ሕንዶች ለላም ትልቅ ክብር እንዳላቸው ይነገራል። ይህ የሆነው ላሞችን ከአምልኮት ጋር ስለሚያያይዟቸው ቢሆንም፣ የሕንድ ላሞች ለጌቶቻቸው የሚሰጡት ጥቅም ግን እምብዛም ነው። ቀድሞ ነገር ሕንዳውያን ሥጋ አይበሉም። የሚሰጡዋቸው ጥቅም የለም ማለት ቢቻልም ላሞች ለሕንዳውያን ቅዱሳን ናቸው። እየተንከባከቡ ይዘዋቸው ይኖራሉ። ይህ የሚያሳየው የሰው ልጅ የሚንከባከበውና ጠብቆ የያዘው ኹሉ ጠቃሚ እንዳልሆነ ነው። እንዲያውም ብዙ ጊዜ ለራሳችን ጥሩ ብለን የያዝነው ነገር በጣም ጎጅና አልባሌ ሆኖ እናገኘዋለን።
አንድ ሰው ኪሱ ውስጥ ለወራት ካስቀመጣቸው ወረቀቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ጥቅም አልባ ሊሆኑ ይችላሉ። ሌላውም ቤቱና ቁም ሳጥኑ ውስጥ ካኖራቸው ቁሳቁሶች ውስጥ የተወሰኑት መወገድ እያለባቸው ቦታ የያዙ እና ለመጭው ጊዜም የማያገለግሉ ሊሆኑ ይችላሉ።
ቁስ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሰዎች አንድን ነገር ለመረዳትና ለማስረዳት የሚከተሉት ዘዴ የማይጠቅም ሲሆን ይታያል። ምናልባትም ቆም ብለው በማየት የያዙትን መንገድ ቢያስወግዱ ከዚያ በቀለለ መንገድ ነገሮችን መረዳትና ማስረዳት ይቻላቸዋል። ስለሆነም ማንም ቢሆን ከራሱ ጋር ይዞት ግን የማይጠቅመውን ነገር በማጤን ማስወገድ ቢችል በመልካም ዕሴት የዳበረ ማኅበረሰብ መገንባት ይቻላል ስትል አዲስ ማለዳ ታምናለች።
በዚህ ወቅት አገራችን ላይ እያየን ያለነው ቀውስ የተፈጠረውም እንደ ማኅበረሰብ ማስወገድ ያለብንን ነገር በጊዜ ማስወገድ ባለመቻላችን ነው።
ግለሰቦች፣ በተለይም ተከታይ አላቸው የሚባሉ የፖለቲካ ሰዎችም እንዲሁ ጠቃሚ ብለው የያዟቸው በርካታ ነገሮች አሏቸው። ምንም ዓይነት ጥቅም የማይሰጥመወገድ ሲኖርበት፣ እየተንከባከቡ ይዘውት የኖረ ተገቢ ያልሆነ የጥላቻ ወይም የተሳሳተ የርዕዮት ዓለም አመለካከት አለ። ይህንም ጥቅም አልባነቱን ተገንዝበው በጊዜ አውጥተው መጣል ሲገባቸው ይባስ ብለው ለተከታዮቻቸው ሲያሸክሙትና ሲያወርሱት እናያለን።
ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ተቋማትና ድርጅቶችም ዕርባና የሌለው በርካታ ነገር አብሯቸው ይኖራል።
በሽብርተኛነት የተፈረጀው ህወሓትም እንደ ሕንዳውያን ላሞች ላይጠቅመው ለዘመናት ይዞት የኖረው አክራሪ ብሔርተኝነትን እንደሆነ መናገር ይቻላል። ህወሓት በ1983 በሄደበት አካሄድ ዛሬም ሥልጣን ለመያዝ ተመሳሳይ መንገድ መከተሉ ለብዙ ዘመን ጠብቆ የያዘውና ያላስወገደው ዕሳቤ መኖሩን ያመላክታል።
