ምዕራባውያን ኢትዮጵያን የመሳሰሉ በማደግ ላይ ያሉ አገራትንም ሆነ ተቀናቃኝ የሆኗቸውን የምሥራቅ አገሮች ሠላዮችን በመላክ አዳክሞ ለመበዝበዝና በዘመናዊ ቅኝግዛት ሥር ለማማቀቅ እንደሚሠሩ ይነገራል። በግብረ-ሠናይና በዓለም አቀፍ ተቋማት ሽፋን እየገቡ ከሙያው ጋር የማይገናኙ ብቃት የሌላቸውን የአገራቸውን ሥራ አጦች፣ እንዲሁም ጥቂት ብቁ የየአገራቱን ዜጎች በመቅጠር እንደሚያሠልሉ ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) በጽሑፋቸው ያስነብባሉ። ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለአገራቸው ሲሉ ሠላዮችም መሆን አለባቸው የሚሉት እኚህ የበርካታ መጻሕፍት ደራሲ፣ እንደምሁርነታቸው በዜጎችም ሆነ በመንግሥት ከምዕራባውያን የተቃጣውን ሴራ ለመመከት መደረግ ያለበትን እንዲህ ያብራራሉ።
ሪፖርተር ጋዜጣ በኅዳር 12 ቀን 2014 ዕትሙ በቆይታ ዐምዱ፣ ‹‹ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጫፍ ላይ አድርሰናታል ቢሉም ይህ ግን በፍጹም የሚሳካ አይደለም›› በሚል ርዕስ ዮናስ አማረ ከ ፍሰሐ አስፋዉ (ዶ/ር) ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረገውን ቃለ-ምልልስ አስነብቦናል።
በዚህ ቃለ-ምልልስ ዶ/ር ፍሰሐ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ሙያዊ፣ በሥራና በዕድሜ ቆይታ ያከማቹትን ትምህርት፣ ዕውቀት እና ጥበባዊ ቁም ነገር አጋርተውናል። ከዚህ በኋላ በኹሉም ረገድ፣ ዕድሜን ጨምሮ አንቱታ የሚገባቸው ቢሆንም ለጽሑፉ ፍሰት እና ለመልዕክቱ ተገባቦታዊ ቅለት ስል በአንተ/በእሱ አገላለጽ የቃለ ምልልስ ተጠቃሾቻቸውን አቅርቤአለሁ።
ዶ/ር ፍሰሐ በቃለ-ምልልሱ ውስጥ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር በማዛመድ የውጭ ኃይሎች በተለይም ምዕራባውያን በአገራችን ላይ በከፈቱብን ኹለንተናዊ የማፈራረስ ዘመቻ፣ ቁሳዊና ሥነ ልቦናዊ ጦርነት ውስጥ የሠላዮችን ሚና አስገንዝቦናል። በዚህ ረገድ የሚከተለውንም ብሏል።
‹‹…ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ነጮችን ወይም ከነጮች ጋር ከሚውሉ ዜጎች ሰብስበህ 100 ብታሰልፍ ከውስጣቸው 10 እና 15 ሠላይ ወይም የሲአይኤ ወኪል አታጣም ››
ሲአይኤ በተለምዶ አሜሪካ ብለን የምንጠራው አገር የሥለላ ድርጅት መጠሪያ ነው። ከመቶ እስከ አስራ አምስቱ ያህል ተባለ እንጂ፣ በኔ ምልከታና ግምግማ ከዚያም በላይ ይሆናሉ። አንባቢያን ልብ አንዲሉ የምሻው ኢትዮጵያን የሚሠልሏት ነጮቹ ብቻ እንዳልሆኑ ነው። ኢትዮጵያዊ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆነው ለሌሎች አገሮች በአብዛኛው ደግሞ ለአደጉ ምዕራባውያን አገራት አገራቸውን የሚሰልሉ፣ ብሎም በባንዳነት የሚያስጠቁና የሚያስወጉ በርካቶች እንደሆኑ ከዶ/ር ፍሰሐ ምላሽ መረዳት ይቻላል። እዚህ ላይ ማሳሰብ የምሻው ሠላይነት መጥፎ ነው ከሚል አጠቃላይ ድምዳሜ መነሳት እንደሌለብን ነው። ይህን ጉዳይ ከተወሰኑ አንቀፆች በኋላ ተመልሼ አጭር ማብራሪያ ሰጥቼበታለሁ።
ልክ እንደ ዶ/ር ፍሰሐ እኔም የአሜሪካን አገር ተማሪ ነበርኩና የማስትሬትና የዶክትሬት ዲግሪዎቼን ያገኘሁት ከዚያ አገር ዩኒቨርስቲዎች ነዉ። በሥለላ ሥራዎቻቸው ጉዳይ እዚያ በነበርኩበት ጊዜ ያስተዋልኩትና የተረዳሁት ነገር አለ። ይኸውም አሜሪካኖች እንኳን በውጭ አገር፣ በአገራቸውም ውስጥ 100ዎቹ ቢሰለፉ ከ20 እሰከ 30 ያህሉ በተለያዩ የሥለላ ድርጅቶች ውስጥ ተመልምለው የሚሠሩ ሠላዮች ሁነው ይገኛሉ ብዬ እገምታለሁ። የሥለላ ድርጅቶች የምላቸው የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት፣ ሲአይኤ፣ ኤፍቢአይ የመሳሰሉትን ተቋማት ያካትታል። እነዚህ በአሜሪካ ሆነ በሌሎች አገራት ውስጥ አሜሪካኖችንም ጭምር የሚሠልሉና የሚከታተሉ ናቸው። ጥያቄው ለምን ይሆናል?
