“ክህሎት የሌላቸው ፖለቲከኞች የጫሩት እሳት ኢትዮጵያን ትልቅ ዋጋ እያስከፈላት ነው”

0
1055

ዶክተር ወሮታው በዛብህ ይባላሉ። የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነት ባለሙያ ናቸው። በአሁኑ ወቅት የአእምሮ የኢንተርፕርነርሺፕ ማስፋፊያ አገልግሎቶች አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅና የቦርድ አባል ናቸው። ሰባት መጻሕፍትን ለብቻቸውና ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሆን አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል። በርካታ የሥልጠና ሲዲዎችንም በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች አቅርበዋል። በመምህርነት ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት እኚህ ምሁር፣ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ እስከ ዩኒቨርስቲዎች ድረስ አስተምረዋል። ኢንተርፕራይዝ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ተቋማት በአሰልጣኝነትም ያገለገሉ ሲሆን፣ በፕላን ኢንስቲትዩት በኢኮኖሚ ተመራማሪነት ሠርተዋል። ስለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ከወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ አንፃር፣ እንዲሁም የምዕራባውያን ጫና በሥራ አጥ ቁጥር ላይ ስለሚኖረው ሚና ከአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አእምሮ የኢንተርፕርነርሺፕ ማስፋፊያ አገልግሎቶች አክሲዮን ማኅበር ምን ምን ተግባራን እያከናወነ ይገኛል?
የአእምሮ የኢንተርፕርነርሺፕ ማስፋፊያ አክሲዮን ማኅበር በአሰልጣኞች የተቋቋመ፣ ኢንተርፕርነርሺፕን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት የተመሠረተ ነው። በ1992 ሥልጠናውን ለመጀመሪያ ጊዜ ወስጄ ዕውቀቱን ካገኘሁ በኋላ፣ ከአሰልጣኝነት ወጥቼ የራሴን ነጻነት ካወጅኩ በኋላ ነው ድርጅቱን ያቋቋምኩት። የራሴን ተቋም መመሥረት እንዳለብኝ እንደወሰንኩ ወዲያውኑ ከዩኒቲ ምክትል ፕሬዝዳንትነትና ዲንነት ለቅቄ ነው የወጣሁት። አዲስ መኪና ሰኞ እንደሚሰጠኝ ተነግሮኝ፣ አርብ ዕለት ነው መልቀቂያዬን ያስገባሁት። ለአንድ ዓመት ኢንተርፕራይዝ ኢትዮጵያ ገብቼ ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ውስጥ ካሰለጠንኩ በኋላ አቆምኩ። በአንድ ዓመት ቆይታዬ ውስጤ የነበረኝን እልህ ተረድቼ የራሴን ድርጅት ማቋቋም አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። አገኝ የነበረውን የ6ሺሕ ብር ደሞዝ ተሰናብቼ የራሴን ድርጅት አቋቋምኩ።

