በጦርነቱ የመጨረሻውን ሳቅ የሚስቅ አይኖርም!

0
620

ጦርነት አሸናፊው ተደስቶ የሚስቅበት ስፖርታዊ ውድድርም ሆነ የቀልድ ፉክክር አይደለም። የጦርነት ፍጻሜ ዕፎይታን የሚሰጥ ኹሉን የፈጠረ አምላክ የሚመሰገንበት እንጂ፣ ብዙዎችን ገድለን አሸነፍን ተብሎ የሚሳቅበት የፈንጠዝያ ወቅት ሊሆን እንደማይገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል፣ ጦርነት የተለያየ ሥም እየተሰጠው መካሄድ ከጀመረ አንስቶ “የመጨረሻውን ሳቅ የምንስቀው እኛ ነን” እየተባለ በጥይት መሆኑ ቀርቶ፣ በላባ ሰውነትን የሚኮራኩሩ ይመስል ብዙዎች ቋንቋውን ሲቀባበሉትና ሲያስተጋቡት ተሠምቷል። የሚገስጽ ጠፍቶ አሁንም ድረስ አባባሉ የንግግር ማሠሪያ አንቀጽ ሲሆን ይደመጣል። ጦርነት ባህላዊም ይሁን ዘመናዊ ጨዋታ እንዳልሆነ በተፋላሚ ወገኖች ቢታወቅም፣ ንግግር ለማሳመር ሲባል የመጨፈሪያና የማሳቂያ ቧልት ምክንያት ለማድረግ የሚሯሯጡም መኖራቸው ይነገራል።

ጦርነት ሰው የሚገዳደልበት አስከፊ ተግባር እንደመሆኑ መወገዝ ሲኖርበት ውጤቱን ተመርኩዞ የአንደኛው ወገን የደስታ ምንጭ ሊሆን ባልተገባ ነበር። ከኹለቱም ወገን የሚያልቀው ሰው ብዛት የሚረሳ ይመስል፣ ፈንጠዝያንም ሆነ ሳቅን ማሰብ ሕሊና ላላው ሰው በጣም ከባድ ነው። አሸነፍን ብሎ ከበሮ መደለቅም ይሁን በደስታ አቅልን መሳት የአባቶቻችን ባህሪ አለመሆኑን መረዳት እንዳለብን አዲስ ማለዳ ለማስታወስ ትወዳለች።

በዐድዋው ጦርነት በአንድ ቀን ውጊያ እንደዚያ ዓይነት ዓለም ያደነቀውን ድል ባገኘን ወቅት እንኳን፣ ጭፈራም ሆነ ደስታ እንዳይደረግ የድሉ መሪ የነበሩት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ መወሰናቸውን የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። የዐድዋ ድል እንዲከበር የተደረገው ዓመታትን ቆይቶ የተሰዉ ቤተሰቦች ሐዘን ሲረሳና የቆሰሉትም ተጠግነው ሲያገግሙ መሆኑ ያለምክንያት አይደለም።

በጦርነት ወቅት በተቃራኒ ጎራ የተሰለፉት ወንድማማች ሕዝቦች ሲሆኑ ደግሞ ሐዘኑ እጅግ የከፋ መሆን ይገባዋል እንጅ፣ ፍፃሜው አስደሳች ሊሆን አይገባም። “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ፣ ሐዘንሽ ቅት አጣ ከቤትሽ አልወጣ” እንደሚባለው፣ የአንድ አገር ዜጎች እርስ በርሳቸው ነፍጥ አንስተው ተገዳድለው ሲያበቁ፣ አሸነፍኩ ለሚለውም ጦርነቱ የደስታ ምንጪ ሊሆን አይችልም። የውጭ ወራሪን ድንቅ በሆነ አካሄድ ድል የነሳንበት መንገድና ውጤቱ የደስታም ሆነ የሳቅ፣ አሊያም ፈንጠዝያ ምንጪ እንዳይሆን ከከለከሉት አባቶቻችን ተምረን፣ አሸናፊም ሆንን ተሸናፊዎች፣ ኹነቱን በጸጋ ተቀብለን ቢያንስ ልጆቻችን በሠላም ቂም ሳይቋጥሩ የሚኖሩበትን መንገድ መቀየስ ይኖርብናል።

በማንኛውም ጦርነት አሸናፊ መኖሩ የማይቀር ቢሆንም፣ ከአሸናፊው ወገን ውስጥ ጦርነት በመጠናቀቁ ኹሉም እኩል ደስተኛ አይሆንም። ከጓደኞቹ እኩል ዘምቶ በድል የተመለሰ ቤተሰብ እና ልጁ መስዋዕት የሆነበት ቤተሰብ እንኳን ደስ ያለህ ሊባል አይችልም። የምንስቅበት ወቅት መሆኑ ይቅርና በይፋ ደስታችንን የምንገልጽበት መሆን እንደማይገባው ማመን እንደሚጠበቅብን አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

