በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ለትግራይ ክልል ነዋሪዎች ጥሪ በማድረግ በተቆጣጠራቸው የተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ያሉ ሰብሎችን አጭዳችሁ ውሰዱ ማለቱንና በአንዳንድ አካባቢዎች አጨዳ መጀመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በተቆጣጠራቸው የተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች እስካሁን በነበረው ቆይታ የነበሩ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረቶችን ዘርፎ እንደጨረሰና መውሰድ ያልቻላቸውን እንስሳት እንደገደለ የሚነገርለት ህወሓት፣ ሰሞኑን ደግሞ የደረሱ ሰብሎችን አጭዶ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው የአዲስ ማለዳ ምንጮች ያመላከቱት።
በሽብርተኛነት በሕዝብ ተወካዮች የተፈረጀው የህወሓት ቡድን፣ ሰሞኑን በአማራ ክልል ግዳን ወረዳ ሙጃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የደረሱ ሰብሎችን ማጨድ እንደጀመረና የራሱን ምሽግ እያዘጋጀ መሆኑን ነው ከአካባቢው ሠሞኑን የተፈናቀሉ ምንጮች የገለጹት።
አካባቢው የገብስ፣ የአተር፣ የምስር፣ የባቄላ ሰብሎችን በማምረት ይታወቃል የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ በተለይም ከሁሉም ቀድሞ ጨርጨሬ የተባለው ገብስ ለመታጨድ ስለደረሰ ቡድኑ ለትግራይ ክልል ነዋሪዎች “ኑ እጨዱና ውሰዱ” ብሎ ጥሪ በማስተላለፍ የደረሰውን ሰብል እያጨደ መሆኑን ነው ከምንጮቻችን መረዳት የተቻለው።
ታጣቂ ቡድኑ ሰብሉን የማጨድ ሥራ ከመጀመሩ በተጨማሪ የሰዎችን ሕይወትም እየቀጠፈ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በላሊበላ አካባቢ የሚገኙ ከሃያ በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን ብልታቸውን “የመስለብ አስከፊ” ድርጊት እንደፈጸመም ነው የተመላከተው።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚያመላክቱት ከሆነ፣ ሌሎች አርሶ አደሮች የደከሙበትን ሰብል በግዳጅ የማጨድ ጥሪው በግዳን ወረዳ ብቻ ሳይሆን ሰብል በደረሰባቸው ሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎችም ጭምር እንደሆነ ነው።
ቡንኝ የተባለ ጤፍ ለአጨዳ ደረሷል የሚሉት ከዋጃ፣ ከጥሙጋና ከራያ ቆቦ ሰሞኑን ወደ ደሴ ከተማ ያቀኑት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ለትግራይ ክልል ሰዎች “የደረሰ ሰብል አለ፤ ኑና አጭዳችሁ ውሰዱ” የሚል መልዕክት አስተላልፏል ሲሉ ነው የተናገሩት።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንዳመላከቱት ከሆነ፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት፣ በአካባቢው የሚገኙ አንዳንድ አርሶ አደሮችን “የደረሰውን ሰብል ራሳችሁ ሰብስቡና 50 በመቶው የእናንተ 50 በመቶው የኛ ይሆናል” የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፉንም ነው መረዳት የተቻለው።
አካባቢውን ከተቆጣተረበት ከሐምሌ ወር ጀምሮ የመንግስሥና የግለሰቦችን ንብረት ዘርፎ ወደ ትግራይ ክልል አጓጉዞ ስለጨረሰ በርሃብ እየተቀጣን መሆኑን ከተናገርን ቆይተናል የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ እህል ደረሰልን ብለው ተስፋ ቢያደርጉም አሁንም ቢሆን ምርቱን የማግኘታው ጉዳይ እንዳሰጋቸው ነው የገለጹት።
አክለውም፣ “ያለፈው አልፏል መሰል ግፍ ዳግም ሳይደርስብን አሁን እንኳን መንግሥት ቢደርስልን ምናለበት? ከዚህ በላይ ምን እስከምንሆን ነው የሚጠበቀው? ጩኸታችን የማይሰማውስ እስከ መቼ ነው?” በማለት ነው ጥሪያቸውን ያስተላለፉት።
በአላማጣና በቆቦ ከተማ መካከል ከምትገኘው ጥሙጋ ከተባለችው ከተማ ሰሞኑን ወደ ደሴ ያቀኑ ወጣቶች እንደተናገሩት፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት የተቆረጠውን የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ “ወደ እኛ ክልል ናችሁ” ብሎ ነበር። ሰሞኑንም ወጣቶችን ከጎናቸው ሆነው እንዲዋጉ በግዳጅ እያፈኑ መሆናቸውን እና ወገናችንን አንዋጋም በማለት የሞገቱ ወጣቶች፣ ጫካ ላይ ሆነው የድረሱልን ጥሪ እንዳስተላለፉ ወጣቶቹ የአይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
ነዋሪዎቹ በመጨረሻም በሽብርተኝነት የተፈረፈው ህወሓት እስካሁን በነበረው ቆይታ ቡቃያዎችን እያወደመ ለፍሬ እንዳይበቁ ማድረጉን አመላክተው፣ ከጥፋት ተርፈው ለመታጨድ የደረሱትን ሰብሎች ደግሞ የራሱ ለማድረግ አየሞከረ ነውና መንግሥት ሊደርስልን ይገባል ሲሉ ነው ያሳሰቡት።
ጦርነቱን እየመከቱ ያሉ የአማራ ታጣቂዎች በበኩላቸው፣ “እኛ ያለብን የመሣሪያ ዕጥረት ነው፣ ጥቃት የሚያደርስብንን ቡድን መመከት እንችላለን፤ መንግስትን መሣሪያ ይርዳን ብለን በተደጋጋሚ ብንጮህም ሊሰማን አልቻለም” ብለዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 153 መስከረም 29 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