ድርጅቱ ከተቋቋመ አንስቶ እስካሁን 930 ዙር ሥልጠናዎችን ሰጥቷል። በእነዚህ ሥልጠናዎች ካገኘሁዋቸው መካከል 47ቱን ይዤ፣ ሌሎች አራት ጨምረን 51 ሆነን የአእምሮ የኢንተርፕርነርሺፕ አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር የሚሰጣቸውን ሥልጠናዎች እያከናወንን እንገኛለን። ድርጅቱ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ ሥራ ፈጠራን(ኢንተርፕርነርሺፕ) ማስፋፋት ነው። ኢንተርፕርነርሺፕ በሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ እንዲካተት የበኩልን ድርሻ ማበርከት፣ ኢንተርፕሬነሮችን በስፋት ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጥሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን፣ በተለይ የይቻላል መንፈስን በሥራ ፈጠራ መንገድ ለወጣቶችና ለሴቶች ማስተማር፣ ለሥልጠና የሚሆኑ መጽሐፎችንና የተለያዩ ማስተማሪያ ቪዲዮዎችን ማዘጋጀት፣ እንዲሁም በተለያዩ ቋንቋዎች ማስተማሪዎቹን በማዘጋጀት፣ ለኹሉም ተደራሽ እንዲሆኑ መሥራት የድርጅቱ ዓላማ ነው። በመደበኛው መንገድ ብቻ ሳይሆን የምሽት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ልምዶችንና ትምህርቶችን ለማስተላለፍ ጥረት ይደረጋል። ከተለያዩ መርሃ ግብሮች ያገኘናቸውን ዕውቀቶች በ6 መጻሕፍት በማዘጋጀት፣ “የብልጽግና ቁልፍ” በሚል ርዕስ አሳትመን የብዙ ወጣቶችን ሕይወት ለመቀየር ሞክረናል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ እንደዋና ዓላማ የያዝነው ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ ኢንተርፕርነርሺፕ የሚባለው የሥራ ፈጠራ ዕውቀት በሥርዓተ ትምህርት ተካቶ ማየት ነው። አንድ ሚሊዮን ሥራ ፈጣሪዎች የተካተቱበትን የሥራ ፈጣሪዎች ተቋምን ዕውን ማድረግም ዓላማችን ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ዓለም አቀፍና አገር በቀል ድርጅቶች ውስጥ በመካፈል በተለያየ ዘርፍ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያንን መፍጠር ነው።

አእምሮ ከተቋቋመ ሰባተኛ ዓመቱን ይዟል። ሥልጠና የሚሰጥ ዩኒቨርስቲ ተቋም እንዲሆንም ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ቦታ ለማግኘት እየጣርን ነው። እኛን እልህ ውስጥ ያስገባን ሥራ መፍጠር እየተቻለ፣ ኢትዮጵያም ጥሩ መሬት፣ ብዙ ሕዝብና በቂ ዕሴት እያላት ችግር ላይ መሆናችን ነው። ስንዴን የመሳሰሉ መሠረታዊ ፍጆታዎቻችንን ራሳችን ማሟላት ያቃተን ሥራ ፈጣሪዎች ቁጥራቸው አነስተኛ በመሆኑ ነው።

በዚህ ሒደት መቀጠል የለብንም። መሬቱንም ሕዝቡንም በአግባቡ መጠቀም አለብን የሚል የእችላለሁ አስተሳሰብን ያነገቡ ሚሊዮኖችን ኢትዮጵያ ውስጥ መፍጠር መቻል አለብን። የራስን ብቃት ማውጣት ችግር ፈቺነት ስለሆነ ውጤቱ ከሕብረተሰብ መሸለም ነው። ዕሴት እየጨመሩ ገቢን የሚያሳድጉንም ሆነ ወጪን የሚቀንሱትን ሥራ ፈጣሪዎችን በብዛት መፍጠር ከተቻለ ለአገሪቱ አስተማማኝ ሠላምና ዕድገት ማምጣት ይቻላል። በዚህ ረገድ በደንብ መሥራት ካልተቻለ ግን መፈናቀል፣ ሥራአጥነትና ኋላቀርነት ይቀጥላሉ። ይህ መሆኑ ደግሞ ለጥገኝነት ይዳርገናል። አሁን የምናየው ክስተት፣ ባብዛኛው ብንሠራ የምንቀድማቸው አገሮች ናቸው ጣታቸውን እየቀሰሩብን የሚገኙት። በቀጣይ 20 ዓመት ሠርተን ኢትዮጵያን ታላቅ አገር እናደርጋታለን የሚል እልህ የያዝን 51 ሰዎችነን ድርጅቱ ውስጥ የምንሠራው።

