በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከጨርቃጨርቅ ገበያ 45 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለጸ

0
1091

ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር ገቢው የ3 ሚሊዮን ዶላር ዕድገት አሳይቷል

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ በ2014 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት፣ 45 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ 45.78 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው ገቢ 44.67 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህ አፈጻጸምም ከዕቅዱ 97.67 በመቶ ማሳካት መቻሉን ያሳያል።

የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ከባለፈው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር 3.26 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ባንቲሁን ገሰሰ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ልማት ኢንስቲትዩት ያገኘችው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ፣ ምንም እንኳን አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ኹኔታዎች አንጻር በርካታ ችግሮች ቢገጥሙም፣ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጻር በዘንድሮው 7.9 በመቶ ብልጫ ገቢ ተገኝቷል።

የጥጥ ልማት ማስፋትን በተመለከተ በ2013/14 ምርት ዘመን በየክልሉ የሚገኙ ጥጥ አልሚዎች ምን ያህል ማሳ በጥጥ እንደሚሸፍኑና፣ በ2014 በጀት ዓመት ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ምን ያህል ጥጥ ሊቀርብ እንደሚችል በታቀደው መሠረት የተሠራ ሲሆን፤
በዚህም በአፋር፣ ደቡብ፣ ኦሮሚያ እንዲሁም በአማራ ክልል የሚገኙ ጥጥ አልሚ ባለሀብቶች 36 ሺሕ 395 ሔክታር መሬት በጥጥ መሸፈናቸው ተገለጿል። ነገር ግን በበጀት ዓመቱ ታቅዶ የነበረው 42 ሺሕ 672 ሔክታር መሬትን በጥጥ ለመሸፈን ነበር።
እንዲሁም አፋር፣ ደቡብና አማራ ክልሎች በአርሶ አደር 17 ሺሕ 780 ሔክታር መሬት በጥጥ ለመሸፈን አቅደው፣ 16 ሺሕ 133 ሔክታር መሬት በጥጥ መሸፈን እንደቻሉ ከየወረዳዎቹ በተወሰደ መረጃ ለማረጋገጥ መቻሉን ባንቲሁን ጠቁመዋል።
በዚህም መሠረት፣ በአጠቃላይ በምርት ዘመኑ 60 ሺሕ 452 ሔክታር መሬት በጥጥ ይሸፈናል ተብሎ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ከታሰበው ውስጥ 52 ሺሕ 528 ሔክታር መሬት እንደተሸፈነ ተገልጿል።

ኃላፊው አያይዘው የሚናገሩት፣ ምንም እንኳን የ2014 በጀት ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በዚህ መልኩ ተግባራዊ ቢደረግም፣ ካለው የአገሪቱ ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር የተፈለገውን ያህል መሥራት አለመቻሉን ነው። በአጠቃላይ በአፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ወቅታዊ የጦርነት ችግር ሥራቸውን ባቀዱት ልክ እንዳይሠሩ መሰናክል እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

ለአብነትም በሁመራ አካባቢ ጥጥ በአርሶ አደር ደረጃ እንዲለማ ቢደረግም፣ ካለው ውስብስብ ችግር አንጻር እንደ ድሮው በስፋት ለማግኘት አልተቻለም ሲሉ ተናግረዋል። እንዲሁም በሌላ በኩል ሥራ በሚከናወንባቸው አንዳንድ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተፈጠረ የቴክኒክ ችግር የሥራ መቆራረጥ እንደነበር ተጠቁሟል።

በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በመሥራት ላይ በሚገኙ ሰን ሻይን ኢትዮጵያ፣ ውል ቴክስታይል እና አንቴክስ ቴክስታይል ፋብሪካዎች የግራውንዲንግ ትራንስፎርመር በመቃጠሉ ምክንያት ለ4 ተከታታይ ቀናት የኤሌክትሪክ አቅርቦት የተቋረጠባቸው ሲሆን፣ ጉዳዩን አዳማ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በማስረዳትና በቅንጅት በመሥራት በአዲስ ተቀይሮ ኃይል እንዲያገኙ ተደርጓል ተብሏል።

በሌላ በኩል ሥራ ከመፍጠር አኳያ፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲትዩቱ ለ385 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ማስገኘቱን የኮሚዩኒኬሸን ዳይሬክተሩ አመላክተዋል። አያይዘውም ከእነዚህም መካከል 350ዎቹ ወንዶች፣ ቀሪዎቹ 35ቱ ደግሞ ሴቶች እንደሆኑ ነው የጠቆሙት። በዚህም በ2013/14 ምርት ዘመን በጥጥ ልማት ዘርፍ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ታቅዶ የነበረው 500 ዜጎች የሥራ ዕድል መሳካቱ ተጠቁሟል።

እንዲሁም፣ 227 ወንዶች እና 29 ሴቶች በድምሩ 256 ዜጎች በኮንትራት ሥራ የተሠማሩ ሲሆን፣ በጠቅላላው በቋሚ እና ኮንትራት ዘርፍ ለ 641 (577 ወንዶች እና 64 ሴቶች) ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ተብሏል።
በዚህም በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ለባለሙያዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ ለ285 (85 ወንዶችና 2ዐዐ ሴቶች) ዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በጥጥ ልማትና በጨርቃጨርቅ ለ 662 ወንዶች እና 264 ሴቶች፣ በድምሩ ለ 926 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here