ታደለ ደርሰህ ግርማ ይባላሉ፡፡ የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዲሞክራሲ(ቪኢኮድ) መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ላለፉት 19 ዓመታት ሠርተዋል፡፡ የዓለም የሠላምና የመልካም ሥነ-ምግባር አምባሳደር የሆኑት እኚህ አንጋፋ የሠብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ፣ በደርግ ዘመን የአየር ኃይል ባልደረባ ከመሆን አንስቶ እስካሁን አገራቸውን በተለያየ መስክ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በአስተዳደርና ሥነ- አመራር፣ በሥርዓተ ፆታ፣ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ እንዲሁም ከምርጫ ጋር በተገኛኘ ሥልጠና በመስጠት የሚታወቁት ታደለ፣ ከተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን፣ እንዲሁም ምርጫን መታዘብን የመሳሰሉ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ ስለወቅታዊው የአገራችን ኹኔታ፣ የምዕራባውያን ተጽዕኖና በሲቪክ ማኅበራት ላይ ስለሚያመጣው ጫና፣ እንዲሁም ስለአጠቃላይ ጦርነቱ ከአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
አሁን ካሉበት የሙያ ዘርፍ በፊት የት የት ሠርተዋል?
ቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዲሞክራሲ(ቪኢኮድ)ን አምስት ሆነን ነው ከ19 ዓመት በፊት የመሠረትነው። ከዛ በፊት፣ በ1983 የመጀመሪያው ሲቪክ ድርጅት አቡጊዳ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኮንግረስ በአብርሃም አበበ ሲመሰረት፣ ድርጅቱ ውስጥ የሥነ-ዜጋ ትምህርት አስተባባሪና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኜ ሠርቻለሁ። ከዛ በኋላም በተለያዩ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ሠርቻለሁ። በኤንባሲዎችና በሴንትራል ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ውስጥም አገልግያለሁ። በቀድሞ መንግሥትም የአየር ኃይል ባልደረባ ነበርኩ። በኢትዮጵያ አየር መንገድም ለኹለት ዓመት ሠርቻለሁ።
የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዲሞክራሲ(ቪኢኮድ) እንዴት እንደተቋቋመ በአጭሩ ያስተዋውቁን?
ድርጅቱ የተመሠረተው በ1995 ነው። ለምሥረታው ምክንያት የሆነው “የምሁሩ ሚና ምን ይሁን” የሚለው የአብርሃም አበበ ጥናታዊ ጽሑፍ ነው። በጽሑፋቸው የደርግ ምሁራንን፣ የአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ምሁራንን ዳሰዋል። እሳቸው አቡጊዳ የተሰኘው የመጀመሪያው የሲቪክ ድርጅት መሥራች ናቸው። ከእሳቸው በፊት የነበሩት የልማት ድርጅቶች ነበሩ።
ሲቪክ ማኅበራት ከ1983 በኋላ ነው የተጀመሩት። በ1984 ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም የመሠረቱት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ውስጥ በመደበኝነት ባይሆንም ከበርካታ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ጋር አብሬ ሠርቻለሁ።
ለቪኢኮድ መመሥረት ትልቁ ሥራ በ1992 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ዳዊት ዮሐንስ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ምርጫ መታዘብ አይችሉም፣ አገር ውስጥ ያሉ የሲቪክ ማኅበረሰባት ይችላሉ ብለው ሲከለክሉ፣ አብርሃም አበበ መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ያደረጉ ኤንባሲዎችን ሰብስበው፣ “እኛ ትምህርት ስለምንሰጥና ስለምንታዘብ አብራችሁን ሥሩ” ብለው ባደረጉት ውይይት፣ በአንድ ቀን ውስጥ በዛን ጊዜ 6 ሚሊዮን ብር ቃል ተገብቶላቸው ነበር። በዚህ ተግባራቸው በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበሩት ህወሓቶች ስለተናደዱ አቡጊዳን ምሽቱን ለመዝጋት ፈልገው ነበር። ድርጅቱን የሚያጠለሽ ምሁራዊ ያልሆነ ጥናት እንዲቀርብ አድርገው በመፈረጅ እንዲዘጋ አድርገዋል። በነጋታው ወረደወልድ ወልዴ የሚባሉ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩ ሰው የተዘጋው ሳይበቃ፣ መቀጣጫ እንዲሆን ንብረቱን አስወርሰው ዜና አስነገሩ። በዛን ጊዜ በቁጭት ነው ቪኢኮድ የተመሠረተው። በወቅቱ አዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ የነበርን ልጆች ተሰብስበን ነው ያቋቋምነው።
በህወሓት ዘመን በርካታ የሲቪክ ማኅበራት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደነበር ይነገራል። አፋኝ የተባለ ሕግን እስከማውጣት የደረሰ ነበር የሚባለውን ሒደት እንዴት ያዩት ነበር?