ኢንተርፕርነሮች ወይም የሥራ ፈጠራ ጥበበኞች ያሏቸው እንዴት ነው ሥራ ይፍጠሩ የሚባለው?
የሥራ ፈጠራ ጥበብ እንደመሬት፣ የሠው ኃብት፣ እንደካፒታል፣ እንደኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ያለ ለሥራና ለሀብት ፈጠራ ግብዓት የሆነ ነው። ይህ ማለት ሐሳብ አፍልቆ፣ ገንዘቡን ተበድሮም ሆነ ከራስ አመንጭቶ፣ የሰው ኃይልን ቀጥሮ፣ ሕብረተሰቡ ውስጥ የሌሉትን፣ ያነሱትን ወይም ጥራታቸው የጎደለ ምርቶችና አገልግሎቶችን ለአገር ውስጥም ለዓለም ገበያም በማቅረብ ተሸላሚ የሚሆን ችግር ፈቺ ጥበብ ነው የሥራ ፈጠራ። ለምሳሌ፣ በቀለ ሞላ በነበራቸው 16 ብር 13 ሆቴሎችን ሠርተዋል። ሳሙኤል ታፈሰም በ500 ብር ጣራ በመጠገን ግድግዳ በመለሰን ተነስተው ዛሬ የ7ሺሕ ሠራተኛ አስተዳዳሪ ሆነዋል። ቀኛዝማች ተስፋዬ ገብረሥላሴ ፊደል ከማዞር ተነስተው የትልቅ ማተሚያ ቤት ባለቤት ሆነው፣ 300 የግዕዝ መጻሕፍትን ወደ አማርኛ ተርጉመው የኢትዮጵያውያን የፊደል አባት ሆነው ለኹላችንም የሚሆን ሥራን አበርክተዋል። በቅርቡ ዘነበ ፍሬውም ሎተሪ ከማዞር ጀምረው የሪል እስቴትና የተለያዩ ፋብሪካዎች ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። ቤተልሄም ጥላሁንም ከወዳደቁ ዕቃዎች ጫማ በመሥራት አሁን ትልቅ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ሥራ ፈጠራ ራስን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ አገርን የሚጠቅምና ሕዝብን ከከፍተኛ ወጪ የሚታደግ ተግባር ነው።

ዋናው ሐሳቡን ማፍለቅ ነው። ገንዘቡን ከባለሃብት ማሰባሰብም ሆነ ከባንኮች መበደር ይቻላል። ሐሳቡ ካለ ሰው ቀጥሮ በአጭር ጊዜ መለወጥ ይቻላል።

አንዳንዶች ትልቅ ቦታ ለመድረስ የተፈጥሮ ብቃትና የግል ጥረት ይጠይቃል እንጂ በሥልጠና የሚገኝ አይደለም ይላሉ። እዚህ ላይ ምን አስተያየት አሎት?
እንዲህ ማለት ይቻላል። እነበቀለ ሞላን የመሳሰሉ ባለሃብቶች የደረሱበት የተገኙት ትምህርት ቤትም ሳይገቡ ነው። አሁን ግን በሥራ ፈጠራ ዙሪያ ያሉት ባለሃብቶች ግን ሠልጥነው ተምረው የደረሱበት ነው። አማራጭ መኖሩን ማየት የሚቻለው አንዱ በትምህርት ነው። ግንዛቤ የሌለው ሰው አማራጩ በጣም ጠባብ ነው የሚመስለው። በተለይ በቀለም ትምህርት ላይ አተኩረው ዕድሜያቸውን ላሳለፉ የእኔ አይነት ሰዎች በንግድ መለወጥ ከባድ ይመስላቸዋል። የተቀጣሪነት መንፈስ የነበረንን እኔን የመሰሉ ሰዎች እኛ አሁን የምንሰጠውን መሰል ሥልጠና በማግኘታቸው ሕይወታቸው ተቀይሯል። በተለይ የተማሩ ዜጎች እየሠለጠኑ ወደተለያየ ሥራ ገብተዋል። ለምሳሌ፣ እኔና ጓደኞቼ ሥልጠናውን ባናገኝ ኖሮ እንዲህ አይነት ሥራ ላይ አንሠማራም ነበር። እኔ አሁን ጡረተኛ ሁኜ እቤቴ ተቀምጬ ማገልገልም አልችልም ነበር።
ስኬት በሥልጠናም በተፈጥሮም ይገኛል። ለዚህም ነው ዓለም ኢንተርፕርነርሺፕን በዶክትሬት ደረጃ የምታስተምረው። እነሄነሪ ፎርድ፣ እነሮክ ፌለር ትምህርታቸውን አቁመው ግዙፍ ፋብሪካዎች ያቋቋሙት፣ እንዲሁም በርካታ የአገራችን ባለሃብቶች ትልቅ ደረጃ የደረሱት ተፈጥሮ በሠጠቻቸው የፈጠራ ብቃት ተጠቅመው ስለጣሩ ነው።

በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ “ሐሳብ አልቸገረንም ያጣነው መሥሪያ ገንዘብና ለመበደሪያ ዋስትና የሚሆን ነው” ሲሉ ይደመጣሉ፤ ይህን እንዴት ያዩታል?
በዚህ ሐሳብ አልስማማም። ለምሳሌ ሎተሪ የደረሳቸው ገንዘቡን ተጠቅመው ትልቅ ቦታ ደረሱ የሚል መረጃ እስካሁን የለኝም። ሐሳብ ኖሯቸው አቅም የሚያጡ ቢኖሩም፣ ገንዝብ ብቻውን ለመለወጥ ምክንያት አይሆንም። ሎተሪ የደረሳቸው፣ ሎተሪ ያዞሩ እንደነበሩት እንደአገራችን ትልልቅ ባለሃብቶች ባለመለወጣቸው ገንዘብ ማግኘት ለስኬት ያበቃል ማለት አይቻልም። በእርግጥ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ትምህርትና ዕውቀትም ያስፈልጋል። በዋናነት ግን 90 በመቶውን የሚይዘው የክህሎት አስፈላጊነት ነው። ክህሎት ማለት ውስጣዊ ቁርጠኝነት፣ ጽናት፣ እልህ፣ ድፍረትና ውሳኔ፣ እንዲሁም ታማኝነትን የሚጠይቅ ነው። ይህ ሳይኖር ወደ ሥራ መግባት በገንዘብም ሆነ በሌላው ረገድ ምንም ስኬታማ አያደርግም። አሁን ብዙዎች የገንዘብ ዕጥረትን ሲያማርሩ ብንሰማም፣ ገንዘብ አግኝተው የሚለወጡ ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው። ባንኮችም ሆኑ መንግሥት ገንዘብ እንፈልጋለን ለሚሉ ለበርካቶች ቢያበድሩም በመክፈል ፈንታ ብዙዎች ሀብቱን ይዘው ጠፍተዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ የጦርነት ሁኔታ አንፃር፣ የሥራ አጥ ቁጥር እየጨመረ ነው መባሉን እንዴት ይገመግሙታል?
ክህሎትና ውስጣዊ እውነት የሌላቸው የፖለቲካ ሰዎች ወደ ጦርነት አስገብተውናል። አሁን ዳቦ ነው ወይስ ጦርነት ነው የሚያስፈልገው? ሥራ ነው ወይስ መፈናቀል ነው የሚያስፈልገው? ሀብትን መጨመር ነው የሚያስፈልገን ወይስ ማቃጠል ነው? ክህሎት የሌላቸው ፖለቲከኞች የጫሩት እሳት ኢትዮጵያን ትልቅ ዋጋ እያስከፈላት ነው። ይህ አሁንም ቢሆን መመለስ የሚችለው በጥበብ ነው። በክህሎት ካልተገነባ ነገም ሌሎች የታወሩ ፖለቲከኞች ሊነሱ ይችላሉ። ክህሎት በየትኛውም ዘርፍ አስፈላጊ ነው። የተሠማራንበት ዘርፍ አገራችንን እንዲጠቅም ነው መሥራት ያለብን። በተለይ የወጣት ግዙፍ ሀብት ስላለን እነሱን ወደፈጠራና ወደተስፋ የሚቀይርን አካሄድ የመምረጥ ያለመምረጥ ጉዳይ ነው። አሁን የተከሰተው በአንድ በኩል የሚያስከፍለንን ዋጋ ያስከፍለናል። በሌላ በኩል ግን በእልኸኝነት አሁንም ከዚህ የበለጠ ታላቅ አገር ለመገንባት፣ ባለጸጋዋን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ዳር እስከዳር እንድንነሳሳ ነው ያደረገን። እንደነዚህ አይነት እኩይ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ያደረጉት ተግባር፣ ምን ያህል ዘረኝነትና ሙሰኝነት አገራችንን እንደበላብን ንቁ ሆነን እንድናይ አድርጎናል።

