በመዲናዋ ሕገ-ወጥና የሌብነት ተግባርን ለሚያጋልጡ ሰዎች የማበረታቻ ሥርዓት ተዘረጋ

0
647

በአዲስ አበባ ከተማ በስፋት የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥነት እና የሌብነት ተግባርን ለማጥፋት በተደራጁ ሌቦች ላይ ተገቢው ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከነዋሪው ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እና እነዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ፈጻሚ ሌቦችን የሚያጋልጥ የከተማው ነዋሪ ሊያበረታታ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል አስፈላጊ በመሆኑ የከተማው ካቢኔ “ሕገ-ወጥነትን ለሚጠቁሙ መረጃ አቅራቢዎች ስለሚሰጥ ማበረታቻ ደንብ” አውጥቷል።
ደንቡ ከለያቸው ዋና ዋና ሕገ-ወጥ ተግባራት መካከል የመሬት ወረራ፣ በመሬት ባንክ ተይዘው የነበሩ ይዞታዎችን ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንዲወጣባቸው ማድረግ፣ ሕገ-ወጥ ግንባታ፣ የአርሶ አደር ይዞታዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ለማይገባው ሰው መስጠት፣ አላግባብ የመንግሥት ቤቶችን፣ ሼዶችን፣ አረንጓዴ ቦታዎች እና ሌሎች ማንቸውንም የመንግሥት ይዞታዎች ወደ ግለሰብ ማዞር ዋናዋናዎቹ መሆናቸው ተጠቅሷል።
እንዲሁም በመሬት፣ በመሬት ነክ እና በማናቸውም የከተማው አስተዳደር አካላት ላይ የተመደበ ኃላፊ ወይም ሠራተኛ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የመንግሥት አግልግሎቶችን በገንዘብ መሸጥ፣ ጉቦ እና መማለጃ መቀበል በግልጽ ባለቤት ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ተገንብተው ያሉ ሕንጻዎች እና ታጥረው የተያዙ ባዶ ቦታዎችን ይዞ መገኘት፣ በስም ዝውውር መክፈል የሚገባውን የአሹራ፣ የቴምብር ቀረጥ፣ እና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ቀንሶ ማስከፍል ተጠቃሽ ናቸው።
በተጨማሪም መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎችን በመደበኛ የንግድ መስመር እንዳይሸጥ መደበቅ፣ ማገድ ወይም መያዝ፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ማዘዋወር፣ በሕገ-ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሬ ማዘዋወር፣ የአገር ውስጥ እና የውጭ ገንዘቦችን በማተምና በማሰራጨት የማጭበርበር ወይም የማታለል ተግባር መፈፀም፣ ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት አገልግሎት መቀበልና መስጠት እና ሌሎች በወጣው ደንብ የተዘረዘሩ መሆኗቸው ታውቋል።
በዚህ መሠረት ማበረታቻውም ተጨባጭ መረጃ ያስገኘውን ውጤት መሠረት በማድረግ በገንዘብ የሚሰጥ ይሆናል ተብሏል። ጥቆማ ያለው ማንኛውም መረጃ አቅራቢም በነጻ የስልክ መስመር 9977፣ በአካል ከንቲባ ጽ/ቤት 4ኛ ፎቅ በመምጣት፣ በኢሜል [email protected] ላይ ጥቆማውን ማድረስ እንደሚችል ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት የተገኘው መረጃ ያጠቁማል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here