መልሱ አሜሪካ ውስጥ ያለው መንግሥት ሁሌም የአሜሪካ በዝባዥ ካፒታሊስቶችና ኢምፔሪያሊስቶች ስብስብ ስለሆነና የነዚህን ስብስብ ጥቅም ያለ ጠንካራ የጦር ኃይልና የሥለላ አደረጃጃት በአሜሪካ ውስጥም ሆነ ከአሜሪካ ውጪ ለማስጠበቅ ስለማይችሉ ነው።
እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን የዶ/ር ፍሰሐ ማብራሪያ ሲአይኤን ስለአመላከተ እንጂ በምዕራቡም ሆነ በምሥራቁ ዓለም፣ እንዲሁም በመካካለኛው እስያና በአፍሪካም በርካታ አገራት ሠላዮችን አደራጅተው እንደሚጠቀሙባቸው ይታወቃል። ቁም ነገሩ ለምን ጉዳይ ይጠቀሙባቸዋል የሚለው ነው።
የውጭ ኃይሎች፣ በተለይም የምዕራቡ ኢምፔሪያሊስት አገራት፣ ለጥቅሞቻቸው ሲሉ የመከላከያና የሥለላ ድርጅቶችን በቀጥታ አደራጅተው ከመጠቀም በተጨማሪ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን (መ.ያ.ድ) በተለምዶ ኤን.ጂ.ኦ. የሚባሉትን በማቋቋም ለሥለላ ሥራ ይጠቀሙባቸዋል። ኤንጂኦዎች፣ በተለይ ምሁር የሚባሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ሙያቸውን ተገን አድርገው የሥለላ ሥራ እንዲሠሩ ያደርጋሉ። ከመ.ያ.ድ በተጨማሪ የኹለትዮሽ የልማት ተራድኦ ድርጅቶችን ለምሳሌ እንደ አሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤድ)፣ እና ዓለም አቀፍ ብዝኀ ድርጅቶች ለምሳሌ እንደነ ዓለም ባንክ፣ የዓለም ገንዘብ ተቋም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ውስጥ ሠላዮቻቸውን በመሰግሰግ በርካታ አፍራሽና እኩይ ተግባራትን ይከውናሉ። ለምን ይሄን ያደርጋሉ የሚለው ጥያቄ ቢነሳ ተገቢ ነው። መልሱ ቀላል ባይሆንም ከወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ ጋር በማያያዝ ዶ/ር ፍሰሐ ምላሽ ሰጥቶበታል።
ምላሹ በከፊል የአካባቢ ተጽዕኖ (ጂኦ ፖለቲካ) ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በተቀረው ዓለም ለጥቁሮች የነፃነት ተምሳሌት ሆና ለውጭ ኃይሎች የተፈጥሮ ሀብት ሆነ ገበያ መር ለሆነ ብዝበዛቸው እንቅፋት ስለሆነች መፈራረስ አለባት ብለውም ስለሚያምኑ ነው። ኢትዮጵያ ታሪካዊና የተፈጥሮ የሆኑ ሀብቶቿን ሆነ ሌሎችን ለመጠበቅና አገራዊ የሆነ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ፕሮግራም እና ኢንስትቲዮሽን (ፖስፕኢ) አደራጅታ ለመጠቀም የምታደርገው ጥረትና እያስመዘገበች ያለው አውንታዊ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ውጤት፣ በሌሎች ታዳጊ አገራት ውስጥ፣ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ ለሚያቅዱትና ለሚተገብሩት የተፈጥሮ ሆነ፣ በገበያ ላይ የተመሠረተ ሀብት ምዝበራ ተግዳሮት ይሆናል ብለው ስለሚያምኑም ነው። ስለዚህ ይህን ለመቋቋም ብሎም ለመቀልበስና ለዘለቄታውም ኢትዮጵያን የማፈራረስና የማጥፋት ፍላጎታቸውን ለማሳካት ከሌሎች መሣሪያዎች ጋር በማጣመር የሥለላ ሥራን በፕሮጀክት ደረጃ ቀርጸው ይጠቀሙበታል።