የ21ኛው ክፍለዘመን ፖለቲካ ብዙ የታወሩ የዓለም መሪዎች ቢኖሩበትም ቀናዎቹ ማንዴላዎችና ጋንዲዎችም አሉ። እውነት የሕብረተሰቡ የመጨረሻ ሀብት መሆኑን፣ ጦርነት ለማንም ምንም የሚፈይደው ነገር እንደሌለ እነጋንዲ አሳይተውናል። የቅኝ ግዛት ሥርዓትን ያለጦርነት ማሸነፍ እንደሚቻል እነማንዴላ አስተምረውናል። ቂም በቀልን አስወግደው ሕብረተሰቡ እንዴት ወደ ሥራ ማተኮር እንዳለበት በተግባር አሳይተውናል። ክህሎት በሌላቸው ፖለቲከኞች የተለኮሰውን ጦርነት እግዚአብሔር እንዲያጠፋልን ኹላችንም የዓቅማችንን ማድረግ እንዳለብን ነው በዚህ አጋጣሚ ማሳሰብ የምፈልገው።

በተለይ በዚህ ሰዓት የውጭ ምንዛሬና ከውጭ የሚገባ የምርት አቅርቦት ዕጥረት ሊያጋጥም ይችላል። ይህን ችግር ለመፍታት ኅብረተሰቡ ወደአገር ውስጥ ምርት ለማተኮር ከፍተኛ እልህና ግብግብ ውስጥ መግባት ይጠበቅበታል። የእኛ የሥራ ፈጠራ ጥበብ በዋናነት የሚያስተምረው ይህንን ነው። ብዙ አገራትን አይቻለሁ፣ ኢትዮጵያ ኹሉም ነገር አላት። ለማደግ የሚያስፈልጉ ነገሮች በሙሉ ስላሏት ወስና መንቀሳቀስ ነው የሚቀራት። እነሱ በበረዶ ተሸፍነው ስንዴ ከሚልኩልን በተፈጥሮ የታደለች አገር ይዘን እኛ ነበርን ለዓለም ስንዴን መሸጥ የነበረብን።
አሁን የተከሰተው ትልቅ ዋጋ ማስከፈሉ ባይቀርም፣ በተቃራኒው ለዓለም ብቃታችንን ልናሳውቅበት የምንችልበትን ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮልናል። ዓለም ትኩረቱን እኛ ላይ በማድረጉ ጦርነቱ ሲያበቃ ነገ በምርትና አገልግሎት እንደቻይና አገራችን የዓለምን ገበያ አልፋ ትገባለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ወደጦርነቱ ልመልሶትና፣ ወታደርነት ሥራ ስለታጣ የሚገባበት ዘርፍ ሊሆን ይችላል?
ወታደርነት ቀርቶ፣ የትኛውም ሙያ ሥራ ስለታጣ የሚገባበት መሆን የለበትም። ወታደርነት ሕይወትህን የምትሰጥበት እንጂ፣ ገንዘብ የምታገኝበት አይደለም። ሌሎች ሥራዎች ሥራው ቢታጣ ገንዘብ ነው የሚታጣበት፤ ወታደርንት ግን ሕይወት ነው የሚሰዋበት። ወታደርነትና አገርነት እኩል ናቸው። ወታደር ሕይወትን ለመገበር የቆመ ዘብ ነው። እጅግ የተከበረ ትልቅ ዋጋ ልንከፍልለት የሚገባን ሙያ ነው ወታደርነት።

