በአዲስ አበባ የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነት መንገድ ላይ በሚገኘው ሀብ አዲስ ሆቴል ሥር ያለው የኤርሚያስ አመልጋ ጤና አዳም ሬስቶራንት ሠራተኛኞች፣ ደሞዝ በአግባቡ እየተከፈላቸው እንዳልሆነ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በዕውቁ ባለሀብት እና ሥራ ፈጣሪ ኤርሚያስ አመልጋ ባለቤትነት የሚተዳደረው ጤና አዳም ሬስቶራንት ሠራተኞች ደሞዝ እንደሚቆራረጥባቸውና አሁን ላይ እየተከፈላቸው እንዳልሆነ ነው የገለጹት። በዓመት ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ለምግብ ቤቱ እንደሚከፍል የተነገረለት ሬስቶራንቱ፣ በሥሩ ከኃምሳ በለይ ሠራተኞች እንደሚያስተዳድር ነው ለማወቅ የተቻለው። ሬስቶራንቱ ደሞዝ በአግባቡ ካለመክፈሉ በተጨማሪ፣ ከተጠቃሚ ደንበኞች የሚሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያ በየወሩ መጨረሻ ላይ ተሰልቶ ሠራተኞቹ ማግኘት ሲገባቸው እያገኙ አለመሆኑን ነው የገልጹት።
ከሠራተኞች መካከል የወር ደሞዟ በተደጋጋሚ ባለመከፈሏ ምክንያት ወደ ክስ የገባች አንዲት ወጣት፣ በፍርድ ቤት አስገዳጅነት ክፍያውን ብታገኝም፣ ከሥራ ደረጃው ዝቅ ብላ እንድትሠራ በአስተዳደር በኩል ተወስኖባት ዳግም ፍርድ ቤት በመሔድ ወደ ቀድመው ሥራ ገበታዋ መመለስ መቻሏን አዲስ ማለዳ ሠምታለች።
ከጤና አዳም ሬስቶራንት ሠራተኞች መሀል ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሠራተኛ የኹለት ወር ደሞዛቸው እንዳልተከፈላቸው ገልጸው፣ የቤተሰብ ኃላፊ በመሆናቸው ከኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ ችግር ላይ እንደወደቁ ገልጸዋል።
ኹለት እና ሦስት ወራትን ያለደሞዝ እንዴት መኖር ይቻላል ብለው ለሬስቶራንቱ ባለቤት ኤርሚያስ ጥያቄ እንዳቀረቡ የሚገልጹት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ የተሰጣቸው መልስ ግን እንዳሳዘናቸው ጠቁመዋል።
“ሥራ ማግኘት በአሁኑ ወቅት ከባድ ነው፤ ሆቴሎች ከወቅታዊ ኹኔታ ጋር በተያያዘ ብዙዎቹ ተዘግተዋል። ያለን አማራጭ አገራዊ ኹኔታ እስኪረጋጋ መታገስ ነው እንጂ፣ ሥራ ለቀን ወደየትም መሔድ አንችልም” ሲሉ የአዲስ ማለዳ ምንጭ ምሬታቸውን ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ወደ ድርጅቱ አስተዳደር ስልክ በመደወል መልስ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ሊሳካ አልቻለም።
ጤና አዳም ሬስቶራንት ከተቋቋመ አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን፣ የሚያቀርበው አገልግሎትም በተመሳሳይ መስክ ላይ ከተሰማሩ ተቋማት የተለየ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በጤናማ አመጋገብ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ጤና አዳም ሬስቶራንት፣ በተለይም ከስኳር እና ከስንዴ ነጻ የሆኑ ምግቦችን ከአትክልት በሚሠራ ተፈጥሯዊ ማጣፈጫ እንደሚያዘጋጅ ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም ከአበባ ጎመን፣ ከጤፍ እና አጃ ዱቄቶች የሚያዘጋጃቸው ኬክ እና ዳቦዎች ሬስቶራንቱን ለየት እንደሚያደርጉት ተሰምቷል።
የሕግ ባለሙያዋ ፌቨን እንዳየሁ ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት፣ ማንኛውም ተቋም አንድ ሠራተኛ የሠራበትን ክፍያ በአግባቡ መክፈል እንዳለበት ሕግ ይደነግጋል። ሆኖም የቀናት መራዘም በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር ይችላል፤ ይህንንም በማኅበራዊ ትስስር በመረዳዳት በመታገስ ሊታለፍ ይችላል፤ ልክ የኮቪድ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በታወጀበት ወቅት የነበረውን ኹኔታ በተከተለ መልኩ፣ በሠራተኛ እና አሠሪ መካከል በሚፈጠር ግንዛቤ ችግራቸውን በውይይት መፍታት ይችላሉ ብለዋል።
ይህ ሳይሆን የቀረ እንደሆነ፣ አሠሪ ወይም ቀጣሪ ተቋም ኪሳራ ገጥሞኛል እንኳን ቢል ንብረቱንም ቢሆን ሸጦ የሚጠበቅበትን ክፍያ፣ የጉዳት ካሳንም ቢሆን ጨምሮ፣ እንዲከፍል ሕግ ያስገድደዋል ሲሉ ባለሙያዋ ገልጸዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014