ከላይ የቀረበውን ማብራሪያ በሌላ ገፅታው ኢትዮጵያውያን መረዳት ያለብን፣ በዝባዥ የምዕራቡ ዓለም የአደጉ አገራት ዕርዳታ፣ ድጎማ፣ ብድር እና የተለያዩ ድጋፎችን አስታከው ወደ አገራችን ውስጥ በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድና አደረጃጀት የሚመጡት፣ እነርሱ እንደሚሉት ዲሞክራሲ ለማስፈን፣ ሶሻሊዝምንና ኮሚኒዝምን ለመዋጋት፣ ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለፍትኅዊነት ወይም ከድህነት ሊያላቅቁን ፈልገው ሳይሆን፣ ቢቻል አገር መስለን በምስለኔዎች እንዲበዘብዙን፣ ካልተቻለም በብሔር/በጎሳ የተከፋፈሉ አካባቢዎችን በመፍጠር አፈራርሰው በጉልበትና በጭቆና ቀንበር ሊገዙን፣ ጉልበታችንን እና የተፈጥሮ ሀብታችንን ሊበዘብዙ ነው።
ዲሞክራሲን ማስፈን፣ ሶሻሊዝምንና ኮሚኒዝምን መዋጋት፣ የሰበዓዊ መብት መከበር፣ ፍትኀዊነት ወይም ከድህነት መላቀቅ የመሳሰሉት ቃላት፣ ሀረጋትና ትርክቶች የማወናበጃ ቋንቋቸው ማዳበሪያዎች ናቸው። ዲሞክራሲ በአሜሪካ ውስጥ የጥቂት ካፒታሊስቶች ሥልጣንን የመቆጣጠሪያ እና ከሥልጣን ጋር የተቆራኘ የመበዝበዣ መሣሪያ እንደሆነ ታዋቂው አሜሪካዊው ኢኮኖሚስት ጆሴፍ ስትግሊዝ ‹‹The Price of Inequality: How Today’s Divided Society Endangers Our Future>>፣ በቀላል አተረጉአጎም ‹‹እኩል ያለመሆን ዋጋው፡- እንዴት የዛሬው የተከፋፈለ ማኅበረስብ ወደፊቱን አስፈሪ እንደአደረገው›› በሚል እ.አ.አ በ2013 በፃፈው መጽሐፉ፣ በተለይ በምዕራፍ አምስት ውስጥ፣ አብራርቶ አቅርቦታል።
እዚህ ላይ አንባቢያንን ማሳወቅ የምሻው በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 በጻፍኩት መጽሐፌ ውስጥ የኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገትና ማኅበራዊ ልማት፣ በተለይም አገራችን በመንገድ ሥራና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ በማዕድንና በቱሪዝም መዳረሻ ሀብቶች ልማት ላይ የምታደርገው አውንታዊ ለውጥ የውጭ ኃይሎችን፣ በተለይም የአደጉ አገራት፣ ኢምፔሪያሊስቶችና ድንበር ዘለል ኩባንያዎች፣ ጦር ሰብቀው እንዲነሱብን እንደሚያደርጋቸው ጠቁሜአለሁ። አንድም የነዚህ የሀብት ተጠቃሚዎች በተቀዳሚነትና በአብዛኛው እነርሱ መሆን እንዳለባቸው ስለሚያምኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ በመንገድና በኤሌትሪክ እንዲሁም በቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፍ እያደረግናቸው ያሉ ለውጦች፣ ኢትዮጵያውያን በብሔርና ጎሳ ከመናቆርና በድንበር ክለላ ከመጋጨት ወጥተው በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ብልጽግና ጎዳና ላይ እንዲተሙ ስለሚያደርጋቸው፤ በአጠቃላይ ከላይ ያመለከትኳቸው የአንድነትና መተሰሳሰር ምክንያት የሚሆኑ መሠረተ ልማት ሥራዎች፣ በእንጭጩ እንዲቀጩ ወይም እንዲወድሙ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የማፍረስ ሴራ ጎንጉነው እንደሚመጡብን ጽፌ ነበር። ዛሬ ላይ እየሆነ ያለው ያ አስቀድሜ ለማስገንዘብ የሞከርኩት ነገር ወደ ትግበራ ገብቶ ነው።