በቀድሞ ዘመን ወታደሮችና በአሁኑ ወታደሮች መካካል ከአመላመል ጀምሮ ልዩነት ያለ ይመስሎታል?
አሁን ስላለው ጠለቅ ያለ ዕውቀት ባይኖረኝም፣ ከሚዲያ ከምሰማውና ከማየው አሁን ያለው ተነሳሽነትና ቆራጥነት የሚያስደንቅ ነው። በአራቱም መዓዘናት ከተዋጊው ጀምሮ ስንቅ አቀባዩም ሆነ፣ ደጀን ሆኖ የሚደግፈውን ሕዝብ ከተመለከትን ኢትዮጵያ እንዴት ዕድለኛ አገር እንደሆነች እንገነዘባለን። ከመሪዋ ጀምሮ ኹሉም በእልህ እየተመመላት ያለ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። ዓለም ከኢትዮጵያ ብዙ ነገር መማር ይገባዋል። ዘረኝነት በቅቶናል። አሁንም እያባላን ቢሆንም፣ ገና ሰንኮፉ አልተነቀለም። ዘረኝነትን የሚነቅልልን ሥራና ዕድገት ነው።

ቀስቃሽ ንግግሮችን በማድረግ እንደመታወቅዎ፣ በአንድ ጦርነት ወቅት የሠራዊቱ የመዋጋት ሞራል እንዲጨምርና እንዲጀግን ፉከራና ሽለላ ይደረግ ነበር። አሁን እንዲህ አይነት ተግባሮች ከተማ ላለነው በሚዲያ ከመቅረቡ ውጭ ለተዋጊው ቀጥታ ግንባር ላይ አይደረግም የሚሉ አሉ። እዚህ ላይ ምን አስተያየት አሎት?
ባህላዊ የሆኑትን መንገዶች ማንም በምንም አይተካቸውም። የኢትዮጵያ ባህላዊ መቀስቀሻ መንገዶች የሆኑት ቀረርቶ፣ ፉከራና ሽለላዎችን የሚተካ ነገር የለም። አሁንም የሚያስፈልጉ ናቸው። ኹላችንም ሲከፋንና አገራችን ስትበደል የምናጉረመርምበት ዜማ አለን። ከባህላዊዎቹ ከፉከራና ሽለላ ጎን ለጎን አነሳሽና ቀስቃሽ የሆኑ ንግግሮች በየግንባሩ ያስፈልጋሉ። የኢትዮጵያ አንዱ ትልቁ ጦሯ ቀረርቶና ሽለላ ነው ብዬ አስባለሁ። ዜማ የሰውን ስሜት ቀስቅሶ የአገር ፍቅር ውስጣችን እንዲሰርጽ የማድረግ አቅም አለው።

