ለአነስተኛ የዳቦ ጋጋሪዎች ዱቄት ማቅረብ ሊቆም ነው

Views: 333

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ ኩንታል 1300 ብር ቅናሽ በማድረግ በድጎማ ሲያቀርብ የቆየውን የዳቦ ዱቄት አነስተኛ መጋገሪያ ማሽን ላላቸው ዳቦ ቤቶች ማቅረብ በከፊል አቆመ።

ካለፉት ስድስት ወራት ጀምሮ መተግበር የጀመረው ይህ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠሉን እና በቀን ከሦስት ሺሕ ዳቦ በታች የሚያመርቱ ዳቦ ቤቶች አቅማቸውን ካላሳደጉ ዱቄቱን እንዳማያቀርብላቸው እንደተነገራቸው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የዳቦ ቤት ባለቤቶች ይናገራሉ። የዳቦ ቤቶቹ ባለቤቶች እንደሚሉት፣ መንግሥት የሚያቀርብላቸው የዳቦ ዱቄት ዋጋ በአንድ ኩንታል በ 796 ብር ሲሆን፣ 15 ኩንታል በ 11 ሺሕ 940 ብር በወር ኹለት ጊዜ ይረከቡ እንደነበር ይናገራሉ።

ነገር ግን ከትስስር (መንግሥት የዳቦ ዱቄትን በቅናሽ የሚያስረክባቸው አባላት መደብ) እንዲወጡ ከተደረጉ በኋላ፣ ከግል ነጋዴዎች ላይ አንድ ኩንታል የስንዴ ዱቄት በ ሺሕ 100 ብር ለመግዛት እየተገደዱ መሆኑን እና በዚህም ምክንያት የዳቦ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። ‹‹በተደጋጋሚ መንግሥት ያወጣው መስፈርት በተገቢው ሁኔታ ይገለጽልን በማለት ቅሬታችንን ለክፍለ ከተማው ለማቅረብ ብንሞክርም፤ የሚሰማን አካል አላገኘንም›› ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በስድስት ወራት ብቻ ስድስት መቶ የሚጠጉ አነስተኛ ዳቦ ቤቶች ከትስስር ወጥተዋል ሲሉ የትስስሩ አባል ይናገራሉ።

በቦሌ ክፍለ ከተማ ዳቦ አቅራዎች እንደሚሉት፣ መጋገሪያ ማሽኖቻቸውን በትልልቅ እና ውድ ማሽኖች ለመቀየር አቅም እንደሌላቸውና ይህንንም ለማድረግ ጊዜ ቢጠይቁም የክፍለ ከተማው የንግድ ቢሮ ኃላፊዎች ሊሰሟቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ይናገራሉ። ‹‹ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠን ከትስስር ተቀንሰን ዱቄት ከመንግሥት መረከብ እንዳንችል ተደርገናል›› ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

በየዓመቱ የመጋገርያ ማሽኖቹ ሥራ ላይ እንደሆኑ እና አንድ ግለሰብ ያለውን የማሽን ብዛት የማጣራት ሥራ ይሠራ እንደነበር እንዲሁም ሥራው የተለመደ እንጂ አዲስ እንዳለሆነ የአዲስ አበባ ንግድ እና ኢንዱስትሪ የቢሮው ምክትል ኃላፊ ይናገራሉ። ምክትል ኃላፊው በበኩላቸው ‹‹ለዳቦ አቅራቢዎች ንግድ ቢሮ ባወጣላቸው ዋጋ እና ግራም መሠረት የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ እየሠራን ነበር›› ብለዋል።

በዛም ምክንያት ውሉን በመጣስ ከወጣላቸው ግራም በማውረድ ሲሸጡ የተገኙ ነጋዴዎች ላይ የማሸግ ሥራ ሲሠራ እንደነበር አስታውሰው፤ ‹‹የተቀሩት ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው የማስተካከል ሥራ እየተሠራ ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በተጨማሪም ኃላፊው እንደገለጹት ‹‹በተደጋጋሚ በኅብረተሰቡ የዋጋ ጫና እየተፈጠረባቸው እንደሆነ ቅሬታ እየቀረበ በመሆኑ እና ትስስሩ መንግሥት በድጎማ የዘረጋው ከመሆኑ አንጻር መስፈርቱን እና ውሉን ጥሰው ሲገኙ የማቋረጥ ሥራ ይሠራል›› ብለዋል።

አያይዘውም ውሉን አፍርሰው በተገኙት ላይ ባለፉት ስድስት ወራት 600 የሚደርሱ የዳቦ አከፋፋዮችን ከትስስር እንዲወጡ በማድረግ፣ ሌሎች የማስተላለፍ ሥራ መሥራታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ኃላፊው ዳቦ አቅራቢዎች ሕግን ተከትለው እንዲሠሩ ከማድረግ አኳያ እርምጃው እየተወሰደ መሆኑን ገልጸው፤ ‹‹በአዲስ አበባ ካሉት 8 ሺሕ 400 ዳቦ ቤቶች ውስጥ ከመንግሥት ጋር በትስስር እየሠሩ ያሉት ዳቦ ቤቶች 1 ሺሕ 60 ናቸው›› ብለዋል። የተቀሩት 7 ሺሕ 340 ዳቦ ቤቶች ከግል አቅራቢዎች ላይ በመግዛት ለተጠቃሚ እያቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በመጨሻም የማጣራት ሥራው እንዳላለቀ እና ከዚህ በኋላም ውሉን አፍርሰው በሚገኙት ነጋዴዎች ላይ ውሉን አቋርጦ ለሌላ የማስተላለፉ ሂደት እንደሚቀጥል የንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊው መስፍን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com