካሂደውን አይነት የጦር ቃልኪዳንም ሆነ ሥምምነት ቆም ብሎ ሊያስብበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች። የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል እንደሚባለው፣ ከሌሎች አገራት ጋር አስሬ ከምንማማል ራሳችንን ችለን እንድንጓዝ ወንዝም ቢገጥመን እንድንሻገር የሚያስችለን የራስ ዝግጅት ብናደርግ መልካም ነው።
ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013