በወቅቱ አፋኙ ሕግ መውጣት እንዳልነበረበት ብዙ ተናግረን ነበር። በተለይ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሠሩ ይፈለግ ነበር። ይህ በይበልጥ የሆነው ከ1997 ወዲህ ነው። በወቅቱ ኢ 95 የሚል ድርጅት አቋቁመን በአብርሃም አበበ መሪነት በመላ አገሪቱ የሥነ-ዜጋና የሥነ ምርጫ ትምህርት ከሰጠን በኋላ የምርጫ ሒደቱን ታዝበናል።
በ1997፣ 25 የምንሆን ሲቪክ ማኅበራት ተደራጅተን የምርጫ ትምህርት ለመስጠት በጠየቅነው መሠረት ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በዩ. ኤን. ዲ. ፒ. አማካይነት የገንዘብ ድጋፍ አድርገውልን፣ በመላ አገሪቱ ትምህርት ሠጥተን የትዝብታችንን ውጤት በወቅቱ ለመንግሥት፣ ለብዙኃን መገናኛና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳውቀን ነበር። በዚህ የተደናገጠው መንግሥት ምርጫውን በፀጋ ከመቀበል ይልቅ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅን በማወጅ፣ የተወዳደሩትንም በማስጠንቀቅ፣ ቆይቶም ያሸነፉትን እንደሚታወቀው እስር ቤት ከቷቸዋል።
ፓርላማ ገብተው ሥልጣን በመያዝ ፈንታ ያሸነፉት እስርቤት፣ የተሸነፉት ደግሞ ከሥልጣን ሳይወርዱ እዛው ሥልጣን ላይ ቆይተዋል። ቀጥለው የፀረ ሽብር ሕግ በማውጣት አፋኝ ሕጎችን ወደማውጣቱ ሔደው ነበር። ከእነዚህ መካከል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሕግ ነው። በዐዋጅ ቁጥር 621/2001 አፋኝ የሆነና ሰውሰው የማይሸት ሕግ ወጥቷል። በዚህ ምክንያት በርካታ ሲቪክ ማኅበረሰባት እንዳይሠሩ ነው የተደረገው።
ዐዋጁ ከመውጣቱና ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ኹለት ጊዜ ስብሰባ ጠርተውን ነበር። ከሰጡን ደቂቃ አንጻር እንድንሰማ እንጂ ሊሰሙን አልነበረም የተጠራነው። እኔ በጊዜው ባገኘሁት ዕድል፣ “እኛ ከ5ና10 በመቶ በላይ ገንዘብ ከውጭ አግኝተን የውጭ አገር ድርጅቶች ከተባልን፣ መንግሥት ከበጀቱ 50 እና 60 በመቶውን ከውጭ እያመጣ የውጭ መንግሥት ሊባል ነው ወይ ?” የሚል ነበር አንዱ ጥያቄዬ። ልመናን ጠንክሮ በመሥራት እንጅ በዐዋጅ ማጥፋት አይቻልም ብዬ ተናግሬ፣ ሦስት ዓይነት ለማኞች እንዳሉ አብራርቼ ነበር። ኹለቱ የሠለጠኑ፣ አንዱ ያልሠለጠነ ነው በማለት፣ ቀዳሚው መንግሥት እንደሆነና ቀጣዩ ደግሞ በተለያየ ሰበብ የሚለምነው የሲቪክ ማኅበረሰቡ ነው። ሦስተኞቹ ራሳቸውን ወክለው በየዕምነት ተቋማቱ የሚለምኑት ናቸው። የሚያሳዝነው ትልቁ ለማኝ ትንሹን አለመውደዱ ነው። ለምን ይህ ይሆናል? ብዬ ነበር የጠየቅኳቸው። ከትከት ብለው ስቀው፣ “ከጓደኞቼ ጋር ተማክሬ ልመለስ” ብለው ነው ወደ ቤተመንግሥት የተመለሱት። ይህ በሆነ በሳምንቱ ነበር ዐዋጁ የጸደቀው።