በየጦር ሜዳው እየተገኙ የሚቀሰቅሱት በተለምዶ አርቲስቶች ናቸው። በየቴሌቪዥኑ የምናያቸው የቀስቃሽ ንግግር ባለሙያዎች ግን ያን ያህል ሠራዊቱን ግንባር ተገኝተው ሲያበረታቱ አይታይም መባሉን እንዴት ይመለከቱታል?
አነቃቂ ንግግር የሚያደርጉ የሌሎችን ያህል አይደለም እንጅ መሄዳቸውን አውቃለሁ። በቀጣይም ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር አብረን መሄድ አለብን ብዬ አምናለሁ። እኔ የምለው የተጠቃነው ሥራ ባለመፍጠራችንና አቅማችንን ባለማጎልበታችን ነው ብዬ አምናለሁ። እንደ እኔ ለዚህ ኹሉ ያበቃን ሥራ ፈጣሪ ጥበብ በአገራችን ባለመስፋፋቱ ነው። ዘረኝነት፣ ምቀኝነት፣ ተንኮልና ሞት የተስፋፋው ሰው ውስጡ ያለውን አልማዝ ባለማወቁ ነው። ሠው ውስጡ ያለውን ማውጣት ቢችል ከራሱ ተርፎ ለአገርም የሚትረፈረፍ ነገር መፍጠር ይችል ነበር። አሁን ያለንን እልህ እናቀጣጥለውና ጥገኝነትን እናስቀር። ተመጽዋችነትንና ድህነትን መጥላት አለብን። ኢትዮጵያ በሕዝቧና በተፈጥሮ ስጦታዋ ልክ ታላላቅ ነገሮችን መሥራት ትችላለች። ዕድሉን ማግኘት ከቻልን በግንባር ተገኝተን እኛም አነቃቂ ንግግር ለማድረግ ፈቃደኞች ነን።

ከምዕራባውያኑ ጫና አኳያ በሥራ አጥ ቁጥር ላይ ተጽዕኖ የሚኖረው ተግባርን እየፈጸሙ እንደሆኑ ይታመናል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አሎት?
እውነት ነው የእነሱ ተግባር በሥራአጥ ቁጥር ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። የመጨረሻ ግባችን የሚሆነው ግን ራስን በራስ መቻል ነው። ሰው ሲቸገር ነው ሐሳብ ማፍለቅ የሚችለው። ኹሉ ነገር በተመቸ መንገድ ሲሆን የፈጠራ ክህሎትም አይወጣም። ችግር ካልገጠመን በእልህ አማራጭ የመፈለጋችን አዝማሚያ ዝቅተኛ ነው የሚሆነው። አንዱ መፍትሔ ሕብረተሰቡ የውጭ ምርት መጠቀሙን መተውና ጥራት ያለውን ምርት እዚሁ ማምረትና በአጎዋ አማካይት ለውጭ ይቀርብ የነበረን እየገዙ ሥራ አጡ እንዳይጨምር ማድረግ ይጠበቃል። ኹሉም እነዚህን ድርጅቶች መተባበር አለበት ብዬ አስባለሁ።

በሌላ በኩል ሌሎች ምርቶቻችንን የምንልክባቸውን ቀጠናዎች መፈለግ አለብን። ሥራአጥነትን ምዕራባውያን በሰጡን አጎዋን በመሳሰሉ መንገዶች አይደለም የምንቀርፈው። የእነሱ ጫና ችግር አይፈጥርብንም ባልልም፣ ችግሩን ተቋቁመን መፍትሔ የሚሆነንን ነገር ለመፈለግ አቅማችንን ያሳድግልናል። በኢንቨስትመንትም ሆነ በሌላው መስክ ሌላ አማራጭ እንድንፈልግ የምዕራባውያኑ ተጽዕኖ ሊረዳን ይችላል። የውጭ ምርቶችን ማምለክ ትተን የአገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም መጀመር አለብን። ኩባና ራሺን የመሳሰሉ አገራት በተደጋጋሚ ማዕቀብ ቢጣልባቸውም ግፊቱን ተቋቁመው እዚህ ደርሰዋል። የምዕራባውያኑ ገበያ ስላለ አይደለም ኢትዮጵያ የምትኖረው።

በመጨረሻም ለየትኛውም አገር የሠላም ዋስትና የሥራ ፈጠራ ጥበብ መሆኑን መረዳት ይገባናል። ይህን ትልቅ ሐብት በሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ አካተን የኢትዮጵያውያንን አእምሮ የመቅረ ጽን ታላቅ ሥራ በአብዮት መልክ ጀምረን ማቀጣጠል አለብን።


ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here