የብሔራዊ ባንክ መመሪያ በአስጎብኚ ድርጅቶች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ ተነገረ

0
633

አስጎብኚ ድርጅቶች ለሚሰጡት አገልግሎት በዶላር ቅድሚያ ከፍለዋቸው ለነበሩና በተለያየ ምክንያት ውላቸውን ላቋረጡ የውጭ አገር ደንበኞች ክፍያቸውን በዶላር መመለስ እንዳይችሉ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ያግዳል ሲሉ አስጎብኝ ድርጅቶች ቅሬታ አቀረቡ።
ብሔራዊ ባንክ እስካሁን ተግባራዊ ባደረገው መመሪያ መሠረት ውላቸውን ለሚያቋርጡ የውጭ አገር ዜጎች ገንዘባቸው በዶላር እንዳይመለስ ይደነግጋል። ጎብኚዎቹ ከፈለጉ በማንኛውም ጊዜ ተመልሰው በመምጣት እንዲጎበኙ ይገደዳሉ እንጂ፣ የከፈሉት የገንዘብ እንዲመለስላቸው አይፈቀድም። ውል ያቋረጡበት ተቀንሶ ሊመለስላቸው እንደሚችል በዓለም ዐቀፍ የተለመደ አሠራር መሠረት ተስማምተው የሚመጡትን ጎብኚዎች ገንዘብ፣ በዶላር ለመመለስ በመቸገራቸው ብሔራዊ ባንክ አሠራሩን እንዲያጤነው አስጎብኚ ድርጅቶች ጠይቀዋል።

መልካሙ ማሞ የተባሉ ‹ግሪን ቫሊ ቱር› የተሰኘ የአስጎብኚ ድርጅት ባለቤት ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ከዓመት በፊት ጀምሮ አስቀድመው ክፍያ ፈጽመው ከነበሩ ቱሪስቶች ውስጥ በኢትዮጵያ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ 65 በመቶ የሚሆኑት ውላቸውን አቋርጠዋል። ወደ 250 ሺሕ ዶላር ተቀብሎ ጎብኚዎቹን እየጠበቀ የነበረው ድርጅታቸው፣ ቀስ በቀስ ውሉ ሲቋረጥበት ያቋረጡበትን መጠን በውሉ መሠረት ቀንሶ የመክፈል ግዴታውን መወጣት ቢፈልግም የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ችግር ፈጥሮበታል። የገንዘቡ መጠን ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር የግድ ሌላ ጊዜ ተመልሳችሁ ጎብኙ ማለቱ ደንበኛ ስለሚያሳጣና የአገርንም ገፅታ ስለሚያበላሽ ሒደቱ ዘላቂ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል።

ብሔራዊ ባንክ አንድጊዜ የገባ ገንዘብ ተመላሽ አይሆንም እያለ፣ ለእኛ ለአስጎብኚዎችም በኢትዮጵያ ብር ስለሚሰጠን የውጭ ዜጋዎቹን ብር ሳንከፍል ለመቅረት እየተገደድን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። የአውሮፓ ነዋሪ እንደመሆናቸው እንዲህ አይነት አሠራር እንደማያውቁ የሚናገሩት መልካሙ፣ አነስተኛ ገንዘብ ቢሆን ውጭ ካለን መክፈል እንችል ነበር ብለዋል። እንደሳቸው ገለጻ የውጭ ፓስፖርት የሌላቸውና አማራጭ የሌላቸው የአስጎብኝ ድርጅት ባለቤቶች ግን ችግር ላይ መውደቃቸውን ጠቁመዋል።

ብሔራዊ ባንክ አገሪቷ ያለባትን የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ከግምት በማስገባት ይጠቀምበት የነበረ ይህን መሰል መመሪያ በማጤን፣ ከወቅቱ ጋር የሚሄድ፣ ያለንበትን ችግር ያማከለና በዘርፉ ላይ ዘላቂ ጉዳት የማያስከትል ውሳኔ ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚገባ መልካሙ አሳስበዋል።
ሌላው ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ያሰሙት ‹የኤፍ ኬ ኤክስፕሎር› አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት ፍቅረሥላሴ አድማሱ ናቸው። በዘርፉ ለ27 ዓመት ቆይቻለሁ የሚሉት እኚህ ግለሰብ፣ ከውጭ ምንዛሬ ጋር የነበረው ችግር የቆየ የዘመናት ነው ይላሉ። ጎብኚዎች በማንኛውም ምክንያት ሲቀሩ ገንዘባቸው በከፈሉበት ምንዛሬ እንዲመለስላቸው መጠየቅ መብታቸው ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገንዘባቸውን መልሶ ለመላክ የሚያስችል ምንም አይነት መንገድ የለውም ብለዋል።