ከታሪክ ብንማር ይህን ዓይነት ቅሌት ውስጥ የሚያስገባ ድርጊትን መፈጸም ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ጦርነትም ባላመራን ነበር ብለው የሚያስቡ በርካቶች ናቸው። ከአፄ አምደጺዮን የጦርነት ታሪክ መማር ለመሪዎች ብቻ ሳይሆን ለእኛ ለተራው ሕዝብም ጠቃሚ ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ በአንድ ጦርነት ወቅት የተናገሩት ለአሸናፊም ሆነ ለተሸናፊ የሚሆን ነው። በአንድ ጀንበር በተካሄደና በብዙ ሺሕዎች የሚቆጠሩ የጠላት ሠራዊት አባላት ባለቁበት የአንድ ቀን ውጊያ ማጠናቀቂያ ላይ፣ ከመኳንንቶቻቸው ጋር እየተዟዟሩ ራሳቸ ሲዋጉበት የነበረ የጦር ሜዳን ሲጎበኙ የተናገሩት ነው። ንጉሡ ድል አድርገው ያለቀውን ጠላት እያዩ እንደዘመናችን ሰዎች በመደሰት ፈንታ፣ የጠላታቸውን አስከሬን ብዛት እያዩ በሐዘኔታ በከንቱ ያለቁ ፍጥረታት በሚል ስለሰው ልጅ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል። ስለራሳቸው ጦር ጉዳት ሳይሆን ስለጠላታቸው ሠራዊት ጉዳት ጭምር የማዘን አቅም ከነበራቸው አያት ቅመ-አያቶቻችን ብዙ መማር ይጠበቅብናል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከዓመት በላይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት መጨረሻ ላይ ሊስቁ የሚችሉት ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ ጠላቶቿ ናቸው። አሁን እየተላለቅን ባለንበት ወቅት እንዳይስቁ ዓላማቸውን ተረድተን እንዳናቆም፣ አሊያም በእልህ ፊታችንን በጋራ ወደእነሱ እንዳናዞር ስለሚሰጉ ከእኛ በላይ ስለእኛ ያዘኑ ለመምሰል እየሞከሩ ይገኛሉ። የአንድ አገር ዜጎች መተላለቃቸውና አቅማቸውን በሚቀንስ መልኩ መዳከማቸው ራሳቸውን ሊጠቅምም ሆነ ሊያስቅ አይችልም። የጦርነቱ ፍፃሜ በደረሰ ወቅት እኛ የምናዝነው ያኔም በሚያደርጉብን ብቻ ሳይሆን እንዲህ እንድንሆን በመሆናችን ጭምር መሆን ነበረበት።

ምዕራባውያኑም ሆኑ የቅርብ ጎረቤት ሆነው የሚያጫፍሩ በጠላትነት የሚያዩን ሐገራት የመጨረሻውን ሳቅ የሚስቁት ከእኛ ጋር እንዳልሆነ የምንረዳበት ጊዜ መራቅ እንደሌለበት አዲስ ማለዳ አበክራ ትናገራለች። ሶሪያና የመን ጦርነት ውስጥ ገብተው እስካሁን የሚፋለሙበት ሁኔታ ጦርነት መጨረሻ እንደሌለው ማሳያ ነው። እኛን የመሳሰሉ አገራት ከእነዚህ አገራት ዕጣ ፈንታ መማር ተስኖን፣ በእሳት እየተጫወትን እርስ በርስ ለመጠፋፋት ምክንያት ስንፈልግ ቆይተን መመለስ የማይቻልበት ቁልቁለትን እሳትን በመወራወር መንደርደር ይዘናል። የምንወረውረው የእሳት ዕቶን ታች ወርዶ ተጠራቅሞ እየጠበቀን መሆኑን ሳናውቅና ወላፈኑ ሳይሰማን በሽቅድምድም ታች ለመድረስና ለመቃጠል እየተሰዳደብን በመውረድ ላይ እንገኛለን።

