ለወትሮው አገራችን እንዲህ በፈረንጅ የዶሮ ዝርያዎች ሳትጥለቀለቅና የዶሮ እና የእንቁላል ዋጋ ጣራ ነክቶ ሕዝቡን ሳያማርር በፊት፣ የሐበሻ ዶሮዎች እንደ አንድ የቤት እንስሳትነት ተቆጥረው ከአብዛኛው የማኅበረሰባችን ክፍል ቤትና ጓዳ ውስጥ አይጠፉም ነበረ።
ከማለዳ አዕዋፋት ጋር የመንጋቱን ብስራት አብሳሪ ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ በሥጋና እንቁላላቸውም ጣፉጭነት እና ጠቃሚ ንጥረ ነገርን አዘልነት ጭምር በብዙዎቻችን ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፈው ዘመናትን አብረውን ዘልቀዋል። የአገረ-ሰብ ዝርያ ዶሮዎች (የሐበሻ ዶሮ)
በተለምዶ የሐበሻ ብለን የምንጠራቸው እኚህ ዶሮዎች፣ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በገጠሩ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ፣ እንደ ሌሎች አገራት የዶሮ ዝርያዎች ኹሉ የእኛው ዝርያ መገለጫዎች ሆነው ከእረጅም ጊዜያት አንስቶ በስፋት ለእርባታና ለምግብነት ይውላሉ።
የማኅበረሰባችን የእርባታ ዘዴ ዘመናዊ አሠራርን ያልተከተለ በመሆኑና የሚረቡት ዶሮዎች ቁጥርም እጅግ አናሳ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የከተማም ሆነ የገጠሩ ነዋሪዎች ዶሮዎቹን ከራስ ፍጆታነት አልፎ የጥቅም ማግኛ መንገድ አድርገው ሳይጠቀሙባቸው ብዙ ጊዜያትን አሳልፈዋል።
አሁን ላይም ከውጪ ከሚመጡት የዶሮ ዝርያዎች ጋር ሲነፃፀሩ በሰውነት መጠናቸው፣ በሚሰጡት እንቁላል አናሳነትና በዋጋቸውም ውድነት ምክንያት ተፈላጊነታቸው እየቀነሰ መምጣቱ የሚታወቅ ነው።
ይህን ተከትሎ ነው እንግዲህ! የዶሮዎችን ምርታማነት ለመጨመር፣ በሽታ የመቋቋም አቅማቸውን ለማጎልበትና ሌሎችም ከዶሮዎች የሚገኙ ጥቅሞችን ከፍ ለማድረግ ታስቦ፣ የአገር ውስጥ ዶሮዎችን ከውጪ ከመጡ የዶሮ ዝርያዎች ጋር የማዳቀሉ ወይንም ሙሉ ለሙሉ የመቀየሩ መላ እንደመፍትሔ ሆኖ የቀረበው።
በዚህም የሐበሻ ዶሮዎች በገበያውም ሆነ በዕርባታው ላይ በድቅል የዶሮ ዝርያዎች እየተተኩ፣ አርቢዎችም ከሐበሻ ዶሮዎቹ ይልቅ ከውጪ ወደሚመጡት የዶሮ ዝርያዎች ፊታቸውን ማዞር ጀመሩ።
“የከዚህ በፊቱ የሐበሻ ዝርያ ዶሮዎችን የዕርባታ ሥርዓት ስናይ ሜዳ ላይ ተለቀው ያገኙትን እየጫሩ የሚኖሩበት ባህላዊ የአረባብ ሥርዓት ነበር የነበረን። ያ ሥርዓት ግን አሁን እያስኬደን አይደለም” የሚሉት በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ ናቸው።
ዶ/ር ፍቅሩ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የዶሮ ምርታማነትን ለማሳደግ ዶሮዎችን ወደቤት ሰብስበን በተሻለ አያያዝና አመጋገብ ማርባት እንዳለብን ያስረዳሉ። እነዚህን በቤት ውስጥ ዘግተን የምናረባቸውን ዶሮዎች ደግሞ እኛው መቀለብ እንዳለብንም አንስተው፣ ከእርባታው ጎን ለጎንም ለቀለብ የሚሆን መኖ የማዘጋጀት ሥራ በእጅጉን ተስፋፍቶ መሠራት እንዳለበት አበክረው ያሳስባሉ።
