ለህወሓት እና ሸኔ ቡድኖች ድጋፍ በማድረግ ወንጀል በተጠረጠሩ 15 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

0
508

በሐረሪ ክልል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁትን ለህወሓት እና ሸኔ ቡድኖች ድጋፍ በማድረግ ወንጀል በተጠረጠሩ 15 ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱን የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዋና አቃቤ ህግ አዩብ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁትን ህወሓት እና ሸኔን በክልሉ የሚደግፉ ግለሰቦችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከህብረተሰቡ እና ጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በዚህም በክልሉ ለቡድኖቹ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርጉ እና ለጥፋት የሚያነሳሱ ግለሰቦች እና ድርጅቶችን በመቆጣጠር የምርመራና ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ ክስ የመመስረት ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

አሁን ላይ ሽብርተኞችን በመደገፍ እና የሽብር ወንጀል በመፈጸም ወንጀል በተጠረጠሩ 15 ግለሰቦች ላይ ክስ እንደተመሰረተ ነው አዩብ ያስታወቁት። በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው ተጠርቶ ከወንጀሉ ነፃ ሆነው የተለቀቁ ግለሰቦች እንዳሉም አመላክተዋል።

እንዲሁም ሰባት ድርጅቶች ታሽገው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ባለንብረቶቹ ለጊዜው ቢሰወሩም 11 ተሽከርካሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ሽብርተኞችን በማንኛውም መልኩ በመደገፍ የሀገርን ሰላም ለመንሳት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ድርጅቶችን ተከታትሎ ለህግ የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here