ዶ/ር ፍሰሐ በቃለ-ምልልሱ ወቅት በሰላዮች ላይ ከሰጠው አስተያየት በተጨማሪ ስለ ውጭ ዕርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞች የሰጠው ምላሽም ትኩረት ይገባዋል። ከዚህ ጉዳይ ጋር አያይዞ በቃለ ምልልሱ ውስጥ የሚከተለውን ተናግሯል።
‹‹ … የውጭ ዕርዳታ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሰዎችን ብትጠይቅ በአገራቸው ሥራ ያጡ ናቸው። ደሞዝ ተቆርጦላቸው ነው ከእነ ቤተሰቦቻቸው እዚህ የሚመጡት ››
ይህ አባበሉን እኔ ከአለኝ ከአርባ ዓመት በላይ በሚሆነው የሥራ ልምዴና ተሞክሮዬ ስመዝነው ትክክለኛ ምልከታ ነው እላለሁ።
አንዳንድ ጊዜ በተለያዩ መድረኮች ውይይት ሳደርግ፣ ከአለኝ የረዥም ጊዜ ጥናታዊ ግንዛቤና ተሞክሮ ላይ ተነስቼ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ውስጥ ከሚሠሩት አብዛኞቹ ነጮች በአገራቸው በትምህርትና ዕውቀት ደረጃቸው ወይም በትግበራ ችሎታቸውና ውጤታማነታቸው ዝቅተኛ የሆነ፣ በድርጅቱ ውስጥም ዘጠና በመቶ ያህሉ በአገራቸው ሥራ አጥ የሚሆኑ ወይም ተቀጥረው ውጤት አልባ የነበሩ የካፒታሊስቶቹ ልጆች ወይም ዘመዶች ስብስቦች እንደሆኑ እገልጻለሁ። በሌላ አገላለጽ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቆሞ ያለው በውስጡ ባሉ 10 ከመቶ በማይበልጡ ትጉህና ጠንካራ ሠራተኖቹ ነው የሚል፣ ግን በተጨማሪ ጥልቅ ጥናት ሊረጋገጥ የሚገባው ትምህርታዊ መላምት /ኃይፖተሲስ/ አቀርባለሁ። እነዚሁ 10 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በአብዛኛው ከታዳጊ አገራት ተመልምለው የተቀጠሩ፣ ድኅነታቸውን አሸንፈው፣ በዙሪያቸው ያሉ በርካታ ደኃ ወገኖቻቸውን ለመርዳት የሚጥሩ የታዳጊ አገር ዜጎች ናቸው ብዬ እሞግታለሁ። በቅርበት ዐይተንና አስተውለን ለመታዘብ ለቻልን ሰዎች የሚያሳዝነው ጉዳይ ደግሞ እነዚህ የታዳጊ አገራት ጉምቱ፣ በዕውቀትና ጥበባዊ ክህሎታቸውም የላቁ ዜጎች ጀማሪና በዕወቀት አናሳ ሆነው ልምድም በሌላቸው የአደጉ አገራት ሰዎች እየተጎነተሉና እየተመናጨቁ መሥራታቸው ነው።
ወደ ሠላዮች ጉዳይ ልመለስ። የዶ/ር ፍሰሐን መልዕክት ለመመርመር ስሞክር፣ ዶ/ር ፍሰሐ ሠላይነት መጥፎ ነው ከሚል መንደርደሪያ ሐሳብ ላይ እንዳልተነሳ የተረዳሁት ይመስለኛል። ኢትዮጵያዊ ለውጭ ኃይሎች በዶላር ተገዝቶ፣ የነዚህን ኃይሎች ጥቅምና የምዝበራ ፍላጎት ለማርካትና ለማሟላት፣ በሒደትም በአሁኑ ጊዜ እንደሚያደርጉት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚደረግን እኩይ ሥራን የሚያግዝ አጥፊ ሠላይ አይሁን የሚል መልዕክት ያስተላለፈ ይመስለኛል። በተጨማሪም ለኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኃይማኖታዊ ባንዳነት ተዳርጎ ለአገራችን አፍራሽ ኃይሎች አስፈፃሚ መሣሪያ አይሁን የሚል መልዕክት ያለው ቃለ-ምልልስ ሆኖ ነው ያገኘሁት።
