የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የ2014 ዓመታዊ የግዥ ዕቅዳቸው በኤሌክትሮኒክ (ኢ-ጂፒ ሲስተም) አስከ ነሐሴ 30/2013 ለሕዝብ እንዲያሳውቁ የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አሥተዳደር ኤጀንሲ ማሳሰቢያ ሰጠ።
የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሰጠኝ ገላን፣ የፌደራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በሙሉ ከወረቀት ነጻ የሆነ ግዢ ሥርዓት ለመፈጸም የ2014 ዓመታዊ የግዥ ዕቅዳቸውን በኤሌክትሮኒክ (ኢ-ጂፒ ሲስተም) የግዥ ሥርዓቱን በመጠቀም እስከ ነሐሴ 30/2013 ድረስ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
የ2014 ዓመታዊ ዕቅዳቸውን በኤሌክትሮኒክ (ኢ-ጂፒሲስተም) በተያዘለት የጊዜ ገደብ የማያሳውቁ መሥሪያ ቤቶች፣ በገንዘብ ሚኒስቴር የሚበጀተው ዓመታዊው በጀት እንደማይለቀቅ፣ በመንግሥት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አማካይነት በሚገዛው የማዕቀፍ ግዥ ተጠቃሚ እንደማይሆኑ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የፌደራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በ2014 በጀት ዓመት ለሥራ ያስፈልጋሉ ብለው ያቀዷቸውን የመሥሪያ ቤቶቹን የጋራ መገልገያዎች፣ ኮምፒዩተሮች፣ ወረቀት፣ የጽዳት ዕቃዎች፣ ተሸከርካሪዎች እና የሚያስፈልጉ የጥገና ዕቅዶችን በኤሌክትሮኒክ (ኢ-ጂፒሲስተም) በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይፋ ማድረጋቸው መንግሥት ከበጀተው ዓመታዊ በጀት ውስጥ ምን ያህሉ ለግዥ እንደሚውል ቀድሞ ለማወቅ ያስችላል፤ በየመሥሪያ ቤቶች አገልግሎት ላይ የሚውሉ መገልገያዎችን ለማወቅ እንዲሁም የግል ባለሀብቶችን ለማበረታታት እና ዝግጅት እንዲያደርጉ ለማድረግ ያጠቅማል ብለዋል።
የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት(ኢ-ጂፒ ሲስተም) በዘጠኝ የመንግሥት ተቋማት ማለትም፤ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ መድኃኒትና ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ፣ በመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ በገቢዎች ሚኒስቴር ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም በመንግሥት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለሙከራ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ በ2014 በጀት ዓመት ሙሉ ግዥያቸውን በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት የሚፈጽሙ እንደሆነ ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓቱን(ኢ-ጂፒ ሲስተም) ለሙከራ ተግባራዊ ካደረጉ ዘጠኝ ተቋማት በተጨማሪ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የፌደራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የ2014 ዓመታዊ ዕቅዳቸውን የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓትን በመጠቀም እስከ ነሐሴ 30 ማሳወቅ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም የፌደራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ዓመታዊ የግዥ ዕቅዳቸው፣ የጨረታ ማስታወቂያ እና የጨረታ ውጤት በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ እና ማስታወቂዎችን በጋዜጣ በማውጣት የሚሠራ በወረቀት ላይ የተመሠረተ አሠራር እንደነበር ጠቅሰዋል።
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እየሠሩበት የሚገኘው የቀድሞ የግዥ ዕቅድ አዘገጃጀት እና የአቀራረብ አሠራር የሚቀጥል ሲሆን፣ ከስድሰት ወራት በኋላ 50 የፌደራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ዓመታዊ ግዥያቸውን በኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት(ኢ-ጂፒ ሲስተም) እንዲፈጽሙ ይደረጋል። በቀጣይ ኹለት ዓመት ውስጥ ጠቅላላ 187 የፌደራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችን በኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ውስጥ ለማስገባት በዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል።
አዲሱ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት(ኢ-ጂፒ ሲስተም) ከሌሎች የግል እና የመንግሥት ተቋማት ጋር ቁርኝት የሚኖረው ሲሆን፣ በባንክ በኩል ገንዘብ ዝውውር እንደሚደረግ እና በገንዘብ ሚኒስቴር የገንዘብ ማጣሪያ እንዲሁም ከገቢዎች እና ጉምሩክ ጋር በታክስ ዙሪያ ግንኘነት እንደሚኖረው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013



