የ‹አጎዋ› ማስፈራሪያ

0
762

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በተደነገገበት በዚህ ሳምንት አሜሪካ ስታስፈራራ የነበረበትን የአጎዋ አባልነት እግድን ተግባራዊ ማድረጓ ለብዙዎች አስተያየት ምክንያት ሁኗል። ምርታቸውን በነጻ ያለግብር ወደ አሜሪካ እንዲያስገቡ ፈቅዳላቸው ከነበሩ የአፍሪካ አገራት ተርታ እንዳትወጡ ይህን አድርጉ እያለች፣ የዕርዳታ ድጋፍን እጅ ለመጠምዘዣ ተጠቀመችበት ሲሉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን አስተያየት ባገኙት አጋጣሚ ሰንዝረዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ይህን ውሳኔ እንዳንወስን እያለ ማስፈራራት ከጀመረ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን የአገር ውስጥ ጉዳይ እንዲህ በጦዘበት ወቅት መወሰኑ ለማን ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ግራ ገብቶት ለቆየ ግልጽ እንዲሆንለት ያደርጋል በሚል አስተያየት የሰጡ አሉ።
መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ መንገድን በመከተል ለውሳኔው ምላሹን ቢያሳውቅም፣ ሕብረተሰቡ ግን ያን መንገድ መከተል የፈለገ አይመስልም። አንድ አስተያየት ሰጪ፣ እንግሊዝኛ የምትችሉ እባካችሁ ተርጉሙና አድርሱልኝ በማለት “ባቄላ ቀረ…” የሚለውን አገር በቀል ተረት ሰንዝሯል።
አብዛኛው አስተያየት ሰጪ፣ “ጥንቅር ብሎ ይቅር” በማለት እንደውም እንጠቀማለን የሚል ይዘት ያለው ሐሳብ አካፍሏል። “ለምን እስከወዲያኛው አትሰርዘንም፣ የኢትዮጵያውያን ዕጣ ፈንታ በኢትዮጵያውያን እጅ ላይ ነው”፤ “ሠረዘች አልሠረዘች እኛ ፍንክች አንልም፤ጣሊያንም መጥታ ከዳቦ ይልቅ ነጻነትን የመረጥን የአባቶቻችን ልጆች ነን”፤ “ከአጎዋ አድዋ ይበልጥብናል”፤ “ከቻይና ጋር ወደፊት”፤ “እኛ ለማኝ አይደለንም፣ አንፈልግም፣ ብሔራዊ ገቢያችንን በአግባቡ መጠቀም ይበቃናል”፤ “እኛ ጥጋብ እንጂ ረሃብን እንችላለን”፤ “ችግርን እንደሆነ ለምደነዋል፤ ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ?”፤ “ከአሸባሪዎች ጋር የተናበበ ተግባር ነው። ከነገው ዕለት ጀምሮ በ48 ሰዓት ውስጥ የአሜሪካንና አውሮፓ ኢምባሲዎችን በጥፋታቸው ልክ ማባረር ነው። ቀጥታ ጉዳዩ የጥቁሮችና የነጮች ጉዳይ ስለሆነ፣ መላው አፍሪካ ከእነዚህ መርዘኞች ጋር ትብብር እንዲያቆሙ መወትወት አለባቸው” እና የመሳሰሉ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ነበር።
አብዛኛው በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጠ ሰው ለምን እንደተወሰነ እንደገባው በመጥቀስ በዕርዳታ ስም የሚደረግ የማስገደድ ድርጊት እንደሆነና፣ የቀረው ቢቀር የአሜሪካንን መንገድ መቀበል እንደማይገባ ሲናገር ነበር። እስካሁን የተለሳለስነው ጠላት ላለማብዛት እንጂ ወዳጃችን እንዳልሆኑ ስላረጋገጥን ከአሁን በኋላ ያለ ይሉኝታ ወደፊት እንጓዛለን ሲሉም የተደመጡ አሉ። ቁርጡን ካወቅነው ራሳችንን በራሳችን ማዳን እንደሚገባን በሌላም መተማመን እንደሌለብን የሚያመላክቱ መልዕክቶች ተላልፈዋል።
በአጠቃላይ፣ ሕዝቡ ምዕራባውያን እያደረጉ ያሉትን ሴራ የተረዳ በሚመስል መልኩ ፣ “ከፍትፍቱ ፊቱ” በሚል አኳኋን እገዳውን በጸጋ ተቀብሎታል። ውሳኔው ይህን ያህል የገንዘብ ጉዳት ያስከትብብናል፣ ይህን ያህል ስራ አጥም ይፈጥራል እያሉ ግብረ አበሮቻቸውና ዓላማቸውን ሲያራግቡላቸው የነበሩ ኢትዮጵያውን ሐሳባቸው ሳይሳካ ቀርቶ መንግሥት ላይ ጫና በማሳደር ፈንታ ደጋፊ አብዝቶ ወሬው እየደበዘዘ ጠፍቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here