እንደውም፣ መልዕክቱ ለአገራችን ሉዓላዊነት መረጋገጥ፣ ጠላቶቿን ፈልፍሎ ለማውጣትና ለመደምሰስ ይቻል ዘንድ፣ ተገቢውን ዕርምጃ በተገቢው ቦታና ጊዜ ለመወሰድ፣ ኹሉም ኢትዮጵያዊ አፍራሾቿንና ጠላቶቿን የሚሠልል መሆን አለበት የሚል ምክር ያዘለ ቃለ-ምልልስ አርጌ አንብቤዋለሁ። ትክክልም ነው። ምክንያቱም የሥለላ ሥራ በአሁኑ ወቅት በጣም ውድ የሆነን፣ የአገር ደኅንነትን ማስጠበቂያ፣ ሰላምን ማስፈኛ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ማቀዳጃና መተግበሪያ፣ የፖለቲካ ሥርዓትን ማረጋጊያ የሆነን ወሳኝ ግብዓትን ያስገኛልና ነው። ይህ ግብዓትም ‹‹ትክክለኛ መረጃ›› ነው።
በአገራችን ታሪክ በእንደዚህ ዓይነቱ የሥላለ ተግባር ተሠማርተው፣ በጠላት ካምፕ ውስጥ ሰርስረው ገብተው አገራቸውንና ሕዝባቸውን ከዕልቂትና ከጥፋት የታገዱ በርካታ ጀግና ሠላይ አርበኞች እንደነበሩን ከታሪክ መጻሕፍት እንረዳለን። ዛሬም ኹሉም ኢትዮጵያዊ የትክክለኛና አገርን ከጠላቶቹ የሚታደጋት መረጃ ሰብሳቢ ሠላይ ቢሆን እመኛለሁ። አባቴ ወታደር ከመሆኑ በፊት በጣሊያን ወረራ ጊዜ ገና በ12 እና 13 ዓመት ዕድሜው በመረጃ ሰብሰቢነት ስለ ሠራ ዛሬ በአዲስ አበባ በሥላሤ ቤተ ክርስቲያን የአርበኞች መቀበሪያ ሥፍራ ሐውልቱ ቆሟል። ስለሠራቸው ሥራዎች የነገረኝ ለአገሬ ምንግዜም ተፈጥሮዓዊ ሠላይ እንድሆንና ለሠላሟና ሉዓላዊነቷ ቀናኢ እንድሆን አድርጎኛል። ኢትዮጵያውያን በዕርዳታ ድርጅቶችም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩት ኹሉ ዛሬም ለአገራቸው በመሠለል ሥራ ላይ ቢሠማሩ፣ ጦር ሜዳ ዘምተው አገርን ለድል ከሚያበቋት የመከላከያና የፀጥታ ኃይሎች ተርታ በጀግንነት መስመር ላይ ያሰልፋቸዋል።
ኢትዮጵያውያን በውጭ ኃይሎች ላይ፣ በተለይም ከምዕራቡ ኢምፔሪያሊስት አገሮች፣ እነ አሜሪካና እንግሊዝ ከመሳሰሉት በሚመጡ ሠላዮች መረጃ አቀባይነት፣ የአገራችንን የተፈጥሮ ሆነ ታሪካዊ ሀብት መዝብረው፣ እኛን በድህነት አረንቌ ውስጥ ዘፍቀው ለመግዛት በሚሹ አገራት ለምሳሌ ግብጽ፣ እንዲሁም ድንበር ዘለል በዝባዥ ኩባንያዎች ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ እኩይ ሥራዎቻቸውን መግታት አለብን። ከዚህ አንፃር በተለይ በዕርዳታና ዓለም-አቀፍ የድጋፍና መተባበር ድርጅት ስም ለዚህ እኩይ ተግባራቸው በአገራችን ውስጥ በሰገሰጓቸው ሠራተኞችና ተላላኪዎቻቸው ላይ የዐይነ ቁራኛ ክትትልና ሥለላ ልናደርግባቸው እንደሚገባ ለማሳወቅ ጥረት ማድረግ ከጀመርኩ ቢያንስ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ሆኖኛል።
ቀድሞ ቅኝ ገዢ የነበሩ እና በአዲስ ይዘት ቅኝ ለመግዛት የተነሳሱ ለምሳሌ እንደ አሜሪካ ዓይነቶች የምዕራባዊ አገራት፣ ታዳጊ አገራትን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ በርቀት/ህቡዕ የቅኝ አገዛዝ (colonialsm-in-absentia) ሥርዓት አማካይነት በግሎባላይዤሽን እና ነፃ ኢኮኖሚ ግንባታ ዲስኩር የሚፈልጉትን የተፈጥሮ፣ ታሪካዊ እና የገበያ ሀብት /ለግብዓትም ሆነ ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶችና አገለግሎቶችን አካቶ/ ለማጋበስ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ከኻያ ስድስት ዓመት በፊት በሠነዶች ዳሰሳ ላይ በተመሠረተ መረጃ ጥናታዊ ጽሑፍ ጽፌ በተለያዩ የሙያና ሕዝባዊ መድረኮች ላይ አቅርቤአለሁ።