በአገር ደረጃ በሐበሻ ዶሮዎች ዝርያ ዕርባታና ምርታማነትን መጨመር ላይ ምን እየተሠራ ነው? ስትል አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄም ሚኒስትር ዴኤታው ሲመልሱ፤ በአገረ-ሰብ ዶሮዎች ዝርያ ወይም የሐበሻ ዶሮዎች ላይ በአሁኑ ወቅት የደብረ ዘይት እርሻ ምርምር የተለያዩ ጥናቶች በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
አክለውም፣ የእኛ ዶሮዎች ትልቁ ችግር ቶሎ “ቁፍ” ወይም “ጭር” የማለት እንደሆነ በማንሳት፣ በዓመት 40 እንቁላል ቢበዛም እስከ 60 እንቁላል እንደሚጥሉና የውጪዎቹ ደግሞ በዓመት 300 እና ከዛ በላይ እንቁላሎችን እንደሚሰጡ ይገልፃሉ።
“ስለዚህ ባለሀብቱን ወደ ሐበሻ የዶሮ ዝርያዎች ፊትህን አዙረህ ትንሽ ምርት የሚገኝበት ዘርፍ ላይ ለዕርባታ ተሰማራ ማለት አይቻልም። እኛ ማድረግ የምንችለው የእኛን ዶሮዎች ምርታማነት ማሳደግ ነው። ይህ ደግሞ የእረጅም ጊዜ ምርምር የሚፈልግ ስለሆነ እየተሠራበት ይገኛል” ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ያስረዳሉ።
ሌላው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ እንስሳት ዕርባታ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ዳንኤል ተመስገን ናቸው። እርሳቸውም የሐበሻ ዶሮዎችን ዝርያ በዘመናዊ መልክ ለማርባትና ምርታማነታቸውን ለመጨመር የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆዩም፣ የዶሮዎቹ ዝርያቸው ምርታማነታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
“የተሻሻሉት የዶሮ ዝርያዎች በምንሰጣቸው መኖ እና እንክብካቤ ልክ ምርት መስጠት ይችላሉ። ነገር ግን፣ ለሐበሻ ዶሮዎች የተለያዩ የመኖ አሰጣጥ ዘዴዎችን ብንጠቀምም ሆነ አስፈላጊውን ዓይነት እንክብካቤዎች ሁሉ ብናደርግም የዝርያቸው ሁኔታ ከተለመደው የተወሰነ ምርት በላይ እንድናገኝ አልፈቀደልንም” ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
የሐበሻ ዶሮዎችን ምርታማነት ለማሻሻል አማራጭ ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ መንገዶችንም ዳንኤል ሲያስረዱ፣ ከዝርያዎቹ ውስጥ የተሻለ ምርት የሚሰጡትን መምረጥ፣ ከውጭ ከሚመጡት የዶሮ ዝርያዎች ጋር ማዳቀል፣ ካልሆነም ባላቸው የምርት ደረጃ ማስቀጠል ብቻ መፍትሔ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን በ2010 ባወጣው መረጃ መሰረት፣ በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ60 ነጥብ 04 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዶሮዎች ነበሩ።
አብዛኛው የዶሮ ሀብት ያለው ከፍተኛ የሕዝብ ክምችት ባለባቸው በወይና ደጋውና በደጋማው የአገሪቱ አካባቢ ሲሆን፣ በቆላና እጅግ ደጋማ በሆኑ አካባቢዎች ግን ያለው ሀብት አነስተኛ መሆኑንም መረጃው ጠቁሟል።
የዶሮ ክምችቱ ባለባቸው የአገሪቱ ክፍሎች እያንዳንዱ ቤተሰብ በአማካኝ ከ6 እስከ 8 ዶሮዎች በመያዝ በባህላዊ መንገድ ያረባል።
ታዲያ ከእነዚህም በአገሪቱ ካሉት ዶሮዎች ውስጥ 88 ነጥብ 5 ከመቶ የአገር በቀል ዝርያ፣ 6 ነጥብ 25 ከመቶ የተዳቀሉ ዶሮዎች፣ እንዲሁም 5 ነጥብ 25 ከመቶው በዘመናዊ መልክ የሚረቡት የውጭ አገር ዶሮዎች መሆናቸውን ነው የባለሥልጣኑ መረጃ የሚያስረዳው።
