ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግብዓት የሚያቀርቡ ተሽከርካሪዎችም ሰለባ ሆነዋል
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ያለው የጸጥታ ችግር ባለመሻሻሉ የዞኑን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ማስተጓጎሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በመተከል ዞን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ እስካሁን ድረስ እልባት ባለማግኘቱ አሁን ላይ በተለይ የገጠሩ ማኅበረሰብን እንቅስቃሴ መገደቡን የዞኑ ነዋሪዎች ገልጸዋል። የተስተጓጎለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ፣ የማኅበረሰቡን ኑሮ ፈታኝ እንዳደረገውም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በዞኑ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር መሻሻል አለማሳየቱን ተከትሎ ዞኑ በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከመከላከያ በተጨማሪ የክልል ልዩ ኃይሎች በአካባቢው መሰማራታቸው የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ነዋሪዎች እንደሚሉት በዞኑ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን የገጠሩን ማኅበረሰብ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነት ለወራት አስተጓጉሏል ብለዋል።
ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ አሁን ላይ በአብዛኛው ከከተሞች ውጪ የሆኑ የዞኑ አካባቢዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እና የማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ እንደተገደበ ነው። የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ባለባቸው አካባቢዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በጸጥታ ኃይል የታጀቡ መሆኑም ተገልጿል።
የታጣቂዎች ጥቃት ያስተጓጎለው የዞኑ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ግብዓት የሚቀርቡ ተሸከርካሪዎችን ጭምር መሆኑን ነዋሪቹ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። ከግልገል በለስ ወደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሚወስደው መንገድ ታጣቂዎች አንድ አሽከርካሪ ገድለው ንብረት መዝረፋቸውን ተከትሎ፣ ለሕዳሴው ግድብ ግብዓት የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከሳምንት በላይ መቆማቸው ተነግሯል።
ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ የሚያገለግል ግብዓት የጫኑ ተሽከርካሪች ግልገል በለስን አልፈው መሄድ ባለመቻላቸው፣ እየተንገላቱ መሆኑን የዐይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። “ጭነት ይዘው የቆሙ የተሽከርካሪ ሹፌሮች ከሳምንት በላይ በመቆማቸው እየተቸገሩ ነው፤ አንዳንዶቹ የአልጋ ገንዘብ አልቆባቸው፣ አልጋ አከራዮች እንዲተባበሯቸው ጠይቀን እየኖሩ ነው” ሲሉ የአይን እማኞቹ ያለውን ሁኔታ ጠቁመዋል።
በመተከል ዞን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከኹለት ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም፣ እስካሁን የንጹኃን ዜጎችን ሞትና መፈናቀል የሚያስቆም መፍትሔ እንዳልተገኘ የሚገልጹት የዞኑ ነዋሪዎች፣ መከላከያ በዞኑ ቢኖርም ችግሩን መቅረፍ አልቻለም ብለዋል። ችግሩ እልባት ባለማግኘቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ በዘንድሮው የምርት ዘመን የግብርና ሥራ ባለማከናወኑ የሚቀጥለው ዓመት ከጸጥታ ችግር በተጨማሪ ለረሃብ አደጋ የሚጋለጥበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል።
በዞኑ የተሰማሩት የመከላከያ እና የክልሎች ልዩ ኃይሎች በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽምን ታጣቂ ኃይል የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድ ችግሩን ይቀርፋሉ ቢባልም፣ አስካሁን እንደተባለው እንዳልተፈጸመ ነው ነዋሪዎቹ የሚገልጹት። የተሰማራው የመንግሥት የጸጥታ ኃይል በዞኑ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይል የሚያደርሰውን ጥቃት በኃይል ለማስቆም የሚያስችል አቅም ቢኖረውም፣ ዕርምጃ እየወሰደ አለመሆኑን ነዋሪዎች መታዘባቸውን ጠቁመዋል። በመሆኑም የፌደራሉ መንግሥት ችግሩን ተረድቶ ለዓመታት የዘለቀውን የዞኑን ማኅበረሰብ ችግር ለመፍታት ታጣቂ ኃይሉ ላይ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካሉት ሦስት ዞኖች በመተከል እና በካማሺ ዞኖች ያለው የጸጥታ ችግር መሻሻል ባለማሳየቱ፣ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በኹለቱ ዞኖች አለመካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ ኹለቱ ዞኖች አዲስ በተመሰረተው የሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት በሕዝብ የተመረጠ ተወካይ የላቸውም።
ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