በጀርመኑ ኦቶ-ቮን ቢስማርክ መሪነት በ1885 ከተቀየሰው ቅኝ አገዛዝ፣ በኋላም በነ ንኩሩማ እና ካስትሮ ከተገለፀው አዲሱ ቅኝ አገዛዝ (Neo-colonialism) የርቀት/ህቡዕ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት የተለያዩ ባህርያት እንዳሉት በተለያዩ ጽሑፎችና መጻሕፍት ውስጥም አብራርቻለሁ። ስለዚሁ ሥርዓት ወቅታዊ ይዘት በ2012 ዓ.ም በጻፍኩት ‹‹ኢኮኖሚው፣ ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ›› በተሰኘው መጽሐፌ ውስጥ በሠፊው ማብራሪያ ስለሠጠሁ አንባብያን መጽሐፉን መመልከት ይችላሉ።
በአጭሩ ለመግለፅ፣ የርቀት/ህቡዕ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ቀድሞ ቅኝ ያልተገዙ /ለምሳሌ ኢትዮጵያ/ አገራትና ቀድሞ ቅኝ ገዢ ያልነበሩ /ለምሳሌ አሜሪካ/ አገራትን አካቶ ትኩረቱ የታዳጊ አገራትን የኢኮኖሚ ነፃነትን ገፎ ፖለቲካዊና አገራዊ አስተዳደር ሥርዓታቸውን በዲሞክራሲ ስም ሸርሽሮ የኢኮኖሚ ጥቅሙን ለማስከበር የሚያስችሉትን የታደጊ አገር ዜጎችን ሥልጣን ላይ ማስቀመጥና የሀብት ብዝበዛ ማካሄድ ነው። ቅኝ ገዢዎቹም ባሉበት አገር ሆነው በርቀት ለዚህ የሚያስችል የፖለቲከ አደረጃጀት ይቀይሳሉ፤ የፖስፕኢ ቀረፃና የማስፈጸሚያ ተቋማትንም ያደራጃሉ። ይህ ማለት በርቀት/ህቡዕ ቅኝ ግዢ ሥርዓት፣ ቀደም ሲል ቅኝ ተገዝተው የነበሩም ሆነ በዚህ አዲስ ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ የሚፈለጉ ቅኝ ተገዝተው የማያውቁ ታዳጊ አገራት በፖለቲካ ራሳቸውን ነፃ አውጥተዋል ወይም ናቸው ቢባሉም፣ ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ጉዳዩች ላይ ግን የሚወስኑት በርቀት ወይም በህቡዕ ቅኝ ገዢዎች ባስቀመጧቸው ሰዎቻቸው ወይም ተቋሞች ይሁንታን ካገኙ ነው የሚል ዕሳቤን የያዘ ነው። በርቀት/ህቡዕ ቅኝ ለመግዛት የፈለገው አገር ለዚህ ፍላጎቱ ያስቀመጣቸው የአገሬው የፖለቲካ ሥልጣን ተቆናጣጮች ከፍላጎቱ ከአፈነገጡበት እነእርሱን ለማስወገድ ቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ያልሆነ የመንግሥት መለወጥ ወይም ግልበጣ ዕርምጃ ይወስዳል። ለዚህ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ሽፍታ፣ ተገንጣይ፣አሸባሪ ወይም በብሔርና ጎሳ የተደራጁና የጦር መሣሪያ የሚያስታጥቃቸውን ቡድኖች ይፈጥራል፤ ያደራጃል፤ ብሎም ግጭቶችና ጦርነቶችን በፋይናንስ፣ በቁስና በቴክኒካዊ አገልግሎት ድጋፍ ይሰጣቸዋል። አስፈለጊም ከሆነ ቅጥረኛ የውጪ አገር ወታደሮችን ለጦርነት አብሮ ያሠማራል። አንባቢያን በዚህ ጉዳይ ላይ ከላይ ከጠቀስኩት መጽሐፌ በተጨማሪ በ2013ዓ.ም ‹‹ኮርፖራቶክራሲ፣ አገራዊ የሚተገበር (ፕራግማቲክ) ብልጽግና ተኮር ፖስፕኢ›› በሚል ርዕስ ያሳተምኩትን መጽሐፍ ቢያነቡ ተጨማሪ ዝርዝር ማብራሪያዎችን ሊያገኙ ይችላሉ።