በወቅቱ ከ50 በላይ የምንሆን የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት በተለያየ ጉዳዮች ላይ ሥራ እንሠራ ነበር። ዐዋጁ ሲፀድቅ ግን ሆድን የሚያክል ጠላት ስለሌለ፣ ኹሉም ማለት ይቻላል ወደ ልማት ሥራ ዞሩ። መኖር ስለነበረባቸው አይፈረድባቸውም። ውኃ ጉድጓድ የሚቆፍሩ፣ ስንዴ የሚያድሉ፣ ድልድይ የሚሸሩ መሆናቸውም አንዱ የሰብዓዊ መብት እንዲሟላ የሚያደርግ በመሆኑ ችግር አልነበረውም።
በዲሞክራሲ፣ በሰብዓዊ መብትና በመልካም አስተዳደር ላይ ሥራ የሚሠራ ግን ከ10 በመቶ በላይ ገንዘብ ከውጭ ማግኘት አይችልም ተባለ። በዚህ ምክንያት የቀረነው ከአራት አንበልጥም ነበር። እኛን ጨምሮ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርና የጠበቆች ማኅበር ነን ቀርተን የነበርነው። አሁን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ሕጉ በዐዋጅ ቁጥር 1113/2011 ተሻሽሎ የሲቪክ ማኅበረሰባት በአንጻራዊነት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግሥት ወደሥልጣን ሲመጣ፣ በቅድሚያ ካሻሻላቸው ዐዋጆች መካከል ይህ የሲቪክ ማኅበረሰባትን የተመለከተውን አንዱ መሆኑ ይታወቃል። አሁን መንግሥት ላይ ተቋማቱ ምዕራባውያንን ተከትለው ከሚያደርሱት ጫና ጋር ሲያነጻጽሩት ለውጡን እንዴት ያዩታል?
ምዕራባውያን ከድሮ ጀምሮ የራሳቸው የሆነ ዓላማ አላቸው። እነሱ ሲቪክ ማኅበረሰብንም ሆነ አንድ አገርን የሚረዱት ከራሳቸው ዕይታ አንፃር ነው። አላማቸው ተቋማቱን ለማገዝም ሆነ አገርን ለመርዳት አይደለም።
ሲቪክ ማኅበሩን በተመለከተ ዶክተር ዐቢይ ወደስልጣን ሲመጡ የሕዝብ ጥያቄ ነበር። በለውጡ እሳቸው ከፍ ብለው ይምጡ እንጂ፣ የ110 ሚሊየን ሕዝብ ጥያቄ ነበር። ምክንያም 27 ዓመቱ ሙሉ የውሸት ፌዴራሊዝም ስለነበር ማንም ሰው ደስተኛ አልነበረም። በዘመኑ በርካቶች ተገለዋል፤ ታስረዋል፤ ተሰደዋል። ከሲቪክ ማኅበራት ውስጥም ብዙዎች ታስረዋል። ለምሳሌ፣ እነዶክተር ዳንኤል በቀለ ሠላማዊ ትግል ስላካሄዱ ነው በሐሰት ምስክር ለኹለት ዓመት ዕስር የተዳረጉት። እኛም 13 ቀን ይሁን እንጂ ሊያስጠይቅ በማይችል ጉዳይ ታስረን ነበር። ይህን ያደርጉ የነበረው፣ ትንሽ ነቃ ያሉ ናቸው ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ብለው ስለሚጠረጥሩ ነው። አፋኝ ሕጉም የወጣው ብዙ የሲቪክ ማኅበራት ሠራተኞችን አንገት ለማስደፋት ነበር።
የተሻሻለው ዐዋጅ ማንን ነው የጠቀመው?
