መንግሥት አገር እንዲያስተዳድር ሙሉ ሥልጣን የሚሰጠው በዋናነት ሕዝብን እንዲጠብቅ ነው። ይህ ኃላፊነት የሚመነጨው ከራሱ ከሕዝብ በተሰጠ ተልዕኮ እንደመሆኑ መንግሥት ነኝ የሚል አካል በቅድሚያ የመሠረተውን፣ የሚያበላውንና የሚደግፈውን ሕዝን ደኅንነት ማስጠበቅ አለበት። ደኅንነት ሲባል ደግሞ ማንኛውንም የሕብረተሰቡን አካል ከሞት፣ ከበሽታና ከማንኛውንም ዓይነት ጤናውን አደጋ ላይ ከሚጥል አደጋና ሥጋት እንደሆነ ይታመናል።
መንግሥት ራሱን ከሕዝብ ጥቃት ለመጠበቅ ብሎ የሚያቋቁማቸው ሠራዊቶችም ሆኑ አደረጃጀቶች እንደማያዘልቁት ሩቅ መሔድ ሳይጠበቅብን ከዓመታት በፊት እዚሁ አገራችን የተከሰተውን በመመልከት መረዳት ይቻላል። መንግሥት የሚኖረው ሕዝብ እስከፈቀደለትና ለሕብረተሰቡ እስካስፈለገ ድረስ ነው። ይህ ካልሆነና ሕዝብ በመንግሥት ተስፋ ከቆረጠ፣ እሱን እጎዳዋለሁ ብሎ አገርንም እንደሚጎዳና ለጋራ ጠላት አብረው ተላልፈው እንደሚሰጡ እሙን ነው።
ሠሞኑን በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል አንድ ዓመቱን ሊያስቆጥር በተቃረበው ጦርነት መነሻነት ብዙ አሳዛኝ ነገሮችን እየሰማን እንገኛለን። የተፈናቃዮች ችግርና ሰቆቃ ራሱን የቻለ የመነጋገሪያ ርዕስ የነበረ ቢሆንም፣ ችግሩን ለመቀነስም ሆነ ምንጩን ለማድረቅ እንደዋና መፍትሔ የሚወሰደው የጦርነቱ መቋጨት ነው።
ጦርነቱ ይጠበቅ የነበረውን አቅጣጫ ትቶ በተቃራኒው መንጎድ በመጀመሩ ሕዝብ ላይ የፈጠረው ሥጋትና መፈናቀልን ማንም የሚያውቀው ነው። ይሁንና መንግሥት የሚለቃቸውና በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት የሚቆጣጠራቸው መሬቶች እየሰፉ መምጣታቸው በራሱ ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ጦርነት በሕዝቡ ውስጥ ፈጥሯል። ይህን ምናባዊ የጦር ሜዳን መቆጣጠር እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።
ያሉትን የጦር ቀጠናዎችም ሆነ የመታገያ ስልቶች ኃላፊነት የተሰጠው የመንግሥት አካል መቆጣጠር ካልቻለ መንግሥት መመለስ የማይችለው አረንቋ ውስጥ እንደሚገባ ግልጽ ነው። አሸባሪ የተባለ ቡድን ሊያሸንፍ ይችላል የሚል አስተሳሰብ በሕዝብ ሥነ-ልቦና ውስጥ እንዲቀረጽ ማድረጉ በራሱ ትልቅ ችግር እንደሚያመጣ ይታወቃል። ይህ ማለት ግን ሁሌ እናሸንፋለን ብሎ በራስ መታበይን እንዳይፈጥር መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ሕዝብም ሆነ ወታደሩ እንዲዘናጋና እንዳይዘጋጅ በሚያደርገው ልክ ጠላትን መናቅ ተገቢ እንዳልሆነ ከደርግ ውድቀት መንግሥት ሊማር ግድ ይለዋል።
ለሕዝብ መሸበር ዋናው መንስዔ የመረጃ በአግባቡ አለመድረስ መሆኑን ብዙኀኑ ይስማማበታል። ትክለኛውን መረጃ አስቀድሞ እንዲያገኘው የተደረገ ማኅበረሰብ አስቀድሞ እንዲዘጋጅ ያደርገዋል። ችግሩ ገፍቶ እንደሚመጣ ወይም እንደታሰበው ላይሆን እንደሚችል ከተረዳ በወቅቱ ሳይሸበር እንዲሸሽ ያደርገዋል። አሊያም የሚመጣውን በጸጋ እንዲቀበል ራሱን አሳምኖ እንዲቆይ ያስችለዋል።