ይህ ከዛሬ 4 ዓመት በፊት የተመዘገበና በአብዛኛው በአርብቶ አደሩ ቤት ያለውን የዶሮ ክምችትት በመቁጠር የተሠራ የአኃዝ መረጃ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ይህ አኃዝ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ እንደሚገኝ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
“የአገረ-ሰብ ዝርያ ዶሮዎች ቁጥር መቀነስ ዋንኛው ምክንያቱ የእኛ ዶሮዎች ምርት ላይ አነስተኛ መሆናቸው ነው። እነዚን የሐበሻ ዶሮዎች እንደ ቢዝነስ ይዞ ትርፋማ መሆን ስለማይቻልም ነው” የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ብርሃኑ ሚሊዮን ናቸው።
በዚህም ምክንያት በዶሮ ዕርባታ ላይ የሚሰማሩ ግለሰቦች ከሐበሻ ዶሮዎች ይልቅ ወደ ፈረንጅ ዶሮዎች ወይንም ተዳቅለው ወደሚመጡ የዶሮዎች ዝርያዎች የማዘንበሉ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ እየታየ እንደሚገኝም ብርሃኑ ያስረዳሉ።
ይህም የውጪዎቹ ቁጥር እየጨመረ የአገረ-ሰብ ዝርያ ዶሮዎች ቁጥር ደግሞ እየቀነሰ እንዲመጣ ማድረጉንም ሥራ አስኪያጁ ጨምረው ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
የሐበሻ ዶሮዎች አሁንም ቢሆን በፍፁም ከገበያው መውጣት የለባቸውም የሚሉት ብርሃኑ፤ “የፈረንጅ ዶሮዎቹን ከውጪ አገር የምናስመጣቸው በመሆኑ፣ አንድ ቀን አትወስዱም ቢሉን አገር ውስጥ እንቁላልና የዶሮ ሥጋ የሚባል ነገር ልናጣ እንችላለን” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።
አክለውም “የእኛ ዶሮዎች ዝርያቸው መራባት የሚችሉ ናቸው። ከውጪ የሚመጡት ግን አንዴ ከወለዱ በኋላ ከዛ በላይ አይወልዱም ይህም ደግሞ ሆን ተብሎ በላኪ አገራት የተሰራ ሥራ ነው” በማለት ይናገራሉ።
የእኛ ዶሮዎችም አሁን ባሉበት ደረጃ ለቤት ውስጥ ፍጆታ እንጂ ለገበያ የሚሆን እንቁላል ብዙ አይሰጡም የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ስለዚህም በተወሰነ ደረጃ ዝርያቸውን ማሻሻልና ምርታማነታቸውን መጨመር የሚቻልበት ሁኔታ ላይ መሥራት እንዳለበት አክለው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማኅበር የተቋቋመበት ዓላማ የአባላቱን ፍላጎትና ጥቅም ማስጠበቅ ነው ያሉት ብርሃኑ፣ የአገረ-ሰብ የዶሮ ዝርያዎች ላይ የምርምር ተቋማት ለሚሰሯቸው ሥራዎች ድጋፍ ከማድረግ ውጪ የዶሮዎቹን ምርታማነት ለመጨመርና አርቢዎች የሐበሻ ዶሮዎችን እንዲያረቡ የማሳመን ምንም ዓይነት ሥራ በማኅበሩና በአባላቶቹ በኩል አለመሠራቱንም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ፣ የእንስሳት እርባታ ላይ ሦስት ማነቆዎች አሉ የሚሉት በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ፣ እነርሱም ዝርያ ማሻሻል፣ የመኖ ሥራ እንዲሁም የእንስሳት ጤና ሥራ መሆናቸውን ይናገራሉ።
