ፀሐይ መስፍን ጨርቃ ጨርቅ፣ አደይ ፓድስ ከጀግኒት እና እኔም ያገባኛል ጋር በመተባበር ‹‹አበባ አየሽ ወይ ትምህርት ቤት ትሄጃለሽ ወይ?›› በሚል ዘመቻ፣ በአዲሱ ዓመት የትምህርት ዘመን ለ50 ሺሕ ሴት ተማሪዎች የወር አበባ መቀበያ ቁስ ለማበርከት የመጀመሪያ ዙር 5000ውን ከጥቅምት 1/2014 ጀምሮ ዕደላ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ ዘመቻውን ለማስፈጸም በጋራ ሆነው በሰጡት መግለጫ፣ የጀግኒት ኢትዮጵያ እና የእኔም ያገባኛል በጎ አድራጎት ድርጅቶች በየግላቸው በኢትዮጵያ በአስሩም ክልሎች፣ ገዝተው መጠቀም ለማይችሉ ሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ፓድ ሲያከፋፍሉ የቆዩ ሲሆን፣ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት በጋራ በመቀናጀት ባለፈው 3 ዓመት ዉጤታማ ሥራ ሠርተዋል ነው የተባለው፡፡ በተጨማሪም የአደጋ ፓድስ በጎ አድራጎት ድርጅት የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የንጽህና መጠበቂያውን ለሴቶች በማከፋፈል ሥራ ላይ ተሰማርቶ እየሠራ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ሴት ተማሪዎች በየወሩ የወር አበባ ሲያዩ፣ በመፍራትና በመሳቀቅ ከት/ቤት ይቀራሉ፡፡ በዓመት ከ 30 እስከ 50 ቀን በዚሁ ችግር ምክንያት በትምህርት ገበታቸው አይገኙም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ ከክፍል ወደክፍል መዘዋወር ስለሚያቅታቸው ዕድሜያቸው ለአካለ መጠን ሳይደርስ፣ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ፣ ለትዳር ወይም ወደ ዐረብ አገራት እንደሚሰደዱም ነው የተገለጸው፡፡
ስለዚህ ይህ እንቅስቃሴ ሴት ተማሪዎች ስለወር አበባ ጠቅላላ ግንዛቤ እንዲያገኙ የማስተማሪያ መንገድ እንደሆነ ፣በተጨማሪም ስለ ንጽህና መጠበቂያ ዕውቀት አግኝተው በሕይወታቸው ተግባራዊ አድርገው፣ በትምህርት ትልቅ ቦታ ደርሰው እራሳቸውን ብሎም አገራቸውን እንዲጠቅሙ እና ከሕልማቸው ጋር እንዲገናኙ የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡
የተለያዩ ጥናቶችን መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ የወር አበባ ከሚያዩ 35 ሚሊዮን ሴቶች፣ 22 ሚሊዮን የሚሆኑት የንጽህና መጠበቂያ እንደማይጠቀሙ፣ ብሎም ስለንጽህና መጠበቂያ ፓድ ምንም እንደማያውቁ ተጠቁሟል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014