መረጃ ለማንም አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል። ሕዝብ መረጃ የማግኘት ሙሉ መብት አለው ቢባልም የአገር ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ ግን ሊደበቅበትና ምስጢር ሊያዝበት እንደሚችል ይታወቃል። ይህ ማለት ግን ስህተቱን ለመሸፈን የፈለገ ባለሥልጣን እንደፈለገ እያማረጠ ‹ይህ ይነገር፤ ይህ ይደበቅ› ማለት እንደማይገባው አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።
ለወገን ተብሎ የሚለቀቅ መረጃ ለጠላት ሊጠቅም ቢችልም መረጃውን ያላገኘ ሕዝብ ይበልጥ የሚጎዳ ከሆነ ጠላት ቢጠቀም ሳይሻል አይቀርም። ከሐውዜን ታሪክ እንደምንረዳው፣ የቀድሞው መንግሥትም ሆነ አማፂያኖቹ ቆሜለታለሁ የሚሉትን ሕዝብ ሕይወት ከጠላት ሞት ማስቀደማቸውንና ድርጊቱ እነሱን ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብን ብዙ መስዋዕትነት እንዳስከፈለ ነው።
ሠሞኑን በወሎ ግንባር እጅግ የከረሩ ውጊያዎች መደረጋቸውን የማያውቅ አይኖርም። ጦርነቱ እንዳ አዲስ ካገረሸበት ቀን ጀምሮ ማሸነፍም ሆነ መሸነፍ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ መረጃ ሳይሆን ፕሮፓጋንዳ ለሕዝብ የሚያቀርበው ይበልጥ ነበር። ተሸንፈናል ብሎ መንግሥት ራሱ አምኖ ባይናገርም፣ ሌላው ሲናገር ግን አፍ አፉን ሊባል ባልተገባ ነበር። ይህ ባለመሆኑ ሕዝብ እንዳያመልጥ የተዘረፈ ንብረቱንም እንዳያሸሽ ማድረጉን የሚናገሩ አሉ።
የፕሮፓጋንዳ ሥራው እንዳለ ሁኖ፣ “ቦታችሁ የጦር ቀጠና ስለሚሆን የፈለጋችሁ ይህን አካባቢ ለቃችሁ ውጡ” ብሎ ቀደም ብሎ ማስጠንቀቅስ ምን ችግር ይኖረዋል። በሶሪያው ጦርነት እንዲሁም እስራኤል በሐማስ ላይ በምታካሂደው ጦርነት በተደጋገሚ የታየና ተቃውሞ የሌለበት አካሄድ እዚህ አገርም ሊለመድ ግድ እንደሚል አዲስ ማለዳ በአጽንኦት ትናገራለች።
ሕዝብን ከለላ አድርጎ መዋጋት ዓላማው ለሕዝብ መቆም ሳይሆን ራስን በሕዝብ ሞት ለማትረፍ መሞከር ነው። ከሕዝብ የተጣላ መቼም መጨረሻው እንደማያምር ቴክኖሎጂ በበዛበት በዚህ ዘመን ባለሥልጣናት ለመማር አያስቸግራቸውም። ሕዝብ ሽንፈትንም ሆነ ድልን ማወቅ ያለበት የሚሞቱት ልጆቹ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን ራሱንም ማዳን ሌላውንም ማገዝ ስላለበት ጭምር ነው።
ወታደራዊ የመረጃ ክፍሉ ጠላት ተሰባብስቦ “ሆ” ብሎ፣ “በለው!” እያለ እስኪዘምት ድረስ ምንም ነገር ለሕዝቡ እንዳይደርስ ማድረጉ አንድም ሕዝቡ “ሆ” ብሎ እንዳከላከል ያደርገዋል። በሌላም በኩል፣ መመከት እንደማይቻል ሕዝቡም ተረድቶ ወታደርን ተከትሎ ሳይሆን ቀድሞ በእግሩም ቢሆን ለመውጣት ይችላል። ወታደሩን “አናሳልፍም” ማለቱ ተገቢ ነው ባይባልም፣ የረጅም ርቀት ተተኳሾችን ለመትከል ወደ ኋላ ማፈግፈግ እንዳለበት አስረድቶ ቢሆን አስቀድሞ የማሳወቅን ጥቅም ይገለገልበት ነበር።