በአዲሱ አዋጅ ማንም ሰው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ማቋቋም ይችላል። የገንዘብ ክልከላም የለበትም። የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራ መሥራትም ይቻላል። አገርንም ወክሎ ያመኑበትን ጉዳይ ማራመድ ይቻላል። በነዚህ ምክንያቶች አሁን የተሻሉ ነገሮች አሉ። ስለዲሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና ሰብዓዊ መብት ለማስተማር የሚያግድ ነገር የለም። የራስ ድክመት ወይም የፋይናንስ ዕጥረት ካልሆነ በስተቀር አሁን ምንም የሚገድብ ነገር የለም።
የገንዘብ ድጋፍ ችግር አሁንም አለ። ይህ የሆነው የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ዶክተር ዐቢይ ወደሥልጣን ሲመጡ ምዕራባውያን ግራ ተጋብተው ስለነበር ነው። በመጀመሪያ ደግፈዋቸው የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ አዝማሚያቸውን ሲያዩ፣ በተለይ አፍሪካውያንን ለማቀራረብ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ሲያዩ ምዕራባውያኑ በመጥፎ ዐይን ማየት ጀምረዋል። በዚህ ምክንያት ለሲቪክ ማኅበረሰባት ያደርጉት የነበሩትን ድጋፍ አልቀጠሉበትም። ለምሳሌ 6ተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሲደረግ ከነበረው ልምድ አኳያ የነበረው የፋይናንስ ድጋፍ በጣም አነስተኛ ነበር።
ስለምርጫ ለማስተማር የነበረው ዕቅዳችን እንደተፈለገው እንዳይሳካ አጭር ጊዜ ሲቀረው ነው ድጋፍ የተለቀቀው። በዘንድሮው ምርጫ ከ3 ሺሕ 500 ሲቪክ ማኅበራት ውስጥ ትምህርቱን እንዲሰጡ 120ዎቹ ብቻ ነበር የተመረጡት። ከዛ ውስጥ ገንዘብ አግኝተው የተንቀሳቀሱት ከ16 አይበልጡም። ለትምህርት የነበረው ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ ለመታዘብ የነበረው እንቅስቃሴ እንዲጀመር የተደረገውም አጭር ጊዜ ሲቀር ነበር። ይህ ቢሆንም ግን፣ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ሕዝቡ በምርጫው ላይ መሳተፉን መታዘብ ችለናል። ምርጫው እንከን የለሽ ነው ብለን መናገር ባንችልም፣ ዲሞክራሲ ተተክሏል ብለን መናገር እንችላለን። በኹለት ክልሎች በ27 ከተሞች ተገኝቼ ስለምርጫው ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ፣ ሒደቱንም በመከታተል ካጋጠሙ አነስተኛ እንከኖች ውጭ በአብዛኛው የተሻለ ነበር ብዬ መናገር እችላለሁ። ሲቪል ማኅበረሰቦችም የሚጠበቅባቸውን ያህል መሥራት ባይችሉም፣ ዐዋጁ በመሻሻሉ የተሻለ ሠርተዋል ማለት ይቻላል።
ሲቪል ማኅበር ሲቋቋም ወገንተኛነቱ ለዲሞክራሲ፣ ለሰብዓዊ መብትና ለሕዝብ ነው። የማንም ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ መሆን የለበትም። ዓላማቸው ሞጋች ሕብረተሰብን መፍጠር ነው።
ቀደም ብለው ሆድ ትልቁ ጠላት ስለሆነ ማኅበራቱ ለመኖር ሲሉ ዓላማቸውን ቀይረው እንደነበር ነግረውናል። አሁንስ የምዕራባውያን ድጋፍ እንዳይቋረጥባቸው ሲሉ የእነሱን ዓላማ ለማስፈጸም ከአገር በተቃራኒው ሊሰለፉ አይችሉም?
