አዲስ የተሻሻለው የታሪፍ ደንብ የወታደራዊ (ሚሊተሪ) ከባድ የጦር መሣሪያዎችን ማለትም እንደ ጠመንጃ፣ ሮኬት፣ ላውንቸር እና እሳት የሚተፉ መሣሪያዎችን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የሚፈቅድ መሆኑ ተገለጸ።
የአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል እና የክልል ፖሊስ ተቋሞች፣ የሕዝብ ደሕንነት ተቋሞች ወደ አገር የሚያስገቧቸዉ የመከላከያና የሕዝብ ደህንነት መሣሪያዎች፣ ለነዚሁ አገልግሎት የሚዉሉ ክፍሎችና እና ቁሳቁሶች (አክሰሰሪዎች) በነጻ እንዲገቡ ማሻሻያው ይፈቅዳል።
አገሪቱ አሁን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት መሣሪያ ወደአገር የማስገባት ፍላጎት አለ። የጦር መሣሪያዎች እና ሽጉጦች ከ5 እስከ 10 በመቶ ቀረጥ ይጣልባቸው የነበረውን መመሪያ በማሻሻል በነጻ እንዲገቡ የሚያደርግ መሆኑንም ማሻሻያው አመላክቷል።
የሌሎች የጦር መሣሪያዎችና የእጅ ቦንቦች፣ የሚቀበሩ ፈንጂዎች እና ባለቀላህ ጥይቶቸ ደግሞ እስከ 35 በመቶ ቀረጥ ተጥሎባቸው ነበር፡
መመሪያዎች ሲሻሻሉ የራሳቸው የሆነ መንገድ አላቸው የሚሉት የሕግ አገልግሎት አማካሪው ሳሙኤል ግርማ፣ በዋናነት የአገሪቱን የወጪ ንግድ በተመለከተ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎችን በተመለከተ የጉምሩክ ቀረጥ በመክፈል የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ እየታየ ከፍ ዝቅ ይደረጋል ብለዋል።
ከኹለት ዓመት በኋላ ማሻሻያ የተደረገበት ይህ የታሪፍ ደንብ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ የሚጣለውን ቀረጥ የአለም ገበያን ያገናዘበ ለማድረግ የታሰበ መሆኑ ሳሙኤል ጠቁመዋል።
የተለያዩ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ዝርዝር የያዘው ባለ 357 ገጽ አዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ፣ ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ ምርቶችን እንዲኖሩ ተደርጎበታል። ከዚህ በፊት ቀረጥ ይጣልባቸው የነበሩት መሠረታዊ ዕቃዎች በነጻ መግባት የሚችሉበትን አማራጭንም አዘጋጅቷል።
የተለያዩ እንስሳት ቆዳ ወደ አገር ውስጥ በነጻ እንዲገቡ የሚያደርገው ማሻሻያው፣ የለፋ ቆዳ ደግሞ እስከ 25 በመቶ እንደሚቀረጥ ይገልጻል ። ከ90 በላይ ወደ አገር የሚገቡ ምርቶች ላይ የገቢ ቀረጥ የተስተካከለ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ባሉበት የቀጠሉ እና የቀነሱ ምርቶች ተጠቅሰዋል።
ያልተሰራ እንጨት፣ጭራሮ እና ግንድ በነጻ የሚገቡ ሲሆን፣ ቅርጽና መጠን ተሰርቶላቸው የሚገቡ የእንጨት ምርቶች ከ15 እስከ 35 በመቶ ቀረጥ ተጥሎባቸዋል።
ምርቶች ቀረጥ የሚጣልባቸው ባላቸው ዓለም ዐቀፍ ገበያ ዋጋ መሠረት ሲሆን፣ የመጓጓዣ እና ሌሎች ወጪዎችን ታሳቢ ተደርጎ የቀረጥ መጠናቸው ከፍና ዝቅ እንደሚል ሳሙኤል ነግረውናል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የቅንጦት ዕቃዎች ላይ የሚጥለው የቀረጥ መጠን ከፍ እንደሚል የሚታወቅ ሲሆን፣ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ላይ ተመጣጣኝ የሆነ ቀረጥ ይጥላል ሲሉ ሳሙኤል ገልጸዋል።
የገቢ ቀረጥ የሚሻሻለው በዋናነት የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ከማሰብ መሆኑን ያነሱት ሳሙኤል፣ በተለያየ መንገድ የሚከፈሉ ክፍያዎችን ታሳቢ በማድረግ የተቀነሱ መኖራቸውን ሳሙኤል ጠቁመዋል።
ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ ከገቢ ቀረጥ ውጭ ኤክሳይስ ታክስ፣ እንዲሁም የመጓጓዣ ወጪዎች ስለሚኖሩ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉ ሳሙኤል ተናግረዋል።
የኑሮ ውድነት፣ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ እና የዶላር እጥረት መኖሩ የቀረጥ ገቢ እንዲሻሻል ምክንያት ናቸው ተብሏል።
የሰዎችን ማኅበራዊ ሕይወት ያቃውሳል ከሚባሉ ምርቶች መካከል በሆኑት መጠጥና ሲጋራ ላይ እጅግ የተጋነነ የቀረጥ ገቢ እንዲጨምር ይደረጋል የሚሉት ሳሙኤል፣ ምክንያቱ ደግሞ የማኅረሰብን ጤና ለመጠበቅ ሲባል መሆኑን ገልጸዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013