ኢትዮጵያ ውስጥ አክራሪ ብሔርተኝነት በብዙዎች ዘንድ ጎልቶ ይንጸባረቃል። በየመድረኩ እየወጡ በሚናገሩት ንግግር፣ በሚጽፉት እና በፈጸሙት ድርጊት ለዘመናት በፍቅርና በመተሳሰብ አብረው የኖሩ ሕዝቦች የጎሪጥ እንዲተያዩና አለመተማመን በውስጣቸው እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላት አብሯቸው የሚኖረው ይህ ልማድ መጥፎ ነውና ሊያስወግዱት አንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥም እንዲሁ ተጠብቀው የተያዙና ከአንዱ ሥርዓት ወደ ሌላ ሥርዓት ሲንከባለሉ የሚኖሩ፣ ምናልባትም መቼ ሊወገዱ እንደሚችል የማይታወቁ ብዙ እንከኖች አሉ። ያለብስለትና ያለ ዕውቀት ዘው ተብሎ መግባትም እስካልተወገድ ድረስ፣ ልምዱ የፖለቲካ ሥርዓቱ እንዳይሻሻል ከማድረጉ ሌላ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰው ምስቅልቅል በቀላሉ ሊቆም አይችልም።
ልንላቀቀው ያልቻልነውና ወቅት እየጠበቅ የሚፈነዳው የዘር ፖለቲካ አሁን ለተፈጠረው ቀውስ መነሻ ነው ቢባል እውነትነቱ የጎላ በመሆኑ፣ አገራችን ይህን ዕሳቤ ንቆ በመተው ከዚህ አዙሪት ውስጥ መውጣት ይገባታል።
ቻይናዎች፣ ‹‹ከኃያ ዓመት በኋላ ምርጥ ዛፍ ለመሆን ዛሬ ራስህን ትከል›› የሚል አባባል አላቸው። ከዓመታት በኋላ የተሻለ ንቃተ-ሕሊና ያለው፣ መልካምና መጥፎውን ለይቶ የሚያውቅ ማኅበረሰብና ጠንካራ የሆነች አገር ለመመስረት የሚወገደውን በማስወገድ ከአሁኑ ቆራጥ የሆነ እርምጃ መውሰድ መጀመር ይገባል።
አዲስ ማለዳ ኢትዮጵያ እንደ አገር ተከብራና ሠላም የሰፈነባት አገር ሆና እንድትቀጥል ከግለሰቦች ጀምሮ ተቋማትና ድርጅቶች ድረስ አብረዋቸው እየኖሩ ግን ደግሞ የማይጠቅሟቸውን ሐሳቦች፣ መርሃ ግብሮች፣ ቁሳቁሶች እና መሰል ጉዳዮችን ማስወገድ አለባቸው ብላ በጽኑ ታምናለች።
መንግሥትም እንደ መልካም ልማድ የያዘውን አጉል ባህሪውን እንዲያስወግድ መሥራት ይኖርበታል። ብዙ ጊዜ አሁን ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ በመንግሥት ሰፊ ጥቃት እንዲሰነዘርበት ክፍተት ሲፈጥር መታየቱ ይነገራል። አንዳንዴ ይህን ድክመቱን ሲናገር ሌላ ጊዜ ደግሞ በድል እናጠናቅቃለን በማለት ሕዝቡ በሒደቱ ዕምነት እንዲያጣና በፍርሀት እንዲሸበር መደረጉ ይታወቃል። በመሆኑም እንዲህ ዓይነቱ ችግር ቀድሞ ባይኖርና ባለፉት ሦስት ዐስርት ዓመታት ገደማ በነበረው ሥርዓት ውስጥ ከነበሩ አባዜዎች መላቀቅ ቢቻል ኖሮ፣ ጦርነቱ እንኳንስ ሸዋ ሊደርስ መቀሌም በድጋሜ የመከሰት ዕድል አይኖረውም።