በ2012ዓ.ም በጻፍኩት መጽሐፍ በምዕራፍ አምስት ‹‹ዕድገት፣ ልማት፣የምዕራቡ ካፒታሊዝም እና ሦስቱ ፖለቲከኞች›› በሚል ርዕስ የምዕራቡ ኢምፔሪያሊስት አገሮች ከራሳቸውም ሆነ ከሌሎች አገራት በሚመለምሏቸው ሠላዮችና ጉዳይ አስፈፃሚዎች፣ በተለይም ተምረዋል በሚባሉ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ባንዳዎች አመቻችነት ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሴራቸው ተግባራዊነት እየተጠናከረ እንደመጣ፣ ይህንም ኢትዮጵያውያን ትኩረት ሰጥተን መከታተልና እኩይ ሥራዎቻቸውን ማክሰም እንደሚገባን አሳውቄአለሁ። በዚሁ ምዕራፍ በተለይ በንዑስ ክፍል 5.2.5 ‹‹ካፒታሊስቶች፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ሲአይኤ›› በሚል ርዕስ አሜሪካኖች የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በሲአይኤ መረብ ውስጥ በነፖል ሔንዝ አማካይነት አጥምደው ኢትዮጵያን በቁጥጥራቸው ሥር እንዳዋሏት አሳውቄአለሁ። በምዕራፍ 14 በንዑስ ክፍል 14.3.3 ‹‹የውጭ ኃይሎች የ 11ኛው ሰዓት ኢትዮጵያን የማፈራረስ አሻጥር›› በሚል ርዕስ በጻፍኩት ማብራሪያ ውስጥ፣ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሴራ በቢሊዮን ዶላር በሚቀረፅ ፕሮጀክት የተደገፈ ሊሆን እንደሚችልም አስገንዝቤአለሁ። በተለይ ምሁራን የሚባሉትን፣ በውጭ ቋንቋ በመናገር ችሎታቸውና በግርግዳ ላይ በኮምፒውተር ስዕላዊና የጽሑፍ /በተለምዶ ፓወር ፖይንት ፕረዘንቴሼን የሚባለው/ አቀራረብ ባለሥልጣናትን በሚያማልሉ ዜጎች በኩል የረቀቀ የአገርን ልማታዊ እንቅስቃሴ የሚያጓትት አሻጥር ይሠራሉ።
በኢኮኖሚው በኩል በሊብራላይዤሽንና በፕራይቪታይዤሽን ስም የሚየደናግሩ አማካሪ ተብዬ፣ ግን የኢኮኖሚ ባንዳዎች እንዲሁም በማህበራዊ ዘርፉ የተማሩ ባንዳዎችን በኤንጂኦዎችና በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በመሰግስግና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች፣ በነዓለም ባንክና በኹለትዮሽ ተራድዖ ድርጅቶቻቸው በኩል ወፈር ያለ ደመወዝ በዶላር ዕሳቤ እንዲከፈላቸው በማድረግ፣ የኢትዩጵያን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ፖስፕኢ አደረጃጀትና ትግበራ ለውጭ ኃይሎች በዝባዥነት እንደሚያመቻቹ በ2013 ዓ.ም ‹‹ኮርፖራቶክራሲ..›› በሚል ርዕስ ባሳተምኩት መጽሐፍ በምዕራፍ 6 ንዑስ ክፍል 6.7 በዝርዝር አብራርቼ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሞክሬአለሁ።
