ከውጭ በሚገባ የምግብ ዘይት ላይ ማንኛውም ቀረጥና ታክስ በመነሳቱ በገበያው ለመወዳደር አስቸጋሪ ሆኖብናል ሲሉ የኢትዮጵያ ምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አዲሴ ጋርካቦ ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነሐሴ 28/2013 ባወጣው መመሪያ መሠረት፣ የምግብ ዘይት ምርት ከተጨማሪ ዕሴት ታክስ እንዲሁም ከሌሎች ማንኛቸውም ቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ የአገር ውስጥ ዘይት አምራቾች በገበያ ላይ ያለው የዋጋ ውድድር ከፍተኛ እንደሆነባቸው ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት የምግብ ዘይት አስመጪዎች የብድር አገልግሎት እያገኙ ነው። ይህም በገበያ ላይ እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ እንዳይኖር ስለሚያደርግ የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት አምራቾችን መጉዳቱ አይቀርም ብለዋል።
አያይዘውም የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት አምራቾች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ገበያ በማረጋጋትና የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ረገድ የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ ጠቅሰው፣ ይህም ከአስመጪዎች ጋር ሲነጻጸር በጣም ከፍተኛ ነው ሲሉ አዲሴ አስረድተዋል።
የአገር ውስጥ አምራቾች የማምረት አቅማቸው ከአጠቃላይ የምግብ ዘይት ፍላጎት ድርሻ በአማካይ 10 ከመቶ ሲሆን፣ 90 ከመቶው በአስመጪዎች የሚሸፈን ነው።
ይህም በተለያዩ ማነቆዎች የተነሳ አምራቾች በሚፈለገው መጠን እያመረቱ እንዳልሆነ ማሳያ ነው ያሉት አዲሴ፣ ከእነዚህም መካከል የጥሬ ዕቃ (የቅባት እህሎች) ዕጥረትና የዋጋ መናር፣ የግብዓቶች የግብይት ሰንሠለት የተሳለጠ አለመሆንና ካለፈው ሐምሌ 15/2012 ጀምሮ የአኩሪ አተር ግብይት በኢትዮጵያ የምርት ገበያ (ECX) በኩል ብቻ መሆኑ፣ በምርት ገበያው የሚቀርበው የአኩሪ አተር ምርትና የፋብሪካዎች የማምረት አቅም አለመመጣጠን ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የቅባት እህሎች በከፍተኛ መጠን ወደ ውጪ መላካቸው፣ የአመራረት ሒደት ዘመናዊ አለመሆን፣ አምራቾች የራሳቸው የሆነ የቅባት እህል የሚያመርቱበት ዘመናዊ እርሻ አለመኖሩ፣ ለጥሬ ዕቃ (ድፍድፍ ዘይት) እና ለመለዋወጫ መግዣ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ አለመገኘቱ፣ የምግብ ዘይት በኮንትሮባንድ አማካይነት ወደ አገር ውስጥ መግባቱ፣ በአገር ውስጥ ከሚመረቱ የቅባት እህሎች ውስጥ በአብዛኛው ምንም ዕሴት ሳይጨመርባቸው ወደ ውጭ የሚላኩ መሆኑ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማነስና በተደጋጋሚ መቆራረጥ በዘርፉ ከሚነሱ ችግሮች ውስጥ ይጠቀሳሉ ብለዋል።
ከጠቅላላው የሰብል ምርት ውስጥ የቅባት እህል ድርሻ በአማካይ 2.71 ከመቶ የሚሸፍን መሆኑን ያወሱት አዲሴ፣ በመሆኑም የቅባት እህል አምራች አርሶ አደሮችን አመራረት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። አክለውም ትላልቅ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች የራሳቸውን የግብዓት ፍላጎት ማሟላት እንዲችሉ የመሬት አቅርቦት ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም አብራርተዋል።
በተጨማሪም የቅባት እህል ሰብሎችን የሚደግፍ የመካከለኛ ጊዜ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ለፋብሪካዎች በቂ ጥሬ ዕቃ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። እንዲሁም በቅባት እህሎች ላይ ዕሴት በመጨመር የተሰማሩ ኩባንያዎች ለምርት ግብአትነት የሚጠቀሙበት ጥሬ ዕቃ በአንድ ዓይነት የግብይት ስርዓት የሚስተናገድበት አሠራር በመቀየስ ግብይቱን ፍትሐዊ ማድረግ ያስፈልጋልም ሲሉ ጠቁመዋል።
በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን 2013 መረጃ መሠረት፣ በኢትዮጵያ የዓመት የምግብ ዘይት ፍላጎት 888 ሺሕ 679 ቶን ነው። በአገሪቱ በአጠቃላይ 232 የሚሆኑ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉ ሲሆን፣ 206 ጥቃቅን አምራቾች ናቸው።
በ2013 የቅባት እህሎችን ጨምቀው በሚያጣሩ ፋብሪካዎች ማምረት የተቻለው የምግብ ዘይት መጠን 18 ሺሕ 159 ቶን ሲሆን፣ የፓልም ድፍድፍ ዘይት በሚያጣሩ ኹለት ፋብሪካዎች 22 ሺሕ 154 ቶን የተጣራ የፓልም ዘይት ለገበያ ቀርቧል። በአጠቃላይ ከፓልም ድፍድፍ ዘይትና ከቅባት እህሎች ተጨምቆ የተገኘው የምግብ ዘይት መጠን 40 ሺሕ 313 ቶን ነው።
የኢትዮጵያ ምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር፣ በዘርፉ በተሰማሩ አምራቾች ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ የማኅበሩን አባላት የጋራ ችግር ለመፍታት፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና ለአገሪቷ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ የተቋቋመ ማኅበር ነው። ማኅበሩ በአገሪቱ የሚገኙትን ጥቃቅን፣ መካከለኛና ከፍተኛ አቅም ያላቸውን የምግብ ዘይት አምራቾች በአንድ አካትቶ የአገሪቱን የምግብ ዘይት ፍላጎት ለመሸፈን የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



