ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ተገለፀ

0
811

የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረገጽ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ የፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ ከቅዳሜ መስከረም 22/2014 ዓ.ም ረፋድ ጀምሮ ያለበትን እንደማያውቁ ጓደኞቹ እና የስራ ባልደረቦቹ መናገራቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ በፌደራል ፖሊስ እጅ ስር እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ኃላፊው እንደተናገሩት ከሆነ ተስፋዓለም በአሁኑ ጊዜ “የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ቢሮ የሜክሲኮ ማቆያ እንደሚገኝ” ገልጸው፤ “ምንም የሚፈጠር ነገር የለም። ያለውን ነገር እያጣራን ነው። ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም” ሲሉ ተናግረዋል።

የወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊው፤ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም በምን ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ጋዜጠኛው ቅዳሜ ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የተሰሙ የተቃውሞ ድምጾችን በኢትዮጵያ ኢንሳይደር የፌስቡክ ገጽ ላይ አጋርቶ የነበረ ሲሆን፤ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ መኖሪያ ቤቱ ላይ ፍተሻ መካሄዱን ከታማኝ ምንጮቼ ሰማሁኝ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
__________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here