የመንግሥት ባለሥልጣናት ሊያዝባቸው የመሰላቸው አካባቢ አስፈላጊ ሠነዶችን ማሸሻቸው ተገቢ ነው ሊባል ቢችልም፣ ከነቤተሰባቸው ለሕዝቡ ሳያሳውቁ ግር ብለው የሚወጡ ከሆነ የሚፈጥረው የሥነ-ልቦና ቀውስ ከፍተኛ ስለሆነ፣ ሕዝብን የመታደግ ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ ሕዝቡን ለሥርዓት አልበኝነት አሳልፈው የመስጠታቸው አዝማሚ ስለሚያመዝን ሒደቱ ሊታሰብብት ይገባል።
በሌላ በኩል፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ምን ሊውጠን ነው እያለ በሚጨነቅበት ወቅት ወቅታዊ መረጃን እንዲያሰራጭ ኃላፊነት የተሰጠው አካል ሕዝቡን ካስጨነቀው ሁኔታ ፍፁም የሚርቅ ጉዳይን ይዞ ሲቀርብ ይሰማል። ሒደቱን በምሳሌ እንየውና፣ ሠውነቱን ማንቀሳቀስ የተሳነውን ሕመምተኛ የሚያስታምመው ግለሰብ “ቢንቢ በላኝ አባራቸው” ሲባል፣ የሚፈለፈሉበትን አንዱን ኩሬ አጥፍቻለሁ ማለቱ በሕመምተኛው መሳለቅ እንጂ ለጭንቀቱ መፍትሔ አይሆንም።
በሽተኛው አገግሞ የሚበሉትን ተባዮች ራሱ ማባረር እስኪችል ድረስ፣ ቅድሚያ ደሙን እየመጠጡ ያሉትን ማባረር ግድ ይላል። እየተመላለሱ ካስቸገሩና አስታማሚውን ካደከሙ አጎበር መሳይ መከላከያን መጠቀም ግድ ይላል። ከተቻለም አጎበሩ ውስጥ በትንሽ በትንሹ እያስገቡ መንገዳቸውን ዘግቶ በቆረጣ መጨረስ ይመከራል። ይህ ሲሆን ግን ነፍሳቱ አውቀው እንዳይደበቁ በመጠንቀቅ ለታማሚው ሁኔታውን ማስረዳት ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ታማሚው “የበለጠ አስበላኝ” ብሎ ሌላ አስታማሚ ሊያስጠራ ስለሚችል መጠንቀቁ ተገቢ ነው።
ተባዮች ተባብረው ግር ብለው ጨለማን ተጠቅመው ቀዳዳ እየፈለጉ የሚገቡ ከሆነ፣ በዘመናዊ መሣሪያ ላጥፋቸው ብሎ ፍሊት ታማሚው በተኛበት መጠቀሙ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። እንዲደክሙ በጭስ አፍኖ እነሱ እንደሚረባረቡት ከሌሎች አስታማሚዎች ጋር ተባብሮ ከያሉበት ማደን በዘላቂነት እንዲወገዱ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ሕመምተኛው መበላቱን፣ አስታማሚውም ብቻውን እንደማይችል፣ እንዲሁም ከኹለቱም ምን እንደሚጠበቅ በግልፅ በወቅቱ ከተነጋገሩና ከተስማሙ ብቻ ነው። አየር ላይ ያለን ቢንቢ በኹለት እጆች ጭብጨባ ለመግደል ምን ያህል የእጆቹ ቅልጥፍናን እንደሚጠይቅ ይታወቃል። ኹለት ሰዎች አንድ አንድ እጃቸው ተጠቅመው በጥፊ አጋጭተው ለመግደል ካሰቡ ደግሞ ምን ያህል መግባባትና መናበብ እንዳለባቸው ግልፅ ነው። ለመጨባበጥ እንኳን እጅን የሚሳሳትና የሚሸዋወድበት ትውልድ ባለበት በዚህ ዘመን፣ አይናችንና ጆሯችንን ብቻ ሳይሆን መጠቀም ያለብን ኹሉንም የስሜት ሕዋሳቶቻችንን ነው።
ውጊያ፣ መሣሪያና ተዋጊ ብቻ ሳይሆን የሚጠይቀው ዝግጁ የሆነ ሥነልቦና፣ ወኔና ተገቢ የሆነ ቅስቀሳን ነው። አዲስ ማለዳ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ይህን ያህል ጊዜ እየተባባሰ የቆየው ጦርነት በአጭር ጊዜ እንዲቋጭና ሕዝብ ወደናፈቀው ሠላሙ እንዲመለስ የተለየ ስልት ሊቀየስ ይገባል ትላለች። እስካሁን ውጤታማ ያላደረገው ተለይቶ እንዲቀር በማድረግ፣ ጠቃሚውን ይዞ ሕዝብን ያማከለ ጉዞ ሊሆን ይገባል።
ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014



