በአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ዕጥረት እና ጥራት መጉደል ምክንያት የማምረት አቅማቸው እየተዳከመ እንደሚገኝ ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች ገለጹ።
መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከውጪ በተለይም ከደቡብ አፍሪካ እና ሩሲያ ይገባ የነበረውን የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት በማሰብ በአሁኑ ጊዜ ወደ 68 የሚጠጉ የአገር ውስጥ አምራች ድርጅቶች የድንጋይ ከሰል የማውጣት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ ።
ኢትዮጵያ በዓመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለሲሚንቶ እና ለሌሎች ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ፋብሪካዎች የድንጋይ ከሰል ከውጭ አገራት ለማስገባት ወጪ ታደርጋለች። ይህም የሆነበት ምክንያት የአገር ውስጥ ከሰል የማመንጨት አቅሙ በአማካይ 4500 ኪሎ ካሎሪ ሲሆን፣ ይህም ደግሞ ሲሚንቶ ለማምረት ከሚያስፈልገው አቀም አነስተኛው እንደሆነ ተገልጿል።
የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዋነኛነት የኃይል ምንጫቸው የድንጋይ ከሰል መሆኑን የኬሚካል እና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱሰትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የሲሚንቶ ዘርፍ ዳይሬከተር ስመኝ ደጉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ኩዩ ሙገር እና ሐበሻ ሲሚንቶ የድንጋይ ከሰል አቅርቦት ችግር እንደገጠማቸው እና ችግሩን ለመፍታት አማራጭ ከሆኑ ቦታዎች ላይ ምርቱን እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑን ስመኝ ጠቁመዋል።
ኩዩ እና ሙገር የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በአሁኑ ሰዓት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተለይም በካማሺ ዞን ጅጋንፎይ ወረዳ ባለው የሠላም ዕጦት እና አለመረጋጋት ምክንያት የድንጋይ ከሰል ለማመላለስ የትራንስፖርት መኪኖች ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ፋብሪካዎቹ ሥራቸውን ለመሥራት እንደተቸገሩ ነው የተገለጸው።
ይህንንም ችግር ለመፍታት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የእጀባ አገልግሎት እንዲያገኙ ከፌደራል ፖሊስ ጋር እየተነጋገሩ አንደሆነ ስመኝ ተናገረዋል።
68 አባላት ያሉት የከሰል አቅራቢዎች ማኅበር ምክትል ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ኤለ ሰኚ፣ ወደ 35 የሚጠጉ በካማሺ ዞን ተሰማርተው የሚገኙ አምራች የማኀበሩ አባላት በጸጥታ ምክንያት ምርት ማቅረብ አለመቻላቸውን ገልጸዋል። የከሰል ምርት ለአየር ከተጋለጠ እንደሚበላሽ የተገለጸ ሲሆን፣ የማኅበሩ አባላት ያመረቱት እስከ 15 ሺሕ ቶን የሚሆን ምርት አደጋ ላይ መውደቁንም ገልጸዋል ።
ፍቃዱ ካሳ (ዶ/ር) የአካባቢ ጥበቃ እና መሰል ዘርፎች ላይ ከ 30 ዓመት በላይ የሥራ ልመድ ያለቸው ሲሆን፣ የድንጋይ ከሰል እንደ ፖላንድና ሩሲያ ባሉ አገራት ከኃይል ማመንጫነት በዘለለ የገቢ ምንጫቸው ነው ይላሉ።
የድንጋይ ከሰል “የሰልፈር መጠኑ የበዛ ከሆነ ጥራቱ የተጓደለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አካባቢ ላይ መጥፎ ጠረን ስለሚያመጣ ምናልባትም የመተንፈሻ አካላት ላይ ጉዳት ሊያስከስት ይችላል’’ ያሉት ፍቃዱ፣ የድንጋይ ከሰል ጥራት ለመጨመር የሚያስችል ማጠቢያ ማሽን ወደ አገር ውስጥ ቢገባ የተሻለ ጥራት ያለው ምርት ለአገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ እንደሚቻል ገልጸዋል።
በአገር ውስጥ ያሉት 13 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዓመት 8.5 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም ሲኖራቸው፣ በገበያ ላይ ከሚፈለገው በ 2.5 ሚሊዮን ቶን ያንሳል። በያዘነው በጀት ዓመትም እስከ 60 በመቶ የሚሆነውን ከሰል በአገር ውስጥ ለመተካት እየተሠራ ነው ተብሏል።
የሲሚንቶ ዕጥረትን ለመፍታት ማስፋፊያ እያደረጉ ከሚገኙ ፋብሪካዎች መካከል ማምረት ከጀመረ ወደ 10 አመት ዕድሜ የተጠጋው ደርባ ሲሚንቶ፣ ባለፈው በጀት ዓመት ከሚያመርተው 5600 ቶን ከሊንከር እና 7500 ቶን ሲሚንቶ አቅሙን በማሳደግና በዕጥፍ ለማምረት የ400 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በድሬደዋ ከተማ የሚገኘው ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ከቻይና ሲሚንት ሊሚትድ ጋር ሽርክና በመፍጠር ከአዲስ አበባ 130 ከሜ ርቀት ላይ በምትገኘው በእንሳሮ ወረዳ በ2.2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በቀን 10000 ቶን የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ እየገነባ ነው።
ቅጽ 3 ቁጥር 155 ጥቅምት 13 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