ብብታችን ገብቶ እንድንስቅ የሚኮረኩር ጣት በማይኖርበት ሁኔታ አንድነታችንን የሚሸረሽርና አካላችንን የሚሰረስር ጥይት እየተወራወርን ስንጨርስ ለመሳቅ ማሰቡ የጤነኝነት አይሆንም። “ደም ያሰከረው፣ ባሩድ የሸተተው” እንደሚባለው፣ ነፍሳችንን ሽጠን ካልሆነ ሞት እንደጋናውያን ቀባሪዎች የደስታ ምንጫችን እንዲሆን ባህላችን አይፈቅድም። ስለጦርነቱ አስከፊ ገፅታ በማሳየት ፈንታ፣ ስለሆነው ነገር በደስታ የምንናገራቸውም ቃላት ሆኑ በሌላው ቁስል የምንሳለቀው ነገር ለተቀናቃኛችንም ሆነ ጠላት ላልናቸው ልጆች ምንን እንደሚያተርፍ አስቀድመን ማሰብ ይጠበቅብናል።

ድል የእግዚአብሄር ነው በሚባልበት አገር፣ የእሱ ፍጥረቶች ነን ብለን የምናስብ ሰዎች፣ እሱ እኛን ለይቶ ማጥፋት ሳያቅተው እርስ በርሳችን ስንጠፋፋ ደስ የሚለው ይመስል ጦርነትን የደስታ ምንጭ ለማድረግ ማሰብ እጅግ የሚሳዝንና ሰብዕናችን ምን ያህል እንደወረደ የሚያሳይ ኹነት ነው።

“በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እየተባለ በያዝነው ሰሞን የሚካሄድ ስፖርታዊ ግጥሚያ ምንም ዓይነት መቆራቆስ ቢኖረው እንኳን ማንም የተወዳዳሪ አካል ወይም ደጋፊ ቂም ቋጥሮ እንዳይሄድ ይደረጋል። መካሰስም ሆነ አንዱ ባንዱ ላይ መሳለቅ እንዳይችል አድርገው በጨዋታ እንኳን ተከባብረን እንድንሸናነፍ ያደረጉን አባቶቻችን አሁን እንዲያፍሩብንና እንዲሸማቀቁብን ማድረግ አይገባንም።

የጠላትም ይሁን የአራዊት፣ ለአስከሬን ክብር ይሰጥባት በነበረች አገር፣ የክቡር ሰው ልጅ አስከሬን የጠላት ነው ተብሎ በአደባባይ ሲንገላታ፣ ቅስቀሳም ሲደረግበት አስተውለናል። እያንዳንዱ ሟች ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ እንዳለው የዘነጋን ቢሆን እንኳን ግፍን ለራሳችን ስንል ልንጠየፋት በተገባን ነበር። አሸናፊነት ጊዜያዊ ድልን ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ዕርቅን የሚያመጣ ካልሆነ ከጠቃሚነቱ ይልቅ ቁርሾ እየፈጠረ የሚጎዳበት መንገድ ሊበልጥ እንደሚችል መገንዘብ ያሻል።

“ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንደሚባለው፣ ሰብዕናችንን ሳናውቀው እንዳናረክሰው መጠንቀቅ ግድ ይለናል። እንቁራሪትን ይዘው የፈላ ውሃ ውስጥ ቢከቷት፣ ተስፈንጥራ በመዝለል ራሷን ከሞት ታድናለች። እሳት ላይ የተጣደ ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ ቢጨምሯት ግን ለብ እያለ ሲሄድ ስለሚያስደስታት አትወጣም። ከአካባቢያዋ ቅዝቃዜ የተሻለ እየመሰላት ስትቆይ ግን በደስታዋ ብዛት ሳይታወቃት ድንገት መንቀሳቀስ ያቅታታል። በኋላ ዘግይታ መውጣት ብትፈልግም ስለማትችል ውኃው ሲፈላ ነፍራ ትቀራለች። የአካባቢዋ ጊዜያዊ ሞቅታ እንደማይቆይ ስላልተረዳች ውኃው እያሳሳቀ ወደ ሞት ይዟት ይሄዳል።

እኛም ሰዎች ሊገለን የመጣን ማስቆም ካቃተን መግደላችን ተፈጥሯዊና ሕጋዊ ነው ቢባልም፣ በመግደላችን መጸጸት እንጂ መደሰት ነፍሳችንን አስይዘን ላደረግነው ቁማር መዳኛ አይሆንም። ለጠፋው ነፍስ፣ ለተጎዳው ሕዝብና ለወደመው ንብረት ከመነሻው ጀምሮ ማዘን እንጂ፣ ድል ነሳን ብለን መደሰት ከጦርነቱ አለመማር ነው። ይህ በመሆኑም ኹላችንም ያለንበትን ወጀብ ተረድተን ውኃው እንዳወስደን፣ እሳቱም እንዳያቃጥለን ወደነፈሰበት ከመንፈስ እንድንቆጠብ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here