አንባቢያን ልብ እንዲሉ የምሻው፣ ይህ ሁሉ የማንቂያና የማስገንዘቢያ ጽሑፌ የቀረበው ዛሬ የገባንበት የጦርነት ቅርቃር ውስጥ ሳንገባ ነበር። እንደገመትኩትና እንደተረዳሁትም ዛሬ ላይ ፕሮጀክቱ ወደ ትግበራ ገብቷል። በአገር ውስጥ ሆነ በውጭ አገር ያለን ኢትዮጵያውያን በምንችለው ኹሉ ተሳትፈን የቢሊዮን ዶላር እኩይ ፕሮጅክቶቻቸውን በኹሉም ዓውድ ውስጥ እንዳይተገበሩና በአጭር ጊዜ ውስጥም እንዲመክኑ ማድረግ አለብን። ለዚህ መሰል መሰሪ ሥራዎች አፈፃጸም የተመለመሉትን ሁሉ / ባንዳዎችንና ሠላዮቻቸውን ጨምረን/ በተለይም በውጭ ዕርዳታ ድርጅቶች ውስጥ ተሰግስገው ያሉ ሠላይ ነጮችንና ከነእርሱ ጋር ተጎዳኝተው የሚሠሩትን ዜጎች በመከታተል ማጋለጥ፣ ተገቢ የሆነ ሕጋዊ ዕርምጃም እንዲውሰድባቸው ማድረግ አለብን።
በመጨረሻ ደግሜ ማንሳት የምሻው ለበርካታ ዓመታት የተመለከትኳቸውንና የታዘብኳቸውን የውጭ ኃይሎች የኢትዮጵያን አገራዊ ዕድገትና ልማት ፖስፕኢ የማደናቀፍ ወይም አፈፃፀም ችግር እንዲገጥማቸው የማድረግ እንቅስቃሴያቸውን አመላክቼ በጽሑፍ ከሰባት ዓመት በፊት የሰጠሁትን ማስገንዘቢያ ነው።
የውጭ ኃይሎች በቅርቡ በተጀመረብን የለየለት የጦርነት ሴራ ገብተው መተግበር ከመጀመራቸው በፊት በአገራዊ ፖስፕኢ ቀረፃና ትግበራ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተመዘገበ ያለው የተፋጠነ የኢኮኖሚ ዕድገትና ኹለንተናዊ ልማት አካሄድ ስላልጣማቸው የኢኮኖሚ አሻጥር ሥራ ላይ እንደተጠመዱ፣ እነዚህም በሦስት የአሻጥረኞች ጎራ እንደሚከፈሉ አመላክቼአለሁ።
አንደኛ፣ በአገር ውስጥ ያሉ በተለይም በፖለቲካ ቡድኖች ውስጥ የተሰገሰጉ አሻጥረኞችና በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሰገሰጓቸው የኢኮኖሚ ባንዳዎች፣ ኹለተኛ፣ ከውጭ የሌሎች አፍረካ አገራት መሪዎችና የዕኩይ ተልዕኮ አንጋቢ አማካሪዎች፣ ሶስተኛ፣ ድንበር ዘለል ኩባንያዎችና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ናቸው። ይህን እንደ አውሮፓዉያን አቆጣጠር በ2015 በእንግሊዘኛ ባሳተምኩት ‹‹Ethiopias Indigeneous Policy and Growth›› በሚል ርዕስ በምዕራፍ 22 ውስጥ በዝርዝር ስለአብራራሁት መጽሐፉን እንዲያነቡት እጋብዛለሁ።
በአጠቃላይ ዶ/ር ፍሰሐ እንዳለው በርካታ ሠላዩች፣ ሲአይኤዎችና የሌሎች አገራት የስለላ ድርጅቶች ሠራተኞች፣ በድህነታችን ስም ከሥራአጥነት ወደ ሠራተኛነት አገራችን ውስጥ ገብተው እህልና ዘይት በማደል በከፍተኛ ደሞዝ ተከፋይነት የሥራ ከለላ፣ በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑና የተራድኦ ድርጅቶች ውስጥ መሽገው የምዕራቡ ዓለም ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ነው። በዚህ ተልዕኮ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን ነጮች እና በሠላይነትና በባንዳነት የተገዙ ዜጎችን ዕኩይ ተግባር ማክሸፍ አለብን። በቀጣይም በአገራችን ውስጥ የሠላይ ሥራአጥ ነጮች ክምችት፣ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና በሌሎች በሚመለከታቸው የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ሊደረግበት ይገባል።
ደምስ ጫንያለው(ዶ/ር)ን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014


