ማኅበራት የት ናችሁ?

0
689

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር በተመሠረተበት ወቅትና ሰሞን፤ ለመንግሥት ሳይቀር አጀንዳና የቤት ሥራ የሚሰጥ ጉልበት ያለው ማኅበር ነበር። ያንን የሚያስቀና ተጽእኖ የመፍጠር አቅም ታድያ ዛሬ ላይ ብዙ ማኅበራት ዘንድ አናገኝም።
ማኅበራት በየተቋቋሙለት ዓላማ የሚያሳኩት ግብና ዘላቂ ርዕይ ያላቸው ናቸው። ከዚህ በተጓዳኝ በየመካከሉ ለሚደቀኑ ፈተናዎች መልስ ከመስጠትና ከመታገል ጀምሮ በመሞገት መለወጥ የሚቻሉትን መለወጥ፣ ከአቅማቸው በላይ የሆነውን ደግሞ ቢያንስ አሳውቆ አቤት እንዲሉና ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ይጠበቃሉ።

ለምሳሌ አሁን በአገራችን ጦርነት እንዲሁም መፈናቀልና ረሀብ በተለያየ አቅጣጫ የምንሰማበት አሳዛኝ ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ከሰብአዊ ጉዳዮችና አገልግሎቶች ጋር በተገናኘ የተመሠረቱ ማኅበራት ሁኔታዎችን እንዲከታተሉና እንደ ማኅበርም የአባላቱን ሐሳብ ሊያንጸባርቁ ያሻል። ያንን ቢያደርጉ ሁኔታው ምን ያህል እንዳሳሰባቸው ለመረዳት ያስችላል።

ሆኖም ይህ ሲሆን በብዛት አላስተዋልንም። አንድ ሰሞን ብቻ ሁሉም በየፊናው ‹እቃወማለሁ! አልደግፍም! ከእገሌ ጎን ነኝ!› ይልና በኋላ ዝም። ማኅበራት አንድ መልክ ባለው ስርዓት (ሲስተም) የሚመሩ ባለመሆኑ፣ እንደ መሪዎቹ ስሜት፣ ፍላጎት፣ አቅም፣ ጥንካሬ፣ ፍርሃት ወይም መሰል የግል ዕይታ መሠረት ይመራሉ። ለዛ ነው በአንድ ዘመን የተጨበጨበለት ማኅበር በሌላ ጊዜ የሚዳከመው ወይም በአንድ ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ አቋምና ድምጽ ያለው ማኅበር የማይታየው።

በአገራችን አንዱ ትልቁ አጥፊ ነገር ይመስለኛል የ‹ዳርቻ አመለካከት› ነው። ይህ ቃል ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ መዋሉን አላውቅም ወይም ሐሳቤን ምን ያህል እንደሚሸከም እንጃልኝ! ብቻ ግን መካከለኛ የሚባል ነገር በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ተቀባይነቱ እምብዛም ነው። ወይ ትስማማለህ ወይም አትስማማም ነው። ድምጸ ተዓቅቦም ሆነ ከኹለቱም አቋሞች ዕይታ ተጋርተህ አዲስ መንገድ ማሳየት የሚባል ነገር ቦታ የለውም።

ማኅበራት ይህን ሳይፈሩት አይቀሩም ወይም በዚህ መንፈስ የተቃኙ ይመስለኛል። የመንግሥት ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ ላለመባል፤ ከሕዝብም ከመንግሥት ባለሥልጣናትን ላለመኳረፍ ዝም ይላሉ። ይህ ዝምታ ብዙ ያስከፍላል።

ይልቁንም በድሃ አገረ ይበልጡን ሴቶችና ሕጻናት በብዙ መልኩ አግባብ ያልሆነ ሸክም በሚሸከሙበት ሁኔታ፣ ስለሴቶችና ሕጻናት ለመሥራት የተመሠረቱ ማኅበራት ዝም ሲሉ ያስከፋል። የሚያደርጉት ባይኖር እንኳ ሐዘናቸውን መግለጽ፣ ተፈናቃይ ባሉባቸው ቦታዎች አቅንቶ መጎብኘት፣ መርዳትና አይዟችሁ ማለት ይገባ ነበር። ግን አልሆነም። ምንአልባት ያላየሁትና ያልሰማሁት ካለ እታረማለሁ። ሁሉንም ማኅበራት በአንድ አውድ መፈረጅም አግባብ እንዳይደለ አውቃለሁ።

ሁሉ ሙሉ፣ ሁሉ ምቹ ቢሆን ኖሮ የማይመሠረቱ ብዙ ማኅበራት አሉ። በጎደለው እንዲሞሉ፣ ችግር እንዲፈቱ አልያም ድምጽ እንዲሆኑ የተቋቋሙት በርካታ ናቸው። በዚህ ቀንና በዚህ ሁኔታ ዝም ካሉ፤ እንግዲያው ዋጋቸው ስንት ነው? ሚዛናቸውስ ምንድን ነው ብለን ልንጠይቅ ይገባል።
አዎን! እኔ እጠይቃለሁ። ለሴቶችና ለሕጻናት፣ ለወጣቶችና ለአረጋውያን የምንቆም ነን የምትሉ ማኅበራት ወዴት ናችሁ? አቋማችሁን መግለጽ ቢቀር ቢያንስ ድጋፍ አሰባስቦ አለሁ ከማለት የሸሻችሁ ለምን ነው?
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here