ይህ የማይጠረጠር ጉዳይ ነው። እንዲህ የሚያደርጉ አሉም፣ ይኖራሉም። ትልቁ ችግርም ይህ ነው። ሲቪክ ማኅበራት ተለጣፊ መሆን የለባቸውም። ይህ በሒደት የሚጣራ ጉዳይ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። የኢትዮጵያ ትልቁ በሽታ አስመሳይነትና አድርባይነት ነው። በአገርና በሕዝብ የሚነግዱ አሉ። ኹላችንም የምንበላው አንድ እንጀራ ሆኖ ሳለ አገርንና ወገንን ለገንዘብ ብሎ መሸጥ ከወንጀሎች ኹሉ የከፋው ነው። ሰው ወደሲቪክ ማኅበረሰብ የሚገባው ቀዳዳ ኪሱን ለመሙላት ወይም አገሩን ለመሰለል ከሆነ በጣም ተሳስቷል። እንዲህ ዓይነት ተግባር የተጠናወታቸው የሲቪል ማኅበራት ከተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል። በሕግ ጭምር ሊጠየቁ ይገባል። ህወሓቶች በሕግ መጠየቅ እንደሚገባቸው ኹሉ፣ በየሴክተሩ የተሰገሰጉ ደጋፊዎቻቸው ጭምር ሊጠየቁ ይገባል። ብልጽግና የተመረጠው አገር እንዲጠብቅና ዜጋውን ከሕገ-ወጥ ድርጊት እንዲከላከል ነው።
ጦርነቱን በተመለከተ የሲቪክ ማኅበረሰቡ ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ወደጦርነቱ ስንመጣ ህወሓቶች ወይም ተላላኪዎቻቸው እንደሚያወሩት ሳይሆን አገርን ለማፍረስ፣ ሕዝቡን ለማዋረድ፣ ለመግደልና ለመዝረፍ የመጣ ጦርነት መሆኑ ይታወቃል። ይህ የእርስበርስ ጦርነት አይደለም። ጦርነቱ በአፍሪካውያን ላይ የታለመ ነው። አፍሪካውያን አንድ ሆነው ከኢትዮጵያ ጎን ሊቆሙ ይገባል። ሲቪክ ማኅበረሰቡም ሕብረተሰቡን የማገልገል ዓላማቸውን በአግባቡ መወጣት መቻል አለባቸው።
ጦርነቱ በብልጽግና ላይ የታወጀ አይደለም። ከሕዝቡ ምንም ጸብ የለንም እያሉ መጥተው፣ ማንን እንደደፈሩ፣ የማንን ንብረት እንዳወደሙና ከብት ሳይቀር እንደጨረሱ ይታወቃል። የባለሥልጣናቱን ሚስትና ልጆችን አይደለም የደፈሩት። ባልን አስረው እፊቱ ሚስቱን በደቦ የደፈሩት ሕዝቡን አንነካም እያሉ ነው። ዓላማቸው ኢትዮጵያን አፍርሰው ትግራይ ሪፐብሊክን ለመመሥረት ነበር። ንብረት እየዘረፉ መውሰዳቸው ሐሳባቸውን ያመለክታል።
መከላከያ ትግራይን ለቆ ከወጣ ጀምሮ ጦርነቱ እየተስፋፋ ሸዋ ደርሷል። ሰሞኑን የማጥቃት ዕርምጃ እስኪጀመር ድረስ የመንግሥት አካሄድ ውጤታማ አልነበረም። የአመራር ሥልጠና ከመስጠታችሁ አኳያ መንግሥት ከስህተቱ ተምሮ ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?
