በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ የመስቀል በዓል ላይ ሦስት ንጹኃን ተገደሉ

0
1471

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉትን መንደር አራት ቀበሌ፣ ሦስት ንጹኃን ዜጎች የመስቀል በዓል ላይ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ከነዋሪዎቹ መረዳት የተቻለው ግድያው የተፈጸመው ባሳለፍነው መስከረም 16/2014 እንደሆነመስቀል በዓልን ለማክበር የተዘጋጀው የደመራ በዓል በሰላማዊ መንግድ እንዲጠናቀቅ ሲያስተባብሩ የነበሩ ሦስት የአማራ ብሔር ተወላጆች ተመርጠው በታጣቂ ኃይሎቹ መገደላቸውን ነው።

ግድያው የተፈጸመባቸው ንጹኃን ገበሬዎች ናቸው የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ የሟቾቹን ሬሳ አንስተው ለመቅበር ታጣቂዎቹ ስለከለከሏቸው በዕለቱ መቅበር እንዳልቻሉ ተናግረዋል። በመጨረሻ ከአንገር ጉተን በመጡ የመከላከያ ኃይሎች እርዳታ ከአንድ ቀን ቆይታ በኋላ መስከረም 17/2014 እንደተቀበሩ ነው የገለጹት።

ነዋሪዎቹ አያይዘውም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት እና ኦነግ ሸኔ በመተባበር ከነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ በምሥራቅ ወለጋ ዞን በየዕለቱ ሰዎች እየገደሉ ነው ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎቹ እንደተረዳችው፣ ከሳምንት በፊት ታጣቂ ኃይሎቹ በኪራሙ ወረዳ ቃና ውልማይ ቀበሌ በሰነዘሩት ጥቃት ከ50 በላይ የአማራ ብሔር ተወላጆች ተገድለዋል። በአካባቢው በየዕለቱ ግድያ ስላለ የሟቾችን ቁጥር በግልጽ እንደማያውቁም ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

‹ጥቃቱ ዘር ተኮር በመሆኑ ሴቶች የገፈቱ ቀማሽ መሆናቸውን› የሚናገሩት መረጃ ሰጪዎቹ፣ ‹‹ዜጎች የሚገደሉትም አካባቢያችንን ለቃችሁ ወደ ክልላችሁ ሒዱ›› በሚል ነው ሲሉ ነው የጠቆሙት።
ከነዋሪዎቹ መካካል አንዱ ወጣት ‹‹ከሳምንት በፊት በኪራሙ ወረዳ አንዷን ሴት ጡቷን በስለት ቆርጠው ሲገድሏት በአካል ዐይቻለሁ።›› በማለት የዐይን ዕማኝነቱን ሰጥቷል። ጥቃት ተሰንዝሮባቸው በሞትና በሕይወት መካከል የሚገኙ ከ20 በላይ ሰዎች መኖራቸውንም ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድርስ ሕክምና አለማግኘታቸውንም አመላክተዋል።

ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢው ተወላጅ እንደተናገሩት ከሆነ፣ ጥቃቱ ከመሰንዘሩ በፊት የአማራ ክልል ተወላጆች ከመንደር አንድ እስከ መንደር 22 ሰፍረው ቢቆዩም፣ አሁን ላይ በተለይም ከመንደር አንድ እስከ መንድር 10 ያሉት ቀበሌዎች በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ነው።

በዚህ ወቅት በ10ሩ መንደሮች የነበሩ የአማራ ክልል ተወላጅ ንብረት ሙሉ በሙሉ በታጣቂዎቹ እንደተዘረፈና ነዋሪዎቹ ወደ አጎራባች ቦታዎች መፈናቀላቸውን ነው ከምንጮቻችን የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
ኦነግ ሸኔ በሚሰነዝረው ጥቃት ቤትና ንብረታቸውን ለቀው ኪራሙና ሀሮ ተብለው በሚጠሩ ከተሞች ተጠግተው የሚገኙ ነዋሪዎች የምግብና የአልባሳት ዕጥረት እንደገጠማቸውም አስረድተዋል።

ሌላኛው የመንደር አራት ነዋሪ በሰጡት አስተያየት፣ ታጣቂዎቹ አሁን ‹አገራችንን ለቃችሁ ውጡ› በማለት ጥቃቱን እየሰነዘሩ እንደሆነ እና የመከላከያ ኃይልም ጥበቃ ሊያደርግላቸው ፍቃደኛ ባለመሆኑ ቄያቸውን ለቀው እየወጡ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሰላም ወዳለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ለመሄድ ቢፈልጉም፣ መንገዶች መዘጋታቸውን ተከትሎ ወደ ነቀምቴና ቡሬ ከተሞች ማለፍ አልቻሉም።

ታጣቂ ኃይሎቹ በብዛት ግድያዉን የሚፈጽሙት ጨለማን ተገን አድርገው ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ በወንዞችና ጫካማ አካባቢዎች በየዕለቱ ሬሳ እንደሚያገኙና እስካሁን እንደወጡ ሳይመለሱ የቀሩ፣ አድራሻቸውም የማይታወቅ ግለሰቦች አሉ ሲሉም ነው የተናገሩት።
የአንገር ጉትን የእርሻ መሬቶች በየዓመቱ የበቆሎ ምርት ይመረትባቸው እንደነበር ነዋሪዎቹ ያወሳሉ። በአሁኑ ወቅት ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው እርሻ እንዳልታረሰ እና በአንዳንድ አካባቢ የደረሱ እህሎችን እንኳን መሰብስብ እንዳልተቻለ ነው የገለጹት። ነዋሪዎቹ ‹‹አገራችንን ልቀቁልን ተብለን ከነሐሴ ወር ጀምሮ ወገኖቻችን እየተገደሉ አልቀዋል። አሁንም ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል። መከላከያም ሊታገልልን ፍቃደኛ አይደለምና መንግሥት ሊደርስልን ይገባል።›› ሲሉ አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here