መቀሌንና የክልሉን አብዛኛው ቦታዎች በአጭር ቀን መቆጣጠር ቢቻልም፣ በመዘናጋትና ጠላትን አሳንሶ በማየት ቡድኑ በድጋሜ እንዲደራጅና ጥፋት እንዲያደርስ መፍቀድ አይገባም ነበር። በመንግሥት በኩል ችግሩ በዚህ ብቻ ባለማብቃቱ ህወሓት ከሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአማራና አፋር ክልሎች ዘግናኝ የሆነ የንጹኃን ዕልቂትና አስከፊ የንብረት ውድመት እንዲያደርስ ሆኗል። እስከ መሀል አገር ድረስ ሰተት ብሎ እንዲገባ፣ የታየውንና የተሰማውን ችግርም እንዲፈጠር፣ የውጭ ኃይሎችም በማያገባቸው ሉዓላዊት በሆነች አገር የውስጥ ጉዳይ ገብተው እንዲፈተፍቱ ዕድል የተሰጣቸው ጠላት ላይ የተያዘው አቋም ጠንካራ ባለመሆኑና ከማጥቃት ይልቅ በመከላከል ብቻ ለረዥም ጊዜ መቆየት ስለተመረጠ ነው።
አሁንም ቢሆን መንግሥት ሆነ ለአገር እሰራለሁ የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መተውና ማቋረጥ ያለባቸውን ነገሮች ለይተው፣ ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ከመሯሯጥ ይልቅ ሳይፈጠሩና ጉዳት ሳያስከትሉ በፊት የመከላከል አዲስ ልማድ ተፈጥሮ ማየት ይኖርብናል።
በየቦታው የሚፈናቀሉና የሚገደሉ ዜጎችንም አስመልክቶ በመንግሥት በኩል የኢትዮጵያን ሠላም እና ዕድገት በማይፈልጉ የጥፋት ኃይሎች እየተፈፀመ ነው ከማለትና ከማለሳለስ አጉል ልማድ ተላቆ፣ በተለየ አስተዳደራዊ ዘዴ በየጊዜው የሚሞቱ ንጹኃንን መታደግ ይገባዋል። ይህን ለማድረግም መጀመሪያ እንደ መንግሥት የቆዩ ልማዶችን መተውና ቀልጣፋ የሆኑ አዳዲስ አሠራሮችን መከተል ያዋጣል።
እንደ መንግሥት ችግሮችን ቀድሞ ከመከላክል አንጻር እንደ አብነት ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰው ጥቃት ማንሳት ይቻላል። ህወሓት ጥቃቱን የሠነዘረው ወታደሩ ባላሰበበት እና ባልተዘጋጀበት ወቅት መሆኑ ይነገራል። ነገር ግን፣ ህወሓት ድርጊቱን የፈጸመው ሳያስብበትና ሳይዘጋጅበት በድንገት አለመሆኑ ደግሞ በመንግሥት ላይ ብዙ ቅሬታዎችን ያስነሳል። ይህም የደኅንነት ተቋም ያላት አገር እንዴት አንድ ቡድን ታላቅ በሆነ የአገር ሠራዊት ላይ ጥቃት ሊፈጽም መሆኑን ቀድሞ በማወቅ ጥቃቱን መከላከል አልተቻለም የሚል ነው።
ከዚያ በኋላም በየቦታው እየተንቀሳቀሰ ጥቃት ሊፈጽም መሆኑን ተረድቶ ማስቆም አለመቻሉ መወገድ የነበረበት ድክመት ነው። አሁንም የዘገየም ቢሆን ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሸጋገሩ ይበል የሚያሰኝ ሲሆን፣ መወገድ ያለባቸውን አሠራሮችን በማስወገድ ህወሓት የሚያደርሰውን ጥፋት በሌላ ዘመቻ እንዲሰልሰው መደረግ የለበትም።
እንደግለሰብም ከኹላችንም ጋር እየኖሩ የማይጠቅሙን በርካታ ነገሮች ስላሉ፣ ለሠላማዊና ስኬታማ ኑሮ፣ እንዲሁም ለተረጋጋችና ለበለጸገች ኢትዮጵያ ሲባል አላስፈላጊ ነገሮች መወገድ አለባቸው ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014