በመጀመሪያ ከጦርነቱ በስተጀርባ ህወሓትን የሚጋልቡት መኖራቸውን መረዳት ያስፈልጋል። ምዕራባውያን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንዲቆይ አይፈልጉም። የህወሓትን መሠሪነትን እያወቁ ነው እንደሚደግፉት በግልጽ እየታየ ያለው። እነሱን ለመጥቀም ሲሉ ምን ያህል የውሸት ፕሮፓጋንዳ በሚዲያዎቻቸው እንደሚያስተላልፉ እያየነው ነው።
ይህ ማለት ግን ከመንግሥት ወገን ስህተት አልነበረም ማለት አይደለም። ለምሳሌ፣ የጥሞና ጊዜ ብሎ መንግሥት ትግራይን ለቆ ሲወጣ ስህተት ተሰርቷል። ጊዜያዊ አስተዳደር ተብሎ የተለያዩ ሰዎች ቢሾሙም፣ በታችኛው እርከን የነበሩ የህወሓት ሰዎች በነበሩበት እንዲቆዩ ነበር የተደረገው። በወረዳ ደረጃ የነበሩት ስላልተነኩ ህወሓት አልተነካም ነበር። የአመራሩን ቦታ ለትግራይ ልጆች ቢሰጥም፣ የሠላም ማስከበሩን ሒደት መከላከያ ነበር ማከናወን የነበረበት። መከላከያው ለቆ መውጣት አልነበረበትም፤ እዛው ከቦ ነበር መቆየት የነበረበት።
ሌላው መከላከያ ሠራዊት ለረጅም ጊዜ መከላከል ላይ ብቻ በማተኮር አለማጥቃቱ ስህተት ነበር። እንደውም አንዳንድ ቦታዎች ላይ ያለምንም ተኩስ ከተሞችን ለቆ ሲወጣ ታይቷል። ተመሳሳይ መንገድ በተደጋጋሚ እየተጠቀመ ህወሓት ከተሞችን ሲቆጣጠር እስከቅርብ ከስህተት መማር አልተቻለም ነበር። መንግሥት ያሰለጠናቸውን ወጣቶች ያለትጥቅ ማስቀመጥም አልነበረበትም። መዋጋት ለፈለገ በነፍስ ወከፍ ማደል ባይቻል እንኳን የቡድን መሣሪያ መንግሥት ማቅረብ መቻል ነበረበት።
በሌላ በኩል፣ ጦርነት ፕሮፓጋንዳ ነው። ህወሓቶች የኢትዮጵያን መንግሥት በዚህ ረገድ በልጠው መገኘታቸው መካድ የለበትም። ህወሓት የሚታወቀው በመሠሪና በተንኮል ሥራው ስለሆነ የ27 ዓመት ልምዱ ረድቶታል። በሴራ ነው እንጂ ፊት ለፊት ተዋግተው ያሸነፉበት ቦታ የለም።
አሁንም ቢሆን ጊዜው ስላልመሸ መደረግ ያለበት ከስህተት መማር ነው። ከደሴው ተምሮ አዲስ አበባ ላይ እየተደረገ ያለው ፍተሻ ተገቢ ነው። ይህ ቢሆንም አንዳንድ ቦታዎች ላይ አመራሮችም ላይ ችግር ይታያል።
ጥፋት ያጠፉ ወታደራዊም ሆኑ የሲቪል አመራሮች ላይ፣ እንዲሁም የብቃት ማነስ ችግር የታየባቸው ላይ የሚወሰድ ዕርምጃ ምን መሆን አለበት?