እንደ አገር በሁሉም ነገሮች ላይ በጥሩ ደረጃ ላይ እንገኛለን ማለት አይቻልም ያሉት ፍቅሩ፣ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ዝርያ የማሻሻል ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመው፣ በዛው ልክ ደግሞ የመኖ ሥራዎችም መሠራትም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
እንደ መንግሥት ሁኔታዎችን ለኢንቨስትመንት ምቹ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም የሚያስረዱት ሚኒሰትር ዴኤታው፣ የፖሊሲ ድጋፍ፣ የመሬትና የፋይናንስ አቅርቦት ማመቻቸትና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመኖ አቅርቦት ግብዓቶችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መደረጉ ዘርፉን ለማሳደግ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች ውስጥ እንደ ማሳያ የሚጠቀሱ ናቸው ሲሉም ያስረዳሉ።
እንደ አጠቃላይ በእንስሳቱ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፎች ላይ ሥራዎች በመንግሥት ብቻ የሚሠሩ አይደሉም፤ መንግሥት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው ሥራው። ስለዚህም የግሉ ዘርፍ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ገብቶ ዝርያዎቹን የማሳደግ ሥራ መሥራት እንዳለበትም ፍቅሩ ጨምረው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ምን አልባትም ከውጪ የሚገቡት የዶሮ ዝርያዎች በብዛት የአገራችንን የዶሮ እርባታ ዘርፍ እየተቆጣጠሩ በመሆኑ የእኛን የዶሮ ዝርያዎች የማጥፋት ስጋትስ አይኖርም ወይ? በማለት አዲስ ማለዳ ላነሳቸው ጥያቄ ዶ/ር ፍቅሩ “ጠፍተው አይጠፉም፤ የተለያዩ የምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ነው። እነሱ ሲጠናቀቁ የተሻለ ምርት የሚሠጡበት መንገድ ይፈጠራል” የሚል ምላሽን ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ ሥነ ምኅዳር ውስጥ የሚኖሩ 14 የሚሆኑ የአካባቢ የዶሮ ዝርያዎች እንደሚገኙ ጥናቶች የሚያመላክቱ ሲሆን፣ እነዚህ የሐበሻ ዶሮ ዝርያዎች በተለያዩ ከባድ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነውም ሳይበገሩ መኖር መቻላቸውና በሽታን የመቋቋም አቅማቸው ከሌሎች አገራት የዶሮ ዝርያዎች ልዩ እንደሚያደርጋቸው ይነገራል።
የሐበሻ ዶሮዎች ከፈረንጅ ዶሮዎች በተለየ እንቁላላቸው ደማቅ ቢጫ ቀለም ያለው ሥጋቸውም የሚጣፍጥ እንደሆነ ይነገራል። ምክንያት ምንድን ነው? ልዩነትስ አላቸው ወይ? በማለት አዲስ ማለዳ ላነሳችው ጥያቄ ብርሃኑ ሚሊዮን ሲመልሱ፤ “በይዘት ደረጃ እንቁላል እንቁላል ነው። የሐበሻ እንቁላል ከፈረንጁ እንቁላል የተለየ ይዘት የለውም፤ ልዩነቱ የሐበሻ እንቁላል በግራም ደረጃ 40 ግራም አካባቢ ነው፤ የፈረንጁ ደግሞ 60 ግራም ነው ስለዚህ በግራም ደረጃ የሐበሻው አነስተኛ ነው። ስለዚህ በሥጋም አንፃር ልዩነታቸው የትልቅነትና የማነስ ነው” ይላሉ።
ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014



