የምግብ ዘይት የሆነው ጤና የሱፍ ዘይት፣ በዱከም ከተማ የፋብሪካ ማስፋፊያ የጀመረ መሆኑን የምርቱ ባለቤት ‹‹54 ካፒታል›› የተሰኘው ድርጅት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ይህን ተከትሎም አሁን ላይ ከኹለት ዓመት በፊት የተጀመረው የማስፋፊያው የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነው 130 በመቶው ተጠናቆ ምርት መሥጠት መጀመሩን ነው የተገለጸው።
ከአንድ ዓመት በኋላ፣ በ2022 መጨረሻ አጠቃላይ የማስፋፊያ ሥራው የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ በዚህም ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሲሸጋገር የዘይት ማጣሪያ ፋብሪካው የድርጅቱን የዘይት አቅርቦት 400 በመቶ እንደሚያሳድገውም ተገልጿል።
‹‹54 ካፒታል›› በአገሪቱ የሚስተዋለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ጤና የተሰኘውን የሱፍ ዘይት በአገር ውስጥ በማምረት የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ይገኛል ነው የተባለው።
እንዲሁም፣ በአገሪቱ የምግብ ዘይት የአቅርቦት መጠኑን ከማሳደግ በተጨማሪ መንግሥት ባወጣው አዲስ ዐዋጅ መሠረት የኤክሳይስ ታክስ በመነሳቱ የምግብ ዘይቱ ዋጋው ሊቀንስ እንደሚችል ተመላክቷል።
በሦስት ጊዜያት የማጣራት ሒደት ውስጥ የሚያልፈው ጤና ዘይት፣ ሁልጊዜም በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጥራት ይመረታል ያለው ድርጅቱ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት አዲሱ የማምረቻ ፋብሪካ ደግሞ ጤና ዘይት በኢትዮጵያ ውስጥ ሁልጊዜም ከፍተኛ ጥራቱን ጠብቆ፣ ተመራጭ የምግብ ዘይት እንደሆነ እንዲቆይ ይረዳዋል ሲል ጨምሮ ገልጿል።
ጤና የሱፍ ዘይት አነስተኛ የተጠራቀመ የስብ ይዘት ያለው ሲሆን፣ በተጨማሪም ከፍተኛ የአንድ እና የብዙ ያልተከማቸ ፋቲ አሲድ የያዘ እና ከፍተኛ የቫይታሚን ኢ፣ እና የቫይታሚን ኬ በውስጡ የሚገኙበት መሆኑ በኩባንያው ተገልጿል።
በርካታ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እየፈጠረ፣ ለሕብረተሰቡ ጤናማ ምርቶችን በማቅረብ ለማኅበረሰብ ጤና እና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ በአሁኑ ወቅት አዲስ የተሠራው የፋብሪካ ማስፋፊያ የኩባንያውን ምርት በ130 በመቶ ከማሳደግም በላይ፣ ከ500 በላይ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችንም ይፈጥራል ነው የተባለው።
‹‹54 ካፒታል›› በመባል የሚታወቅው ኩባንያ፣ በ2013 የተቋቋመ አፍሪካዊ ንብረት አሥተዳዳሪ ሲሆን፣ ኩባንያው ጤና የሱፍ ዘይትን፣ 555 ሳሙናን፣ ኦውራ ሳሙናን፣ ሼፍ ሉካ ፓስታን እንዲሁም አኳ ሴፍ ውኃን የመሳሰሉ ምርቶችን ያቀፉ 5 ‹ፖርት ፎሊዮ› ኩባንያዎችን የሚያስተዳድር መሆኑን ከኩባንያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