ለዘመናት የቆየው ይህ አሠራር ከደንበኞቻችን ጋር ከመጣላት ባለፈ ወደ ክስ ሊሄዱ የሚችሉበት አጋጣሚ እንዳለ ፍቅረሥላሴ ጠቁመዋል። ውል ስንዋዋል በውጭ አገር ሕግ እንደምንዳኝ ስለምንፈርም ክስ ቢመሰረት ለከፍተኛ ወጪ እንዳረጋለን ሲሉ ተናግረዋል። የቱሪዝም ዘርፉን የሚያስተዳድረው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ጎብኚዎች በአገራችን የሚዳኙበት የሕግ ማዕቀፍ አለማዘጋጀቱ አንዱ የመንግሥት ድክመትን የሚያሳይ እንደሆነ ይናገራሉ።

ውላቸውን ላቋረጡ ጎብኚዎች “መክፈል አልቻልንም” ስንላቸው፣ “አልፈለግንም” እንደማለት ስለሚቆጥሩት፣ በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን ስለአገራችን የሆነ ክፉ ነገር ቢጽፉ፣ የተበላሸን ገጽታ ለማስተካከል አስቸጋሪ ይሆናል ሲሉ ሥጋታቸውን ለአዲስ ማለዳ አጋርተዋል።
የአገር ገጽታ የሚበላሸው መሪዎች ሲያጠፉ ብቻ ሳይሆን የውጭ ዜጎች በተለያዩ ድርጅቶች ሲከፉ ጭምር ነው የሚሉት እኚህ የአስጎብኚ ድርጅት ባለቤት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ዶላር ኪሱ ካስገባ በኋላ አልመልስም ማለቱን ሊያስብበትና የውጭ ምንዛሬ ሕጉንም በድጋሚ ሊቃኝ ይገባዋል ብለዋል። የጥቁር ገበያውን እንዲህ ያደለበውና ዶላርን እንዲህ አምላክ ያደረገው ዋናው ሕጉ ነው ይላሉ።

መፍትሔው ግለሰቦች ያስገኙትን የውጭ ምንዛሬ ማንቀሳቀስ የሚችሉበት የዶላር አካውንትን መፍቀድ ነው የሚሉት ፍቅረሥላሴ፣ ይህ ቢሆን ሕዝቡ ይዞ የመጣውን የውጭ ምንዛሬ በጥቁር ገበያ ለመሸጥ አይገደድም ነበር ብለዋል። ሒደቱን መንግሥት ይቆጣጠር እንጂ የምናመጣውን ዶላር የማናይበት ሥርዓት መሆን እንደሌለበትም ይጠቁማሉ። ሕጉን ቀለል ማድረግ ከተቻለ ዘርፉን ማሳደግና ያለውን አለመተማመን መቀነስ ይቻላል ያሉ ሲሆን፣ ኬንያ ይቅርና ከተመሠረተች አጭር ጊዜ በሆናት ደቡብ ሱዳን የውጭ ምንዛሬ አካውንት ከፍቶ በይፋ ማንቀሳቀስ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

የቱሪዝም ፖሊሲው ሲረቀቅ ጀምሮ ነበርኩ የሚሉት ፍቅረሥላሴ፣ በወቅቱም እንዲህ መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ ብቃወምም የሚሰማ አካል አልነበረም ይላሉ። በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮችን መንግሥት እንዲረዳን ሐሳባችንን የምንገልጽበት መድረክ ቢመቻችና በይፋ ተናግረን ሊስተካከል የሚችልበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም እንደሚሆንም ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

የአስጎብኚ ድርጅቶቹን ቅሬታ ይዘን ወደ ብሔራዊ ባንክ ያመራን ሲሆን፣ በደብዳቤ ጠይቁ በተባለው መሠረት አስገብተን ብንጠብቅም፣ ይህ ኅትመት እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ደጋግመን ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።


ቅጽ 3 ቁጥር 151 መስከረም 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here