ከፍተኛ ገቢ የተገኘው ከዳያስፖራው ነው
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በነሐሴ 2013 በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች የተሰበሰበው ብር ካለፈው 2012 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ55 ሚሊዮን ብር መቀነሱ ተገለጸ።
በነሐሴ 2013 በአጠቃላይ 96.7 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፣ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ55 ሚሊዮን ብር ልዩነት አለው ሲሉ የሕዳሴ ግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በ2012 ነሐሴ ወር ላይ 152 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፣ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት የተቻለው የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌትን ተከትሎ ነው ሲሉ ኃይሉ አስታውሰዋል። በነሐሴ 2013 የተሰበሰበው ከአገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭ 24.5 ሚሊዮን ብር፣ ከውጭ አገር ዲያስፖራ ቦንድ ግዢና ስጦታ 55.7 ሚሊዮን ብር፣ በ8100 አጭር የጽሑፍ መልክት 16.2 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 109 ሺሕ ብር መሆኑ ታውቋል።
ኅብረተሰቡ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚያደርገው ድጋፍ ተቋርጦ አያውቅም የሚሉት ኃይሉ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የድጋፍ መጠኑ ሊለያይ ይችላል ብለዋል። በ2012 በጣም ከፍተኛ ገቢ የተገኘው ሰኔ ወር ላይ ሲሆን፣ በወቅቱ 87.5 ሚሊዮን ብር ማግኘት ተችሏል። ከዚያ በመቀጠል የመጀመሪየው ዙር የሕዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት መከናወን ሕዝቡን ያነቃቃው በሚመስል መልኩ በሐምሌ ወር የተሰበሰበው ገቢ 120 ሚሊዮን ብር ደርሶ ነበር።
በ2013 ነሐሴ ወር የተሰበሰበው ገንዘብ ቀንሶ የታየው በተለያየ ምክንያት መሆኑን የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ፣ የሕዳሴ ግድብ ኹለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት ቢኖርም የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታን ተከትሎ ኅብረተሰቡ ለአገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በመዋጮ መሳተፉ አንዱ ነው ብለዋል።
ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ ራሱን የቻለ የአገር ጉዳይ በመሆኑ የኅብረተሰቡን ትኩረት ሊስብ ችሏል ሲሉም ገልጸዋል። በሐምሌ እና ነሐሴ 2013 ኹለት ወራት ውስጥ በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውን በተገለጸው ምክንያት አነስተኛ መዋጮ ያደረጉ ሲሆን፣ በይበልጥ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ከፍተኛ መዋጮ ማድረጋቸውን አያይዘው አመላክተዋል።
በተጠቀሱት በእነዚህ ኹለት ወራት በአጠቃላይ 201 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የገለጹት ኃይሉ፣ ዳያስፖራው 122 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል ሲሉ ጠቅሰዋል። ይህ በ10 ዓመት ታሪክ ውስጥ የዳያስፖራው ድጋፍ ከፍ ብሎ የታየበት ሲሆን፣ የተለያዩ ዘመናዊና ቀላል የገንዘብ መሰብሰቢያ መንገዶች መፈጠራቸው ለዚህ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።
ከእነዚህም አንዱ የኦንላይን ዘዴ ሲሆን ‹‹it is my Dam›› (ግድቡ የኔ ነው) በሚል ንቅናቄ፣ በብሔራዊ ባንክ፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም ‹በዘመን ባንክ ከቻፓ እና ኤግል› ከሚባሉ ድርጅቶች ጋር በመሆን 338 ሺሕ ዶላር በሐምሌ እና በነሐሴ ወር ብቻ ማሰባሰብ ተችሏል።
ይህ የዳያስፖራው ድጋፍ ተቋሙ የተለያየ ቀላልና ዘመናዊ የሀብት አሰባሰብ አማራጮችን በመፍጠር ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ማገዝ እንዳለበት ማሳያ መሆኑንም ኃይሉ ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የአገር ውስጥ ድጋፍ ሰጪዎችን፣ የክፍለ አገር አርሶ አደር እና አርብቶ አደሮች ጋር ተደራሽ መሆን፣ ሰፊ የአገሪቱ ሕዝብ ያለው በገጠር አካባቢ ስለሆነም ከፍተኛ ቅስቀሳ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል። ኅብረተሰቡ በአሁኑ ሰዓት ለሕዳሴ ግድቡ አዲስ ስላልሆነ በገንዘብም ሆነ በሞራል የሚደግፉትን ማበረታታት ይኖርብናል ብለዋል።
የተለያዩ ሚዲያዎች፣ ማስታወቂያ ባለሙያዎችና የሲቪል ማኅበረሰቦች ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ዕቅድ መያዙንም ነው ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት። የሕዳሴ ግድብ ትስስር በሚል የማኅበራዊ ድረ-ገጽ እንቅስቃሴ ደግሞ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቅስቀሳ ማድረግ እና የሰው ኃይል በመመደብ በተለያዩ ተቋማት የሚንቀሳቀሱ የቅስቀሳ መንገዶችን ለመጠቀም ታስቧል።
ከዚህ በፊት የተለመዱ የሚዲያ እና የኪነጥበብ ሰዎችን በመጠቀም ንቅናቄ የመፍጠር ተግባራትና ድጋፎች እንዲቀጥሉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ኃይሉ አንስተዋል።
ረጅም ጊዜ የፈጀው የሕዳሴ ግድቡ የኹለት ተርባይኖች ሥራ ሙሉ በሙሉ፣ እንዲሁም የተርባይኖቹ አካል የሆነ የሚያሽከረክው ግንባታ ሥራ ተጠናቋል። እነዚህ ተርባይኖች በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ሌሎች የተርባይን ሥራዎችም በከፍተኛ ፍጥነት እየተሠሩ ነው ሲሉ ኃይሉ ገልጸዋል። ኹለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት ከተከናወነ በኋላ በአሁኑ ሰዓት ግድቡ የሚፈልገውን መጠን ይዞ ውኃው እየፈሰሰ ይገኛል።
ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



