በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የገበያ እድገት እና እየጨመረ የመጣውን የገበያ ፍላጎት ታሳቢ ያደረገው 4ኛው የአግሮፉድ እና የፕላስቲክ ህትመት ማሸጊያ የንግድ ትርዒት ከጥቅምት 4 እስከ 6 2014 ድረስ በስካይ ላይት ሆቴል እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የንግድ ትርዒቱ በጀርመኑ የንግድ ትርዒት አዘጋጅ ፌር ትሬድ እና በኢትየጵያው ፕራና ኢቨንትስ የጋራ ትብብር የሚካሄድ ሲሆን፤ አጠቃላይ የእሴት ሰንሰለቱን የሚወክሉ ዓለም ዓቀፍ ኩባንያዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑበትም አዘጋጆቹ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ አስታዉቀዋል።
ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ዓለም ዓቀፍ የዘርፉ መሪዎች የግብርና፣ የምግብ እና መጠጥ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂ ግብዓቶችን፣ የፕላስቲክ ህትመት እና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎችና መፍትሄዎችን ይዘው በትርዒቱ ላይ እንደሚቀርቡ ይጠበቃል ሲሉ የፕራና ኢቨንትስ መስራች እና ዋና ዳይሬክተር ነብዩ ለማ በመድረኩ ተናግረዋል።
የፌር ትሬድ መሴ መስራች እና ማኔጂንግ ፓርትነር ማርቲን ማርዝ በበኩላቸው፣ የንግድ ትርዒቱ ተሳታፊዎች ሰፊውን የእሴት ሰንሰለት በመወከላቸዉ በጣም ኮርተናል ያሉ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በተዘጋጁ ሶስት የንግድ ትርዒቶች ላይ አመርቂ የሚባል ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በትርዒቱ ላይም ከ11 ሀገራት ማለትም ከኢትዮጵያ፣ ከፈርንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከህንድ፣ ከጣሊያን፣ ከኩዌት፣ ከናይጄሪያ፣ ከሩሲያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ከቱርክ እና ከአሜሪካ የተውጣጡ ድርጅቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም የንግድ ትርዒቱ አስፈላጊውን የኮቪድ 19 ፕሮቶኮሎች በጠበቀ መልኩ እንደሚካሄድ የተገለፀ ሲሆን፤ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ከመላዉ ኢትዮጵያ እና ጎረቤት ሀገራት የመጡ የንግድ ጎብኚዎች ትርዒቱን ይታደማሉ ተብሏል።