ያጠፋ መጠየቅ አለበት። ሰውን መሾም ብቻ አይደለም፣ የሚሾመውን ማንነት ማወቅና ምን እየሠራ እንዳለ መከታተልም አስፈላጊ ነው። አሁንም ድረስ የህወሓት ደጋፊዎች በትልልቅ የኋላፊነት ቦታ ተቀምጠው ይገኛሉ። መንግሥት ጊዜው እስኪደርስ መግለጽ ያልፈለገው ነገር ያለ ይመስለኛል። የተያዙ እንዳሉ ሰምተናል። ዕርምጃ የተወሰደባቸውን ጨምሮ ለወደፊት የሚወሰንባቸውንም እናውቃለን የሚል ተስፋ አለኝ። ለውጥ ከተባለ ከሥር ነው መሆን ያለበት። ህወሓትን ከ4ኪሎ ቤተመንግሥት ስላስወጣህ ብቻ አይኖሩም ማለት አይደለም።
መንግሥት ከደርግ ስህተት ምን መማር አለበት ብለው ያስባሉ?
ለብዙ ሰው ግልጽ ያልሆነ ስለፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም የሚነገር አለ። ፈርጥጠው አገር ጥለው ወጡ ይባል የነበረው አሁን ግልጽ ሁኗል። በወቅቱ አማራጭ ስላልነበራቸው ነው ወጥተው የቀሩት። ምጽዋና አሰብ ሲያዝባቸው ከቻይና የገዙትን መሣሪያ በጅቡቲ ለማስገባት ጅቡቲ ሔደው ሲነጋገሩ ድሬዳዋ ሦስተኛው አየር ምድብ ውስጥ ነበርኩኝ። በዛ በኩል ያለው ሁኔታ አስተማማኝ ስላልሆነላቸው በኬንያ ለመሞከር ነበር ወደዛ የተጓዙት። ዳንኤል አራክሞይን ሞምባሳ ወደብን እንጠቀም ብለው ለማነጋገር በምስጢር ለመሄድ ሞክረዋል። ብላቴን ያሉ ተማሪዎችን ለማነቃቃት በሚል አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ ለአስቸኳይ ጉዳይ ወደ ኬንያ እንዲበር ነበር የተደረገው።
ኬንያ ሲገቡ ሲአይኤ የሠራው ሥራ ነው ያስቀራቸው። ለፕሬዝዳንት አራክሞይ ደውሎ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ከሥልጣን ስለወረደ ከአሁን በኋላ ስለማይመለስ አውሮፕላን አዘጋጅተህ ወደ ዙምባብዌ ላከው፣ ወጪውን አሜሪካ በካናዳ መንግሥት በኩል ትፈጽማለች ብለው ነው ያስገደዱዋቸው። በአንድ ስልክ ነው የኢትዮጵያን ታሪክ የቀየሩት። ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ጆሞ ኬንያታ አየር ማረፊያ ሆነው ዜናውን ሲሰሙ በንዴት አንድ ፓኮ ሲጋራ ነው ያጨሱት።
ምዕራባውያኑ ዛሬ ይህን ዶክተር ዐቢይ ላይ ለመድገም የማይሞክሩበት ምንም ምክንያት የለም። የእነሱን ሴራም ሆነ የመንግሥቱ ኃይለማሪያምን መውጣት ሕዝቡ አሁን አሁን ነው መረዳት የጀመረው። ምዕራባውያን የፈለገው ነገር ቢደረግ ለኢትዮጵያ አይመለሱም። እውነቱን እያወቁት እኮ ነው ያላወቁ የሚመስሉት። አመራሩ የውጩን ሴራ ተረድቶ ብልህ መሆን አለበት። ኢትዮጵያውያንም ልዩነታችንን አጥብበን ለጋራ ዓላማ አንድ ሆነን መቆም መቻል አለብን።
ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014



